ሐይቁ የሚገኝበት አካባቢ ዘወትር ልምላሜን የተላበሰና ውብ በመሆኑ በርካቶች የእረፍት ቀናቶቻቸውን ለማሳለፍ ምርጫቸው ነበር:: ልምላሜ የተላበሰው የሐይቁ ዙሪያ ገብ በሥራ የደከመ አዕምሮውን አዝናንቶ፣ ውብ የሆነውን ተፈጥሯዊ እና የሰው ሠራሽ ሐይቁን ተመልክቶ፣ በተንጣለለው አካባቢ የለማውን ሰብል ቃኝቶ፣ ንፁህ አየር አግኝቶ የሚመለሱበት ምቹ ሥፍራም ነበር – ገራይ ሐይቅ::
በምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ፍኖተ ሰላም አቅራቢያ የሚገኘው የገራይ ሰው ሠራሽ ሐይቅ (ግድብ) በተለይም በየዓመቱ ሰኔ 30 የትምህርት መጠናቀቅን (መዘጋትን) ተከትሎ ተማሪዎቹ ወደ ቦታው ተጉዘው የሚዝናኑበት፣ ፎቶ በመነሳት ማስታወሻ የሚይዙበት እንዲሁም ጋብቻ ለሚፈፅሙ ሙሽሮች ለመዝናናት የሚመርጡት ማራኪ ስፍራም እንደነበር በርካቶች ምስክር ናቸው::
ገራይ ሐይቅ ከመዝናኛነቱ ባለፈ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው:: በሐይቁ ውስጥ የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎች ስለሚገኙ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሌላ የገቢ ምንጭም ነው:: በተለይም ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አርሶ አደሩ በስፋት እየተጠቀመ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ምርቱን ለገበያ እንዲያቀርብ ጉልህ ሚና ይጫወታል:: ለቱሪዝሙ ዕድገትም ሐይቁ ሚናው የሚናቅ አይደለም::
ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ የሚሰጠው ይህ ሰው ሠራሽ ሐይቅ አሁን ላይ ግን በመጤ አረም ስርጭት እና በደለል መሞላት ምክንያት ሕልውናው አደጋ ላይ መውደቁን በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች እና በሐይቁ ላይ ሕይወታቸውን የመሰረቱ ግለሰቦች ለበኵር ጋዜጣ ሐሳባቸውን በስልክ አጋርተውናል::
የሐይቁን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ አርሶ አደሮች እንዳብራሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሐይቁ ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው አረም የውኃውን መጠን ከመቀነሱም በላይ ብዝኃ ሕይወቱን ክፉኛ እየጎዳው መሆኑን ነው:: ይህ ሁኔታም በሐይቁ ላይ ሕይዎታቸዉን መሰረት ያደረጉ የአካባቢው ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሯቸዉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሯል::
በጉዳዩ ዙሪያ በኵር ጋዜጣ በስልክ ያነጋገራቸው በአርባዕቱ እንስሳ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ሀብታሙ ተሰማ የገራይ ሐይቅ አሁን ያለበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል:: ሐይቁ ቀድሞ በነበረው ተፈጥሯዊ ውበት እና ይዞታ ለአካባቢው ህብረተሰብ የሕይወት መሰረት ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ተገቢው እንክብካቤ ባለመደረጉ እና በአረም በመወረሩ ምክንያት ገጽታው እየተበላሸ እና ሐይቁም መጠኑ እየቀነሰ እንዲሁም ወደ መሬትነት እየተቀየረ መምጣቱን ተናግረዋል::
እንደ አቶ ሀብታሙ ማብራሪያ እርሳቸዉን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች የገራይ ሐይቅን በመጠቀም በበጋ መስኖ ስንዴ፣ ገብስ፣ ነጭ እና ቀይ ሽንኩርት፣ ሸንኮራ፣ ቃሪያ፣ ቲማቲም፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ቡና፣ ድንች እና ሌሎች የአትክልት እና ፍራፍሬ ሰብሎችን በስፋት እያመረቱ ይገኛሉ:: ይህም ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እንደሆናቸው ያስረዳሉ:: ሰው ሠራሽ ሐይቁ ከተገደበ ጊዜ አንስቶ ሕይወታቸው በሐይቁ ላይ እንደተመሰረተም አርሶ አደር ሀብታሙ አረጋግጠዋል::
