የሴቶች ድምጽ

0
100

በርካታ ሀገራት በ20ኛው ክፍለ ዘመን በተለይም ከጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር ከ1915 እስከ 1950 ባለው ጊዜ ውስጥ የነጻነት እንቅስቃሴዎችን ተከትለው ለሴቶች የመምረጥ መብት ሰጥተው እንደነበር ወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው (worldpopulationreview.com) ላይ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡  ሀገራቱ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል የሆነ ሙሉ ሁለንተናዊ የመምረጥ መብት ከማግኘታቸው በፊት መጀመሪያ ላይ ውስን የመምረጥ መብት ነበራቸው፡፡  እነዚህም ዕድሜ፣ ማንበብ እና መጻፍ መቻል እና የንብረት ባለቤትነት  ለሴቶች ለመምረጥ በመስፈርትነት የተቀመጡ ነበሩ፡፡

ቡክስኦፕንኤዲሽን  /books.openedition.org/  ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ ለሴቶች የመምረጥ መብት የሰጠ የመጀመሪያው ግዛት በ1838(እ.አ.አ) የፒትኬርን ደሴቶች ነበር፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አብዛኞቹ ሀገራት ለሴቶች የመምረጥ መብትን ሰጥተዋል፡፡ ይህን ካደረጉት ቀዳሚዋ አውስትራሊያ ናት፡፡ ጊዜውም እ.አ.አ በ1902 ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአገሬው ተወላጆች(ሀገሪቱን የመሰረቷት)እስከ 1962 ድረስ የመምረጥ መብት አላገኙም፡፡

ፊንላንድ በ1906 እ.አ.አ ለሴቶች የመምረጥ መብት ሰጠች፣ ካናዳ ደግሞ እ.አ.አ. በ1917 ተከትላለች፡፡ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ለሴቶች መብት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ምክንያቱም በርካታ የዓለም ታላላቅ ሀገራት በዚህ ጊዜ ነበር ለሴቶች የመምረጥ መብት የሰጡት፡፡ ሀገራቱም ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ዩክሬን፣ ሩሲያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ቤልጂየም እና እንግሊዝ ነበሩ፡፡

የሴቶች ድምፅ ወደ ምርጫ ሳጥን ሲገባ የሚወስነው  ማን ይመራ? የሚለውን ብቻ አይደለም፤ ሴቶችን ማን ይሰማል? ማን ለእናቶች ጤና፣ ለሴቶች ደኀንነት፣ ለሴት ተማሪዎች እድል እና ለእኩል ተሳትፎ ይቆማል? `የሚለውም ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶች የመምረጥ መብት በሕግ የተረጋገጠ  ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (NEBE) የምርጫ ሂደት መመሪያ እንደሚያሳየው የተመዘገቡ ዜጎች ሁሉ በምርጫ ቀን በተመዘገቡበት ጣቢያ በሚስጥር እና በነፃነት ድምፅ መስጠት ይችላሉ፡፡ ነፍሰ ጡሮች፣ እናቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች በመመዝገብና በመምረጥ ሂደት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ተጠቅሷል፡፡ ይህ የሕግ መብት በተግባር ሲጠቀሙበት እውነተኛ ኀይል እንደሚሆን መረጃው አክሏል፡፡

የኢንተር-ፓርላማ ሕብረት (IPU) እንደሚለው ሴቶች የፈለጉትን የፖለቲካ ፓርቲ እና መሪ ሲመርጡ የራሳቸውን ድምፅ ወደ ፖሊሲ መቀየር ያስችላቸዋል፡፡ ሴቶች በምርጫ ወቅት በጥንቃቄ መሪያቸውን ሲመርጡ የቤተሰብ እና የማሕበረሰብ ችግር ወደ መንግሥት አጀንዳ ማምጣት ይችላሉ፡፡ ለአብነትም የእናቶች ጤና አገልግሎት፣ የሴቶች የወሊድ እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ የትምህርት እኩልነት፣ የፆታ ጥቃትን መከላከል፣ የሥራ እድል እና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ያሉ ጉዳዮች በሴቶች ድምፅ ብርታት የበለጠ ቦታ ያገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፓርላማ የሴቶች ውክልና መረጃ እንደሚያሳየው ሴቶች በንቃት ድምፅ ሲሰጡ የሴቶች ፖለቲካዊ አቅም እና ተሰሚነት ይጨምራል፡፡ ተሰሚነታቸው እየጎላ በመምጣቱም  ሴቶች ከመምረጥ ወደ መምረጥ ተሸጋግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አሁን ያሉት ሴት አባላት 202 ሲሆኑ ይህም 41ነጥብ 9 በመቶ ነው፡፡ ይህ ቁጥር በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ከተሻሉ ሀገራት መካከል ያስገባታል፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤትም 43 ሴቶች አሉ፤ ይህም 29 ነጥብ 7 በመቶ ነው፡፡ እነዚህ ቁጥሮች የሴቶች ድምፅ በተደጋጋሚ ሲጠናከር የፖለቲካ ውክልና እንደሚጨምር ያሳያሉ፡፡

