የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ማሕበራቱ ምን ፈየዱ?

0
83

መግቢያ

የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት  በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 813/2006 መግቢያ ላይ ከተቀመጡት መሠረታዊ ነጥቦች ውስጥ “ለሸማቹ ማሕበረሰብ ጤናማ የግብይት ሥርዓትን መዘርጋት እና ሸማቹ ካወጣው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል” የሚለው ይገኝበታል፡፡ በማሕበራቱ አገልግሎት ለመጠቀም ለሚፈልጉ እና የአባልነት ግዴታዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ በጾታ፣ በማሕበራዊ አቋም፣ በዘር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በአካል ጉዳተኝነት ወይም በሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ ለሁሉም አገልግሎቶቹን መስጠት የሚሉት ደግሞ መሠረታዊ መርሆቹ እንደሆኑም በአዋጁ ተመላክቷል፡፡

የነዋሪዎችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ እና የኑሮ ውድነትን መቀነስ የማሕበራቱ ዋና ዓላማም ነው፡፡

ዘ ጋርዲያን ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው የመጀመሪያ የሕብረት ሥራ ማሕበር የተቋቋመው እ.አ.አ በ1761 ስኮትላንድ ውስጥ ነው፤ ለማሕበራት መቋቋም ምክንያቱ ደግሞ ስኮትላንዳዊ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች በዱቄት ጥራት መቀነስ እና በዋጋ ውድነት መማረራቸው ነበር፡፡ በመሆኑም ማሕበረሰቡን በማደራጀት ማሕበሩ እንደተጀመረ ነው

መረጃው የሚጠቁመው፡፡ ማሕበሩም ጥራቱን የጠበቀ ዱቄት ለማሕበሩ አባላት በቅናሽ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ ችሏል፡፡

 

ይህም የሕብረት ሥራ ማሕበራት በተለያዩ አካባቢዎች እና ሀገራት እንዲስፋፉ አድርጓል፤ ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እያደገ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደግሞ በአውሮፓ በተለይም በእንግሊዝ ተስፋፍቷል፡፡

በሀገራችንም የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት በቀዳማዊ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን እንቅስቃሴ ማድረግ ቢጀምሩም የተጠናከረ ሥራ የጀመሩት ግን በ1967 ዓ.ም አካባቢ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፤ ለዚህ አብነት የሚጠቀሰው ደግሞ መሬት ለአራሹ የሚለው አዋጅ ቁጥር 31/1967 ነው፡፡ ይህን አዋጅ ለማስፈፀም ኃላፊነት ከተሰጣቸው አካላት አንዱ የሆነው የኢንዱስትሪና የሀገር ውስጥ ንግድ ሚኒሥቴር የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራትን እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሕብረት ሥራ ማሕበራት በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋት ችለዋል፡፡

የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ የሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራት ከአምራቾች ጋር በቀጥታ ግንኙነት በመፍጠር እየሠሩ መሆኑን የአማራ ክልል ሕብረት ሥራ ኮሚሽን አስታውቋል፤ ማሕበራቱ “የዋጋ ግልጽነት እና የክፍያ እፎይታ አገልግሎት እያበረከቱ ነው”ም ብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚታየው የኑሮ ውድነት እና የገበያ አለመረጋጋት በማሕበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ ነው፡፡

የመሠረታዊ ምግብ እና ሸቀጣ ሸቀጦች  ዋጋ በፍጥነት መጨመር በተለይ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ክፉኛ እየፈተነ ይገኛል፤ አብዛኛው ነዋሪ የገቢ መጠኑ ዝቅተኛ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በግጭቶች ምክንያት እንቅስቃሴዎች መገደባቸውም የገበያ እጥረትና የአቅርቦት መዘግየት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የኑሮ ውድነቱ እንዲጨምር አድርጓል፡፡

የዋጋ መናርን ለመቀነስ እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ከሚያስችሉ አማራጮች መካከል ደግሞ የሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህን መሠረት በማድረግም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት በትኩረት እየሠሩ እንደሚገኙ ነው የክልሉ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ያስታወቀው፡፡

ሐሳባቸውን ለበኩር የሰጡ ሸማቾች በበኩላቸው የኑሮ ውድነቱ በየዕለቱ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፤ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋም በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ፣ ኑሮም ፈታኝ እንደሆነ አክለዋል፡፡ የሕብረት ሥራ ማሕበራትን በማጠናከር መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እንደሚያደርጉም ነው ያነሱት፡፡

በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማሕበራት ተጠቃሚ እንደሆኑ የገለጹልን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ የሺዋስ ጌትነት አንዱ ናቸው፡፡ ነዋሪው  እንደነገሩን ከሕብረት ሥራ ማሕበራት የገዙት  ዕቃ ዋጋ  ከግል ሱቆች ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ቅናሽ አለው፡፡ “አንድ ኪሎ ስኳር ከገበያ 200 ብር ሲሸጥ እኔ ከሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበር በ165 ብር ገዝቻለሁ፡፡ ይህ ልዩነት ቀላል አደለም፡፡ ሁሉንም የወር ፍጆታየን  ከማሕበራቱ ገዝቻለሁ” ሲሉ ነው የማሕበራቱን አበርክቶ የጠቀሱት፤ በዚህም ከተጨማሪ ወጭ መዳናቸውን  ነው የገለጹት፡፡

