የማይደገመዉ አሻራ

0
88

ሁሉም የራሱ መንገድ አለው:: ፀሐይ ከጨረቃ ጋር አትወዳደርም:: ጥቁር ከነጭ ጋር አይነጻጸርም:: አባት ልጁን ሊቀድም፤ ልጅም አባቱን ሊቀድም ይችላል:: ሁሉም ሰው የራሱ ልዩ ቀለም እና አቅም አለው:: አንዱ ከሌላው ጋር አይወዳደርም::

ሕይወትን እንደ ውድድር ማየት እና ራስን ዘወትር ከሌሎች ጋር ማወዳደር የሰው ልጅ ራሱን በገዛ እጁ ከሚያስገባባቸው አሰቃቂ የሥነ-ልቦና እስር ቤቶች አንዱ ነው:: ውድድር መጀመሪያ ላይ የሚያነቃቃና አቅምን የሚያወጣ ቢመስልም መነሻውን ከሌሎች ሰዎች ጋር ባደረገ ቁጥር ወደ ማያባራ የነፍስ ስቃይ እና የውስጥ ባዶነት ይለወጣል::

በውድድር መንፈስ ውስጥ ያለ ሰው ስኬቱን የሚለካው ከሌሎች አንጻር በመሆኑ ሌላው ሲያልፈው በቅናት፣ በቁጭት እና በዝቅተኛነት ስሜት ይቃጠላል:: እርሱ ሲቀድም ደግሞ በጊዜያዊ የትዕቢት ስሜት ይሰክራል እንጂ እውነተኛ ሰላም አያገኝም:: ይህ አዙሪት “በቂ አይደለሁም” ወይም “ገንዘቤ፣ እውቀቴ፣ ውበቴ አነሰ” የሚል የዘወትር የጭንቀት ድምጽ በአእምሯችን እንዲያስተጋባ ያደርጋል:: የሌላው ሰው ስኬታማነት የራሳችን መውደቅ ሆኖ ይሰማናል:: በዚህም ምክንያት የሕይወትን ጣዕም እናጣለን::

ተፈጥሮን በጥሞና ብንመለከት ማንም ከማንም ጋር ሲሻማ አንዱ የሌላውን ቦታ ሊወስድ ሲታገል አናይም:: ክረምት ከበጋ ጋር አይፎካከርም፤ ፀደይ ከበልግ ጋር ጦርነት አይገጥምም:: ፀሐይ ቀኗን በሙሉ ደምቃ አብርታ ማታ ላይ ስፍራዋን በክብር ለጨረቃ ትለቃለች እንጂ “ለምን ጨረቃ ቦታዬን ወሰደች?” ብላ አትወዳደርም::

ጥቁር የራሱ ውበትና ግርማ አለው:: ነጭም የራሱ ብሩህነት አለው:: አንዱ ሌላውን ሊተካ ወይም ሊያጠፋ አይሞክርም:: የሰው ልጅ ሕይወትም ልክ እንደዚሁ ነው:: እያንዳንዳችን የራሳችን የሆነ ዜማ፣ የራሳችን የሆነ ሪትም፣ እና ፈጽሞ ከማንም ጋር የማይመሳሰል ልዩ የሕይወት መንገድ አለን:: እኛ ግን አብዛኛውን ጊዜ ይህንን ረስተን የራሳችንን የሕይወት ምዕራፍ ከሌሎች ሰዎች የሕይወት ገጽ ጋር ስናወዳድር የራሳችንን ልዩ ቀለም እናበላሻለን::

በስነ-ልቦና ጥናቶች እና በኒውሮ ሳይንስ ዘርፍ የተደረጉ ዘመናዊ ምርምሮች ራስን ከሰው ጋር ማወዳደር የሚያስከትለውን አስከፊ ጉዳት በሳይንሳዊ መነጽር ያሳዩናል:: አእምሯችን በተፈጥሮው ማህበራዊ መስተጋብራችንን ለመመዘንና አካባቢያችንን ለመቃኘት ይሞክራል:: ነገር ግን ራሳችንን ከሌሎች ጋር አብዝተን ስናወዳድር፣ በተለይም ‘ከእነሱ አነስኩ፣ ወደኋላ ቀረሁ’ የሚል ስሜት ውስጥ ስንገባ በአንጎላችን ውስጥ የጭንቀት ሆርሞን የሆነው ‘ኮርቲሶል’ በከፍተኛ መጠን ይመነጫል:: ይህ ሆርሞን የውስጥ ሰላማችንን ያናጋል:: እንዲሁም የደስታ፣ የእርካታ እና የትኩረት ሆርሞኖች የሆኑትን ዶፓሚን እና ሴሮቶኒን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል:: በዚህም ምክንያት የፈጠራ አቅማችን ይዳከማል፤ ውስጣዊ ሞራላችን ይወድቃል::