የውኃ አካሉ በተለይም በአካባቢው ለሚከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች፣ ለእንስሳት የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ለሌሎችም የአካባቢው ሥነ-ምህዳር ሚዛን መጠበቅ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው:: በመሆኑም ይህ አረም በአስቸኳይ ካልተወገደ እና ሐይቁ መታደግ ካልተቻለ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እና የምርት መቀነስ ሊዳርግ እንደሚችል አርሶ አደሮች ስጋት ተጋርጦባቸዋል::
ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው የአካባቢው አርሶ አደር አቶ መስፍን ተሰማ ናቸው:: አርሶ አደሩ ሰው ሠራሽ ሐይቁን ተጠቅመው የግብርና ሥራቸውን ማከናወን ከጀመሩ 30 ዓመታትን አስቆጥረዋል:: ከዚህ በፊት የነበረዉ የሐይቁ ውኃ በቂ በመሆኑ የመስኖ ሥራቸውን ሲያሳልጥላቸው መቆየቱን አርሶ አደሩ አስታውሰዋል:: “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የውኃ መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ እና እየደረቀ፤ በደለል እየተሞላ እና በአረም እየተዋጠ ወደ መሬትነት እየተቀየረ ነው:: በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል:: ዘንድሮ የዘራሁት ድንች የውኃ እጥረት አጋጥሞታል” በማለት አብነት ጠቅሰው ስጋታቸውን ተናግረዋል::
የአካባቢው ማህበረሰብ ሐይቁን ለማትረፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው:: በየአብያተ ክርስቲያናቱ ቅስቀሳ በማድረግ እንዲሁም ከሌሎች አጎራባች ቀበሌዎች ጭምር ሰዎችን በማስተባበር በየሳምንቱ ረዕቡ የጉልበት ሥራ በዘመቻ አረሙን ለማስወገድ እየታገሉ እንደሚገኙም አቶ መስፍን ጠቁመዋል:: እርሳቸው እና የአካባቢው ነዋሪ ሐይቁን ከደረሰበት ችግር ለመከላከል የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት አቶ መስፍን መንግሥትም ሆነ የሚመለከተው አካል ሐይቁን ለመታደግ የጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል::
በተመሳሳይ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የገራይ ሐይቅ አካባቢ ነዋሪው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በግል እና በማኅበር በመደራጀት በዓሳ ማስገር ሥራ ተሠማርተው ሲሠሩ ቆይተዋል:: በዚህም ለፍኖተ ሰላም፣ ለጅጋ፣ ለደንበጫ እና ለቡሬ ከተሞች ዓሳ በማቅረብ የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር ነግረውናል:: ስለሆነም ሐይቁ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ጉል ሚና እንደነበረው አስረድተዋል::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሐይቁ ደኅንነት በተገቢው መንገድ ባለመጠበቁ በዓሳ ሃብት ልማቱ ላይ ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን ተናግሯል:: ሐይቁን የመንከባከብ ተግባራት በመቀዛቀዙ ከሐይቁ የሚገኙ ጥቅሞች እየቀነሱ መሆኑን ያስረዳሉ:: ስለሆነም አካባቢውን ከደለል መከላከል፣ አርሶ አደሩ በሐይቁ ዙሪያ ቆሻሻ ከመጣል መቆጠብ እና ለሰብል ልማት የሚጠቀምባቸውን መርዛማ ኬሚካሎች ወደ ሐይቁ እንዳይገቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ሐሳባቸውን ሰጥተዋል::
የገራይ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ከተጋረጠበት ችግር እንዲወጣ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በተመለከተ የጃቢ ጠህናን ወረዳ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊን በስልክ አነጋግረናል:: የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ታደሰ እንደገለፁት ሐይቁ በአካባቢው ለሚገኙ ከአምስት ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እያደረገ ነው:: በተለይም የቡና ልማት እንዲስፋፋ በመደረጉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል:: ሐይቁ በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶችም ዓሳ በማስገር ተጠቃሚ የሚያደርግ ጭምር እንደሆነም ነው ያስገነዘቡት::
ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሐይቁ ችግር እንደተጋረጠበት አረጋግጠዋል:: ሐይቁ በተለምዶ ‘’አለምሲሳ’’ በተሰኘ አረም መወረሩን ነው የጽሕፈት ቤት ኃላፊው የተናገሩት:: በየጊዜው ከአካባቢው ወደ ሐይቁ በሚመጣ የጎርፍ ደለል በመሞላቱ እና ውኃው እየሰረገ በመሆኑ የውኃ መጠኑ እየቀነሰ መምጣቱንም አስረድተዋል::
የሐይቁን ደኅንነት በሚፈለገው ልክ ለማስጠበቅ እንቅፋት ሆኖ የቆየው እንደ ክልል ከሐምሌ ወር መጨረሻ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው ግጭት መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል:: አሁን ላይ የሐይቁን ደኅንነት ለማስጠበቅ ወረዳው የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም በዘላቂነት ለመፍታት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል::
በአሁኑ ወቅት ባለሙያ በመላክ የችግሩ ስፋት ምን ያህል እንደሆነ የአካባቢ ተፅዕኖ ምርመራ እየተደረገ ስለመሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል:: ዞኑም የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግ የጋራ መግባባት መደረሱን ገልፀዋል::
የፍኖተ ሰላም እና አካባቢው ወጣቶች፣ ሴቶች እና አዛውንቶች በሐይቁ ላይ የተከሰተውን አረም በማስወገድ በኩል እየሠሩት ያለውን ሥራም ኃላፊው አመስግነዋል፤ አድንቀዋልም:: ማህበረሰቡ በባለቤትነት ስሜት ሐይቁን ለመታደግ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል::
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ሐይቁ ከተጋረጠበት የመጥፋት አደጋ ወደ ነበረበት ለመመለስ በጊዜያዊነት የተስፋፋውን አረም በሰው ጉልበት እና የተበላሹ ጀልባዎችን አስጠግኖ የማስወገድ ሥራ እየተከናወነ ነው:: በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት አደረጃጀት ተፈጥሮ እየተሠራ ሲሆን የጎርፍ እና የደለል ክምችቱ ወደ ሐይቁ እንዳይገባ ማድረግ፣ በግድቡ ዙሪያ ለእርሻ አገልግሎት የሚውለውን መሬት እስከ ጥግ ድረስ እንዳይታረሱ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ መሥራት፣ በአካባቢው ያሉ ደኖች እንዳይጨፈጨፉ ማድረግ፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራን በሰፊው ማከናወን እና የተለያዩ የዕፅዋት አይነቶችን በዙሪያው መትከል እና መሰል ተግባራት እየተከናወኑ ካሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው::
ከመሬት አሥተዳደር፣ ከግብርና መምሪያ፣ ከእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ጽ/ቤት እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልም አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል::
የአካባቢው ነዋሪዎች በባለቤትነት ስሜት ያለማንም ቀስቃሽ እና ጉትጎታ ሐይቁ የሚሰጠውን ጥቅም ተረድቶ መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ ማልማት እና ለሐይቁ ስጋት የሆኑ ተግባራትን ከመፈፀም መቆጠብ፣ በሐይቁ ላይ የሚደረጉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን መከላከል እንዲሁም ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት እንደሚገባ ኃላፊው ጥብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል::
መረጃ
የገራይ ሰው ሠራሽ ሐይቅ በ1971 ዓ.ም ለመስኖ ሥራ በሚል የተገደበ እንደሆነ ከወረዳው አካባቢ እና ደን ጥበቃ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ፍኖተ ሰላም ከተማ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው አስፋልት መንገድ ላይ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል እንደተጓዝን ከመንገዱ ወደ ደቡብ አቅጣጫ 500 ሜትር ርቀት አካባቢ ይገኛል።
ሐይቁ እስከ ስድስት ሄክታር አካባቢ ስፋት እና 12 ሜትር ገደማ ጥልቀት ያለው ነው።
ከስምንት መቶ ሔክታር በላይ የእርሻ እና የልማት ቦታዎችን እንደሚሸፍንም መረጃዎች ያሳያሉ።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


