በዳመና ላይ የተንጠለጠለዉ  ከተማ

0
94
Early morning in wonderful Machu Picchu

በደቡብ አሜሪካ የፔሩ ተራሮች ሰንሰለት መካከል በታላቁ የአንዴስ ተራራ ጫፍ ላይ አንድ እጅግ አስገራሚና አስደናቂ ከተማ ይገኛል። ይህ ከተማ ማቹ ፒቹ (Machu Picchu) ይባላል። ከባህር ጠለል በላይ በ2 ሺህ 430 ሜትር ከፍታ ላይ በደመና የተከበበውና በአረንጓዴ ጫካዎች የተሸፈነው ይህ ስፍራ የኢንካ ስልጣኔ የደረሰበትን ከፍተኛ የምህንድስና፣ የስነ-ፈለክና የኪነ-ጥበብ ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ማቹ ፒቹ ተራ ፍርስራሽ አይደለም፤ የሰው ልጅ የማይቻል የሚመስለውን ተፈጥሮ እንዴት ተቋቁሞ ወደር የማይገኝለት ጥበብ መፍጠር እንደሚችል ያሳዬበት የታሪክ ምስክርም ነው።

የኢንካ ኢምፓየር በ15ኛው ክፍለ ዘመን የደቡብ አሜሪካን ምዕራባዊ ክፍል የገዛ ግዙፍ መንግሥት ነበር። ይህ ግዛት ከኮሎምቢያ እስከ ቺሊ የተዘረጋ ነው። በወቅቱ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ የተደራጁና ባለጸጋ ስልጣኔዎች አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል። ማቹ ፒቹ የተገነባው እ.ኤ.አ. በ1450 ዓ.ም. አካባቢ በታላቁ ንጉሥ ፓቻኩቲ (Pachacuti Inca Yupanqui) ዘመን እንደሆነ የታሪክ ተመራማሪዎች ይስማማሉ።

ከተማው ለምን ተገነባ? የሚለው ጥያቄ ለብዙ ዘመናት አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንዶች ለንጉሳዊ ቤተሰቦች የበጋ መዝናኛ  እና መኖሪያ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ እጅግ ቅዱስ የሆነ የሃይማኖት ማዕከልና የፀሐይ አምልኮ ስፍራ እንደሆነ በመጥቀስ ይከራከራሉ። ለምንም ትገንባ ለምን የተገነባበት ስትራቴጂያዊ ቦታና ጥበብ ግን ኢንካዎች ለተፈጥሮና ለሃይማኖታቸው የነበራቸውን ጥልቅ ክብር ያሳያል።

ያለምንም ማጣበቂያ የቆመ ተዓምር

የማቹ ፒቹ እጅግ አስገራሚው ገጽታ ህንፃዎቹ የተገነቡበት መንገድ ነው። ኢንካዎች “አሽላር” (Ashlar) የተባለ ልዩ የድንጋይ አሰራር ጥበብ ይጠቀሙ ነበር። ይህ ዘዴ ግዙፍ የግራናይት ድንጋዮችን ያለምንም ሲሚንቶ፣ ጭቃ ወይም ማጣበቂያ አንዱን ከሌላው ጋር በትክክል አገጣጥሞ የመስራት ጥበብ ነው።

የድንጋዮቹ አገጣጠም በጣም ጥንቁቅ ከመሆኑ የተነሳ በሁለት ድንጋዮች መካከል ቀጭን ቢላዋ ወይም ወረቀት ማስገባት አይቻልም። ይህ ጥበብ ውበትን ከመስጠት ባለፈ ትልቅ ሳይንሳዊ ጥቅም አለው። ፔሩ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚከሰትባት ሀገር በመሆኗ እነዚህ ድንጋዮች በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት በቦታቸው ላይ “ይጨፍራሉ” (ይንቀጠቀጣሉ) እንጂ አይፈራርሱም። ንዝረቱ ሲቆም ድንጋዮቹ ወደ ነበሩበት ትክክለኛ ቦታ ይመለሳሉ። ይህ መሃንዲሶችን እስከ ዛሬ ድረስ የሚያስደንቅ የጥበብ ውጤት ነው።

የከተማው መዋቅርና የስነ-ፈለክ እውቀት

ማቹ ፒቹ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለ ነው፤የእርሻ ዞንና የከተማ ዞን። የእርሻ ዞኑ በተራራው ዳገት ላይ የተሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ እርከኖችን (Terraces) ይይዛል። እነዚህ እርከኖች ለምግብ ምርት ብቻ ሳይሆን ተራራው በዝናብ ውሃ ተሸርሽሮ እንዳይናድ እንደ ግድብ ሆነው ያገለግላሉ። ይህ ኢንካዎች ለአፈር ጥበቃና ለግብርና የነበራቸውን ከፍተኛ እውቀት ያሳያል።

በከተማው ዞን ውስጥ ደግሞ አስደናቂ ቤተ-መቅደሶች፣ ቤተ-መንግስታት እና የመኖሪያ ቤቶች ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል “ኢንቲዋታና” (Intihuatana) የተባለው ድንጋይ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። “ኢንቲዋታና” ማለት “ፀሐይን የማሰሪያ ምሰሶ” ማለት ነው። ኢንካዎች ይህንን ድንጋይ ተጠቅመው ወቅቶችን ይለኩ ነበር። በታህሳስ 21 (የክረምት ወቅት መጀመሪያ) ፀሐይ ቀጥታ በድንጋዩ ላይ ስታርፍ ምንም ጥላ አይኖረውም። ይህ ጥልቅ የስነ-ፈለክ (Astronomy) እውቀት ማቹ ፒቹ ከሰማያዊ አካላት ጋር ያላትን ግንኙነት ያሳያል።