እ.አ.አ በ1954 ታዋቂው የስነልቦና ባለሙያ ሊዮን ፌስቲንገር የማህበራዊ ንጽጽር ንድፈ ሀሳብ በሚለው ጥናታቸው እንዳረጋገጡት ሰዎች የራሳቸውን ዋጋና ስኬት የሚተምኑት ከሌሎች ጋር ራሳቸውን በማነጻጸር ነው:: ነገር ግን ይህ ልማድ ከልክ ሲያልፍ ሰዎችን ወደ ዝቅተኛ የራስ ግምት፣ ወደ ባዶነት ስሜት፣ የምቀኝነት መንፈስ እና ወደ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ይመራቸዋል::

አሁን ባለንበት የዲጂታል እና የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ደግሞ ነገሩ የከፋ ነው:: ሰዎች የሌላውን ሰው የተዋበ የሕይወት ገጽ እና የስኬት ጫፍ ከራሳቸው የእለት ከእለት የጀርባ ታሪክ ውጣ ውረድ ጋር እያወዳደሩ ራሳቸውን በማይገባ የሥነ-ልቦና እስር ቤት ውስጥ አስገብተው እየተሰቃዩ ይገኛሉ::

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት “ንጽጽር የደስታ ሌባ ነው” በማለት ባለን ነገር ረክተን የራሳችንን ህይወት እያጣጣምን እንዳንኖር የሚያደርገንን ትልቁን ጠላት ጠቁመዋል:: ታላቁ የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን በበኩሉ “ሁሉም ሰው አዋቂ ነው፤ ነገር ግን አንዲትን አሳ ዛፍ ላይ የመውጣት አቅሟን መዝነህ የምትፈርድባት ከሆነ ዕድሜዋን ሙሉ ራሷን እንደ ሞኝ ስትቆጥር ትኖራለች”  ብሎ ነበር:: እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ፈጽሞ የማይደገም አቅምና ተሰጥኦ እንዳለው አበክሮ ተናግሯል::

በዘመናችን ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት መጻሕፍት አንዱ በሆነው እና በካናዳዊው የስነ-ልቦና ባለሙያ ጆርዳን ፒተርሰን በተጻፈው “12ቱ የሕይወት ህጎች” በተሰኘው መጽሐፍ አራተኛው ህግ ላይ “ራስህን ትላንት ከነበርኸው ማንነትህ ጋር አወዳድር እንጂ ዛሬ ሌላ ሰው ከደረሰበት ጋር አታወዳድር” በማለት በጥብቅ ይመክራል::

ትክክለኛው ጤናማው እና እድገት የሚያመጣው ውድድር መሆን ያለበት በራስህ ውስጥ ካለው የቀድሞ ማንነትህ ጋር እንጂ ፈጽሞ ከተለየ የህይወት መነሻ፣ አስተዳደግና መስመር ከመጣ ሌላ ግለሰብ ጋር መሆን እንደሌለበት መጽሐፉ በሰፊው ያትታል::

የጦር ሜዳ ውሎን እና የሕይወት ፍልስፍናን አጣምሮ የያዘው ሮማዊው የጦር መሪ እና ፈላስፋው ንጉሥ ማርከስ ኦሬሊየስ ‘ሜዲቴሽንስ’ በተሰኘው ማስታወሻው ላይ “ወደ ራስህ ተመልከት፤ የደስታ፣ የጥንካሬ እና የሰላም ምንጭ በውስጥህ ነው ያለው:: የሌላውን ሰው አእምሮ ስላላነበብክ የምትጎዳው ነገር የለም:: ነገር ግን የራስህን ልብና መንገድ ካልተረዳህ በርግጥም ትጠፋለህ” በማለት የሰውን ኃይል ከመመዘን ይልቅ የራስን ውስጣዊ አቅም ማሳደግ ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ተናግሯል::

ሌላው ታዋቂው የቻይና የጦር ስትራቴጂስት ሰን ትዙ በ “ዘ አርት ኦፍ ዋር” መጽሐፉ ላይ “ራስህን እና ጠላትህን ካወቅህ በመቶ ጦርነቶች ውስጥ እንኳን አደጋ አይደርስብህም፤ ነገር ግን ራስህን ሳታውቅ ሌላውን ብቻ ካወቅህ ለምታገኘው እያንዳንዱ ድል አንድ ሽንፈት ይደርስብሀል” ብሏል:: እውነተኛ ጀግንነት የራስን ፍርሃትና ውስንነት ማሸነፍ እንጂ የሌላውን ኮቴ መከተል አይደለም::