ሴቶች ድምፅ ሲሰጡ የሚፈጠረው ፖለቲካዊ ውጤት ብቻ  አይደለም፤ የራስ ክብር እና የእኩል ዜግነት ስሜትም ነው፡፡ ሴቷ  እንደ ወንዱ  በሀገሯ ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንደምታሳድር ስትረዳ  የፖለቲካ ተሳትፎዋ ከምርጫ ቀን በላይ ይሄዳል፡፡ ከዚያ በኋላ በሕዝብ ውይይት፣ በአካባቢ አመራር፣ በማሕበራዊ ድርጅቶች እና በፓርቲ ውስጥ የምታሳየው ንቃት ይጨምራል፡፡

ሴቶች በምርጫ መሳተፋቸው ደግሞ  ለሚቀጥለው ትውልድ አርአያ ይሆናሉ፡፡ እናት የምርጫ መብቷን በንቃት ስትጠቀም ልጆቿ ዴሞክራሲን በቤት ይማራሉ፡፡ ሴቶች በፖለቲካ ሂደት ላይ ሲታዩ ሴት ልጆች “መሪ መሆን ይቻላል!” የሚል እምነት ያገኛሉ፡፡ ይህ የትውልድ ትምህርት ነው፤ ዛሬ የተሰጠ ድምፅ ነገ የሴት አመራር መሠረት ሊሆን ይችላል፡፡

ሴቶች በብዛት እና በንቃት ድምፅ ሲሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ለምርጫው እንደ ኀይል መቁጠር ይጀምራሉ፡፡ ይህም ፓርቲዎች በመመሪያቸው ውስጥ የሴቶች ጉዳይ እንዲገባ፣ በአመራር ደረጃ ሴቶችን እንዲያበረታቱ እና የሴት ዕጩዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋሉ፡፡

ኢትዮጵያ በምርጫ የላቀ ልምድ አላት፡፡ ይሁናን ጉዞው ገና አልተጠናቀቀም፡፡ በኢትዮጵያ የሴቶች የፓርላማ ውክልና ከብዙ ዓመታት በኋላ ከፍ ብሏል፡፡ የዪኤን ውሜን (UN Women ) ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት እ.አ.አ በ1995 ዓ.ም. በፓርላማ ውስጥ ያሉ ሴቶች ሁለት  በመቶ ብቻ ነበሩ፤ በ2010 ደግሞ ከ21 እስከ 22 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ በ2015  የፓርላማ አባላት ሴቶች 38 ነጥብ 8 በመቶ ደርሰዋል፡፡

ድምፅ መስጠት የመጨረሻ ሳይሆን የመጀመሪያ ርምጃ ነው፤ ሴቶች መሪያቸውን እና ፓርቲያቸውን መምረጥ መቻላቸው ትልቅ ነገር ነው፤ ነገር ግን ይህ የመጨረሻ አይደለም፡፡ ድምፅ ከሰጡ በኋላ የመረጡትን አመራር መጠየቅ፣ ተስፋ የተሰጡ ፕሮግራሞች ተፈጻሚ እንደሆኑ መከታተል፣ በሕዝብ ውይይት መሳተፍ እና ከአካባቢ የሴቶች ማሕበራት ጋር መሥራት የዴሞክራሲ እውነተኛ ግንባታ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሴቶች በምርጫ ወቅት መሪያቸውን እና የፖለቲካ ፓርቲያቸውን መምረጣቸው የሚያስገኝላቸው ጥቅም ከአንድ የድምፅ ወረቀት በላይ ነው፡፡ ስለዚህ የሴቶች ድምፅ በምርጫ ቀን የሚሰማ ብቻ አይደለም፤ በሀገር ታሪክ ውስጥ የሚቀር ድምፅ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶች የመምረጥ መብት በሕግ ደረጃ

