ሴት ተማሪዎችን ለማብቃት ምን ተሠራ?

0
96

በክልሉ የተከሰተው ግጭት ዘርፈ ብዙ ጉዳትን አስከትሏል፤ ሴቶች እና ህጻናት ደግሞ ዋነኛ ተጋላጮች ናቸው። ይህም በትምህርታቸው፣ በአካላዊና በአዕምሮ ጤናቸው፣ እንዲሁም በወደፊት ሕይወታቸው ላይ የሚታይ ጥቁር አሻራ ጥሎ ያልፋል።

ግጭቱ ትምህርት ቤቶች መደበኛ ሥራቸውን እንዲያቋርጡ አድርጓል። እነዚህ የመፈናቀል እና የደህንነት ስጋቶች  ደግሞ በተለይ ሴት ተማሪዎችን ከትምህርታቸው ያርቃል። በቀጣይም ሴቶች ወደ ትምህርት የመመለስ ዕድላቸውን ያሳንሳል፣ በአንዳንድ አካባቢም ፍጹም ሊቋረጥ ይችላል።

ግጭት ያለበት አካባቢ የፆታ ጥቃትን፣ የግዳጅ ጋብቻን እና ሌሎች ማሕበራዊ ጥቃቶችን ይጨምራል። ይህ ሁኔታ ሴት ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት ርቀው እንዲኖሩ ያደርጋል፣ እንዲሁም የቤተሰብን አስተምሬ ለውጤት አበቃለሁ የሚለውን ተስፋ እና የራሳቸውን እምነትም ይፈትናል። በዚህ ምክንያትም የአዕምሮ ጫና እና ስነ-ልቦናዊ ችግሮች ይፈጠራሉ።

ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በግጭቱ ምክንያ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል፤ ይህ ደግሞ በተለይ ሴት ተማሪዎች ለያለ ዕድሜ ጋብቻ እና አስገድዶ መደፈር እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል:: ፍርሃት፣ ጭንቀት እና የአቅመ ቢስነት ስሜት በተማሪዎች ላይ በጣም ይታያል፣ ይህም በመማር ችሎታቸው እና በአጠቃላይ ዕድገታቸው ላይ ከፍተኛ ጫናን ያመጣል።

በአጠቃላይ፣ በክልሉ የተከሰተው ግጭት በተለይ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ብዙ ዘርፎችን የሚነካ ሲሆን፣ ይህን ችግር ለመቀነስ የመንግሥት፣ የማሕበራዊ ድርጅቶች እና የማሕበረሰብ ተቋማት ርብርብ አስፈላጊ ነው።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እየሩስ መንግሥቱ ከበኩር ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ሴቶችን ከማስተማር እና ከማብቃት አኳያ እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል፤ ቢሆንም ግን አሁንም ክፍተቶች ይታያሉ:: ለዚህ ደግሞ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ችግሮቹ እንዲጨምሩ ምክንያት ስለመሆኑ ነው ያነሱት::

በክልሉ የተከሰተው ግጭት ሁለት ዓመታትን ቢሻገርም በአሁኑ ወቅት የሚታየው አንጻራዊ ሰላም ካለፉት ዓመታት የተሻለ የትምህርት እንቅስቃሴ እንዲኖር አስችሏል፤ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን  ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ:: ከዚህ ውስጥ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል::

ወይዘሮ እየሩስ አክለውም “በተለይ የሴት ተማሪዎችን  ተሳትፎ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እየተሠራ ነው”ም ብለዋል:: በዚህም የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲውን አካታች በማድረግ፣ የትምህርት አዋጁ ለሴቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያስችሉ  ሕጎችን በማውጣት፣ የሚዘጋጁ የሥርዓተ ትምህርት መጻሕፍት እና ግብአቶች ሴቶችን ያካተተ ሆኖ እንዲቀረጽ መደረጉን እብነት አንስተዋል::

በቢሮ ደረጃም የሚዘጋጁ መመሪያዎች ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን ነው ወ/ሮ እየሩስ የተናገሩት::

በተመሳሳይ ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ከመጡ በኋላ እንዲበቁ በርካታ ሥራዎችም እየተሠሩ ነው:: የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የትምህርት ዕድል እንዲያገኙም ተደርጓል:: የማጠናከሪያ ትምህርት በልዩ ሁኔታ ለሴት ተማሪዎች እንዲሰጥ መደረጉ ሴቶች እንዲበቁ ከተከናወኑ እና እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል ዋናው ነው::

ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ እንዳሉት ቢሮው የተለያዩ  መድረኮችን በማዘጋጀት፣ ዘግይተው የመጡ ተማሪዎችን ለማስተናገድ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም እንዲማሩ በማድረግ፣ የርቀት እና የማታ ትምህርትን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል::

የሴቶች ክበባትን በማቋቋም፣ በሌሎች ክበባትም የመሪነት ሚናን እንዲጫወቱ በማድረግ ተሳትፎአቸውን እንዲያሳድጉ እና የመሪነት ሚናን ከታች ጀምሮ ልምምድ እንዲያደርጉ እየተሠራም ነው:: በተከናወኑት ተግባራትም አበረታች ውጤት ተገኝቷል:: የሴት ተማሪዎች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለም መጥቷል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ “ሴት ተማሪዎችን ለማብቃት እና ሀገር ከሴቶች  መጠቀም ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ አሁንም የሚቀሩ ብዙ ሥራዎች አሉ” ነው ያሉት:: ለዚህ ማሳያ ደግሞ በተለይ ሴቶች በሚፈለግባቸው ልክ ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ ሀገራዊ ግጭቱ ፈተና የሆኑባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ነው ያነሱት::

በሌላ በኩል በሴት ተማሪዎች ላይ ያለው የተዛባ አመለካከትም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉ ማነቆ ነው፤ ይህ እንዲፈታ ደግሞ ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ ነው፤ ቅንጅታዊ ሥራውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ወ/ሮ እየሩስ ተናግረዋል::

ሴቶች ዘርፈ ብዙ ኃላፊነት አለባቸው፤ በዚያው ልክ ለችግር ተጋላጭነታቸውም ከፍ ያለ ነው:: በመሆኑም በሁሉም ዘርፍ ብቁ ሆነው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ለጥቃት ተጋላጭም እንዳይሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል::

“ሴትን ልጅ ማገዝ እና ማስተማር ቤተሰብን እና ሀገርን እንደማስተማር ነው፤ ሴቶችን ስናስተምር ቤተሰብን እና ሀገርን እንደምናስተምር ማሰብ ይኖርብናል” ሲሉም ነው ወ/ሮ እየሩስ መልዕክት ያስተላለፉት::

 

አማርኛ በአማርኛ

መን- ሽማ መሥሪያ ዕቃ

ሰማያ – የጦር እጀታ

ቧጋች- ለማኝ

ንዳማ – ቁጭት

ቀርፊ- የወጥ ጭልፋ

መርግ – ናዳ

ዘባን – ጀርባ

አንጣር – አቅጣጫ

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመጋቢት 14  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here