ወደ መነሻችን ጥልቅ ሀሳብ ስንመለስ ሁሉም የራሱ መንገድ አለው:: አባት ልጁን ሊቀድም፤ ልጅም አባቱን ሊቀድም ይችላል:: ይህ የሕይወት ውበት ነው:: የሰው ልጅም እንደዚሁ ነው:: እያንዳንዳችን የተፈጠርነው በልዩ አላማ በተለየ የሕይወት ሰዓት እና አቅም ነው:: አንዳንዱ በሃያ ሁለት ዓመቱ ተመርቆ የሕይወቱን አቅጣጫ ለማግኘት አምስት ዓመት ይፈጅበታል:: ሌላው በሰላሳ ዓመቱ ተመርቆ ወዲያው ፈጣን የስኬት መንገድ ላይ ይወጣል:: አንዱ በሃያ አምስት ዓመቱ የድርጅት ስራ አስኪያጅ ሆኖ በሃምሳ ዓመቱ ያልፋል:: ሌላው በሃምሳ ዓመቱ ጀምሮ እስከ ሰማንያ ዓመቱ ዓለምን የሚያስደምም፣ ታሪክ የማይረሳው ታላቅ ስራ ይሰራል:: የሁሉም ጊዜ ትክክል ነው:: የሌላው ሰው ስኬት የእኛ ውድቀት አይደለም:: የእኛም መዘግየት ከእነሱ ጋር በአንድ ሩጫ ላይ ስለሆንን አይደለም:: አንዳችን ከሌላችን የተለየን ነን::

‘ትላንት ከነበርኩበት ማንነት ዛሬ ምን ያህል አደግሁ? በውስጤ ያለውን አቅምና ተሰጥኦ ምን ያህል ተጠቀምኩበት? ዛሬን የተሻለ ሰው ሆኜ እንዴት ልዋል?’ በሚለው ራስን የማሳደግ ጥያቄ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው:: ሁሉም አበባ የሚፈካበት የራሱ የተፈጥሮ ወቅት አለው:: እኛም የሁላችን ጊዜ አለን::

ታዲያ ከዚህ አድካሚ የውድድር እና የንጽጽር ስቃይ እንዴት እንውጣ? የመጀመሪያው  የራስን የስኬት ትርጉም በግልጽ ማስቀመጥ እና መቀበል ያስፈልጋል:: የሌላው ሰው የስኬት መለኪያ ለእኛ ላይሰራ ይችላል፤ የእነሱ ጉዳይ  የእኔ ጉጉት ላይሆን ይችላል:: ሁለተኛው የትኩረት አቅጣጫን ማስተካከል ነው:: ትኩረታችንን “እነሱ ምን አገኙ?” ከሚለው አጥፊ ጥያቄ ወደ “እኔ ዛሬ ምን አደግሁ?” ወደሚለው ገንቢ ጥያቄ ማዞር፤ ውድድራችን ከቀድሞው ማንነታችን ጋር ብቻ መሆን አለበት::

ሶስተኛው ያለንን የማመስገን ልማድ ማዳበር ነው:: ያለንን ነገር ማድነቅና ማክበር ስንጀምር የሌላውን መመኘት እናቆማለን:: አእምሯችንም ከ’ጭንቀት’ ርቆ በ’በደስታ’ ይሞላል:: አራተኛው የየራሳችንን የጊዜ ሰሌዳ ማክበር ነው:: አንዳንዱ በሃያ ዓመቱ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል፣ ሌላው በሃምሳ ዓመቱ ዓለምን የሚያስደምም ስራ ይሰራል፤ የሁለቱም ጊዜ ትክክል ነው:: መዘግየት ውድቀት አይደለም::

ስለዚህ የራስህን መንገድ መውደድ፣ ማክበር፣ ማጽዳት እንጂ ከሌላ ሰው ጎዳና ጋር  ማወዳደር የሚጠቅም አይደለም:: ከውድድር ስቃይ ነጻ ወጥተን በራሳችን ልዩ ቀለም ደምቀን በራሳችን የሕይወት መንገድ ተጉዘን ከማንም ጋር ሳንነጻጸር የራሳችንን ድንቅ እና ማንም ሊደግመው የማይችለውን ታሪክ እንጻፍ::

(አቢብ አለሜ)

በኲር የመጋቢት 14  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here