ሌላው ድንቅ ስራ “የፀሐይ ቤተ-መቅደስ” (Temple of the Sun) ነው። ይህ ህንፃ ከፊል ክብ ቅርጽ ያለው ሲሆን በመስኮቶቹ በኩል የሚገባው የፀሐይ ብርሃን በዓመቱ ውስጥ የሚከሰቱትን ልዩ የፀሐይ ቀናት በትክክል እንዲያመለክት ተደርጎ ተቀርጿል። ኢንካዎች ፀሐይን እንደ አምላክ ያመልኩ ስለነበር፣ ከተማውን ለፀሐይ ክብር ሲሉ እጅግ ውብ አድርገው ሰርተውታል።

ምስጢራዊው መጥፋትና ዳግም መገኘት

ማቹ ፒቹ የተገነባው በ1450 ዓ.ም. አካባቢ ቢሆንም፣ ከ100 ዓመታት በኋላ በ1550 ዓ.ም. አካባቢ ነዋሪዎቹ በድንገት ጥለውት ወጥተዋል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስከ ዛሬ በውል አይታወቅም። አንዳንዶች በስፔን ወራሪዎች የመጣ የፈንጣጣ በሽታ ህዝቡን ጨርሶታል ሲሉ ሌሎች ደግሞ በውስጥ ጦርነት ምክንያት እንደሆነ ይገምታሉ።

ስፔናውያን ደቡብ አሜሪካን በወረሩበትና የኢንካዎችን ስልጣኔ ባወደሙበት ወቅት፣ ብዙ ከተሞችንና የወርቅ ቤተ-መቅደሶችን አፍርሰዋል። ነገር ግን ማቹ ፒቹ በተራራ ጫፍ ላይ የተደበቀና ጥቅጥቅ ባለ ጫካ የተከበበ ከተማ በመሆኑ ወራሪዎቹ ሊያገኙት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ከተማው ሳይፈርስና ሳይበላሽ ለዘመናት በምስጢር ቆይቷል።

እ.ኤ.አ. ሐምሌ 24 ቀን 1911 ዓ.ም. አሜሪካዊው የታሪክ ተመራማሪ ሂራም ቢንግሃም፣ አካባቢው በሚኖሩ ገበሬዎችና በአንድ ትንሽ ልጅ እርዳታ ይህንን “የጠፋ ከተማ” ዳግም ለዓለም አሳወቀ። ቢንግሃም መጀመሪያ ላይ ያገኘው ቦታ “ቪልካባምባ” የተባለው የመጨረሻው የኢንካዎች መጠጊያ መስሎት ነበር፤ ነገር ግን በኋላ ላይ የተገኙ መረጃዎች ማቹ ፒቹ ከዚያም በላይ ታላቅ ስፍራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ዛሬ ማቹ ፒቹ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚስብ የቱሪስት መዳረሻ ነው። ወደዚህ ስፍራ የሚደረግ ጉዞ አካላዊ ጥንካሬን ብቻ ሳይሆን፣ መንፈሳዊ እርካታንም ይሰጣል። ከተራራው ጫፍ ላይ ቆመው ወደ ታች ሲመለከቱ፣ ከታች የሚፈሰው የኡሩባምባ ወንዝ ድምፅ እና በተራራው ላይ የሚንሳፈፉት ደመናዎች ለሰው ልጅ ታላቅነት ምስክር ናቸው።

ማቹ ፒቹ የድንጋይ ክምር አይደለም፤  የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ልህቀት ለተፈጥሮ ያለው ፍቅርና የማይበገረው የኢንካዎች መንፈስ ውጤት ነው። የጥንቶቹ ኢንካዎች ያለምንም ዘመናዊ ማሽን፣ ያለምንም ተሽከርካሪ እና ያለምንም የብረት መሣሪያ የገነቡት ይህ ከተማ፣ ለዘመናዊው ዓለም ትልቅ የትህትና ትምህርት ይሰጣል። ተፈጥሮን ሳያጠፉ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ህያው ምስክር ነው።

አጭር እውነታ

ስለ ፔሩ አጫጭር እውነታዎች፦

  • ፔሩ በደቡብ አሜሪካ የሚገኝ አገር ሲሆን ዋና ከተማዋ ሊማ ናት።
  • ታዋቂው የጥንታዊ ሥልጣኔ ኢንካ እዚህ ነበር የተመሰረተው።
  • የዓለም ዝነኛ ታሪካዊ ቦታ ማቹ ፒቹ በፔሩ ይገኛል።
  • ፔሩ የአማዞን ደን ክፍል ያላት ስለሆነ ብዙ የተፈጥሮ ሀብት አላት።
  • የአማዞን ወንዝ መነሻ አካባቢዎች በፔሩ ውስጥ ይገኛሉ።
  • ዋና ቋንቋ ስፓኒሽ ነው፣ ነገር ግን ኩችዋ (Quechua) እና አይማራ (Aymara) ደግሞ ይነገራሉ።
  • ፔሩ በምግብዋ ዝነኛ ናት፤ በተለይ ሴቪቼ በዓለም የታወቀ ነው።
  • የአንዲስ ተራሮች (Andes Mountains) በፔሩ ውስጥ ይሄዳሉ።
  • ፔሩ ከብዙ የተፈጥሮ እና ታሪካዊ መስህቦች የተነሳ ታላቅ የቱሪዝም መዳረሻ ናት።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የመጋቢት  14  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here