ነዋሪው አክለውም በየጊዜው እየናረ የሚሄደው የኑሮ ውድነቱን እና የፍጆታ ዕቃዎች የዋጋ ንረት ለመቀነስ የሕብረት ሥራ ማሕበራት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፤ በመሆኑም ማሕበራቱን በማጠናከር ለነዋሪው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ ሐሳቧን ያካፈለችን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ፋሲካ መላኩ በበኩሏ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባለፈ  በክፍያ እፎይታ መግዛት እንዳስቻላት ትናገራለች፡፡ ወጣቷ እንዳብራራችው በአንድ ጊዜ ክፍያ ትገዛ የነበረውን ጤፍ ከሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበር በሁለትና በሦስት ዙር ክፍያ እንድትገዛ ዕድል ፈጥሮላታል፤ ይህም ኑሮን አቅሎላታል፡፡ ይህ የክፍያ ሥርዓት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች  ተጠቃሚ  የሚያደርግ ነው፡፡

የሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራት በመሠረታዊነት አባላትን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በተረጋጋ አቅርቦት ለማገልገል የተቋቋሙ  ናቸው፡፡ እነዚህ ማህበራት ከአምራቾች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት ለመግዛት ያስችላሉ፡፡ በተጨማሪም ማሕበራቱ የምርት ክምችቶችን በማስተዳደር የገበያውን እንቅስቃሴ ማስተካከል ይችላሉ፡፡

የሕብረት ሥራ ማሕበራት የምርት እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ዕቃ በማቅረብ ዋጋ እንዳይጨምር ያደርጋሉ፤ በተቃራኒው በቂ ምርት ሲኖር በማከማቸት ወደ ፊት ሊከሰት የሚችል እጥረትን ይቆጣጠራሉ፡፡ ይህ ተግባር በተለይ በምግብ እና በሌሎች መሠረታዊ ዕቃዎች ገበያ ላይ የሚታየውን ዋጋ በመቀነስ የገበያ መረጋጋትን ይፈጥራሉ፡፡

በሌላ በኩል ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለኑሮ ውድነት ሌላው ምክንያት ነው፤ የሕብረት ሥራ ማሕበራት ደግሞ የዋጋ ግልጽነትን በማስፈን ሕገ ወጥ ንግድንም በማስቀረት ጤናማ ውድድር በገበያ ውስጥ እንዲኖር ያስችላሉ፡፡

ገበያውን ለማረጋጋት እና ለሽማቹ የክፍያ እፎይታ ጊዜ በመስጠት አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ማህበራት ውስጥ አንዱ የጎተራ ሕይዎት ትሬዲንግ አክሲዎን ማህበር  ነው፡፡ ማህበሩ የግብርና ውጤቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሮች በመግዛት በተመጣጣኝ ዋጋ እና በሁለትና ሦስት ጊዜ ክፍያ ለማህበረሰቡ በማቅረብ ገበያን ለማረጋጋት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል።

የማህበሩ የሂሳብ ባለሙያ አቶ አስማማው ሁነኛው እንደገለፁት ማህበሩ በሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ገበያው እንዲረጋጋ በተለይም በኑሮ ውድነት ወቅት ለማህበረሰቡ የሚገኙ አማራጮችን በማስፋፋት አስፈላጊ ሚና እየተጫወተ  ነው።

በአጠቃላይ የጎተራ ሕይዎት ትሬዲንግ አክሲዎን ማህበር የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት፣ የሸማቾችን የግዥ አቅም ለማጠናከር እና በአርሶ አደሮች እና በሸማቾች መካከል የቀጥታ ግንኙነት በመፍጠር በኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ነው አቶ አስማማው ያብራሩት።

የአማራ ክልል ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌትነት አማረ በአማራ ክልል ከ31 ሺህ በላይ መሠረታዊ የሕብረት ሥራ ማሕበራት ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፤ ከእነዚህም መካከል በተለይ የሸማች ማሕበራት የምርት አቅርቦትን በማስፈን ገበያን በማረጋጋት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ማሕበራቱ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለአባላት በማቅረብ ክፍተትን እየቀነሱ ነው፤ በተጨማሪም የግብርና ምርቶችን በማቅረብ የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡

አቶ ጌትነት እንዳስገነዘቡት መንግሥት ለማሕበራቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፤ ማሕበራት ደግሞ የመንግሥትን ድጋፍ በቀጥታ ለነዋሪው ለማድረስ እንደ ድልድይ የሚያገለግሉ መዋቅር ናቸው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ታዲያ መንግሥት ትኩረት በመስጠት ከማሕበራቱ ጋር በመሥራት የዋጋ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ለማስፈጸም እየሠራ ነው፡፡

በተጨማሪም በለውጥ ሥራዎች መካከል ደካማ ማሕበራትን በማዋሃድ የካፒታልና የአስተዳደር አቅማቸውን የማጠናከር ሥራም ተከናውኗል፡፡  ይህም አገልግሎታቸውን እና የአቅርቦት አቅማቸውን እንዲሻሻል አድርጓል፡፡ ነገር ግን አሁንም በአቅርቦት መጠን፣ በአደረጃጀት እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህን ለመፍታት ከንግድና ገበያ ልማት ቢሮ እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራት የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ፣ የገበያ መረጋጋትን ለማጠናከር እና ለሕዝብ በቂ አቅርቦት እንዲኖር የማይተካ ሚና እየጫወቱ ነው፡፡ ስለዚህ ማሕበራቱን መደገፍ፣ ማስፋፋት እና ከአምራቾች ጋር ቀጥተኛ የአቅርቦት ሥርዓትን ማጠናከር የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር አይነተኛ መፍትሔ ነው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ኮሚሽነሩ አቶ ጌትነት ያመላከቱት፡፡

 

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here