“በኢትዮጵያ ሴቶች የመምረጥ  ሙሉ መብት አላቸው፤ ነገር ግን በተግባር አንዳንድ እንቅፋቶች አሉ” በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 38 መሠረት በሕግ ደረጃ ሴቶች ሙሉ የመምረጥ መብት አላቸው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በፆታ ልዩነት ሳይደረግ 18 ዓመት ከሞላ በኋላ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት አለው/አላት፡፡ ማለትም ሴቶች እና ወንዶች በሕግ ፊት እኩል የምርጫ መብት አላቸው፡፡

እንደ ዓለም አቀፍ የፓርላማ መረጃ ቋት (IPU) በኢትዮጵያ ሴቶች የመምረጥ መብታቸውን ያገኙት  ከጎርጎሮሳዊያኑ ከ1955 ጀምሮ ነው፡፡ በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ከተመዘገቡ መራጮች ውስጥ  54 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ 46 በመቶ ደግሞ ሴቶች ነበሩ፡፡ ይህ አሃዝ ሴቶች በብዛት እየተሳተፉ እንዳሉ ያሳያል፡፡ ይሁንና  ከወንዶች ጋር እኩል ገና አልደረሱም ማለት ነው፡፡

ስለዚህ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ  እድሜያቸው ከ18 ዓመት ጀምሮ የሚገኙ  ሴቶች መብታቸውን እንዲጠቀሙ እንመክራለን፡፡

በኢትዮጵያ በመጭው ግንቦት 24 በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ሴቶች የሚወክላቸውን ለመምረጥ ቅድሚያ የሚፈለጉትን መስፈርቶች በማሟላት እንዲመዘገቡ የአማራ ክልሉ ሴቶች ፣ ወጣቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ የሴቶች በተመራጭነት ተወዳድሮ ማሸነፍ የራሳቸው ጉዳይ በራሳቸው ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡

ሴቶች በመራጭነት መመዝገባቸው የሚወክላቸውን ለመምረጥ ድምጻቸው ትልቅ ዋጋ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያሉ ተቋማት ሴቶችን ተሳታፊ ለማድረግ ግንዛቤ እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

“የሴቶች ድምጽ ዋጋ ስላለው የድምጽ መስጫ ካርድ ላወጣ መጣሁ” ያሉን በባሕር ዳር ከተማ በበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ   በምርጫ ጣቢያ 07 ሁለት ለ” ያገኘናቸው ወይዘሮ መሪዎቻቸውን ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ምዝገባ ለማድረግ እንደመጡ ተናግረዋል፡፡ “ድምጼ የምፈልገውን መሪ ለመምረጥ ዋጋ አላት” ያሉን ወይዘሮዋ   ሌሎች ሴቶችም መሪያቸውን እንዲመርጡ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚ  አቶ ታደሰ መስፍን በበኩላቸው  በጣቢያው እስካሁን/እስከ መጋቢት 11/2018 ዓ.ም/ድረስ  ካርድ ካወጡት መካከል አብዘኛዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ እኛም በቦታው በተገኘንበት ወቅት አብዛኞቹ ተመዝጋቢዎች ሴቶች መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡

 

ማን ናት

ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ  ጥር 6 ቀን 1908 ዓ.ም. በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በመናገሻ አውራጃ በአዲስ ዓለም ከተማ ተወለዱ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ቀዳሚዋ ሴት አርበኛ፣ መምህርት፣ ፀሐፌ ተውኔት፣ የፓርላማ ተመራጭ እና የመብት ተሟጋች ነበሩ፡፡ የከንቲባ ገብሩ ደስታ ልጅ የሆኑት እኝህ ታላቅ ሴት በአውሮፓ (ጀርመንና ስዊዘርላንድ) ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ወይዘሮ ስንዱ በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በብዕር ተጋድሏቸውና አርበኝነታቸው በስፋት ይታወቃሉ፡፡

በትምህርት ሚኒሥቴር ውስጥ በመምህርነት እንዲሁም በደሴ እና በአዲስ አበባ (እቴጌ መነን) ትምህርት ቤቶች በዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡ በርካታ ተውኔቶችንና ስነ-ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆን በተለይም “የጥንት ዘመንና የዛሬ ትውልድ” የተሰኘው ተውኔታቸው ይታወቃል፡፡ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ በኢትዮጵያ የሴቶች እኩልነትና የትምህርት ዘርፍ ትልቅ አሻራ ጥለው ያለፉ አርአያነት ያላቸው ታሪካዊ ሰው ናቸው፡፡

ምንጭ:-ሰዋሰው

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here