የካፍ እና የሴኔጋል ውዝግብ መጨረሻዉ ምን ይሆን?

0
72

ዓይንዎን ከድነው ይህንን ትዕይንት ለአፍታ በምናብዎ እስኪ ይሳሉት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአህጉሪቱ ትልቁን የአፍሪካ ዋንጫ አንስቷል:: ሚሊዮኖችም አደባባይ ወጥተው ጨፍረዋል፤ የደስታ እንባም ተራጭተዋል፤ ጀግኖቻቸውንም በክብር ተቀብለዋል:: ይህ አስደናቂ ድል ከተፈጸመ ሁለት ወራት አልፎታል:: አንድ ቀን በማለዳ ከእንቅልፍዎ ሲነቁ ግን ያን ለሳምንታት ያከበሩትን ዋንጫ ተነጥቃችኋል የሚል ዜና ቢሰሙ ምን ይላሉ? ዜናው ከበረዶ የቀዘቀዘ፣ የልብ ምትን ከፍ ዝቅ የሚያደርግ፣ ህልምን ወደ ቅዠት የሚቀይር አስደንጋጭ መርዶ እንደሚሆንብዎት አንጠራጠርም:: ሴኔጋሎችን ያጋጠማቸው ይኸው አሳዛኝ ክስተት ነው::

መጋቢት ስምንት ቀን 2018 ዓ.ም ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫን አነሳች:: አሳዛኙ ዜና እስከተሰማበት ዕለት ድረስ የሴኔጋል ዳካር  ጎዳናዎች ገና ከጭፈራ አልበረዱም፤ የአፍሪካን ክብር በጀግንነት ለተቀዳጁት የቴራንጋ አንበሶች የተዘፈነው ጉሮ ወሸባ አየር ላይ ካስተጋባ ፣ርችቶች በራባት ስታዲየም ሰማይ ላይ ከተበተኑ ገና ሁለት ወራት እንኳን አልሞላውም:: የካፍ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በካይሮ ባደረገው ዝግ ስብሰባ፣ የቴራንጋ አንበሶች በራባት ስታዲየም ሞሮኮን አንድ ለባዶ አሸንፈው ያገኙትን የ2025ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ድል በአንድ መግለጫ ሰርዞታል:: በምትኩም ሴኔጋል የካፍን ጥብቅ የዲስፕሊን ሕግጋት ጥሳለች በሚል አዘጋጇን ሞሮኮ ሻምፒዮን አድርጓል:: ካፍ ለሳዲዮ ማኔ አበርክቶለት የነበረውን የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትንም እንዲመልስ ትእዛዝ አስተላልፏል:: የአፍሪካ ዋንጫው ምርጥ ተጫዋችነትን ከሳዲዮ ማኔ ነጥቆ ለሞሮኳዊው ብራሂም ዲያዝ መስጠቱን አሳውቋል::

ይህ የካፍ ውሳኔ መላውን የእግር ኳስ ዓለም ያነጋገረ እና አጀብ ያሰኘ በስፖርቱ ታሪክ አቻ የማይገኝለት ያልተጠበቀ ክስተት መሆኑን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አስነብቧል:: ወደ ኋላ መለስ ብለን የዓለምን እና የአፍሪካን የእግር ኳስ ታሪክ ማህደር ገልጠን ስንመረምር እንደዚህ አይነት ውሳኔ ያልተለመደ እንደሆነ መረጃዎች ያሳዩናል::

በውድድር መሃል ቡድኖች በዲስፕሊን ግድፈት ከውድድር ሲባረሩ ወይም በማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ አስተዳደራዊ ቅጣት ሲጣልባቸው  ማየት እንግዳ አይደለም:: ለአብነት  ሴኔጋል ለ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እ.አ.አ በ2012 ከኮትዲቫር ጋር ስትጫወት ደጋፊዎቿ  በፈጠሩት ሁከት ጨዋታው ተቋርጦ ከውድድሩ መሰረዟ አይዘነጋም:: ይሁን እንጂ አንድ ብሔራዊ ቡድን የፍጻሜውን ጨዋታ እስከመጨረሻው አጠናቆ፣ ሜዳሊያ በአንገቱ  አጥልቆ ወደ  ሀገሩ የወሰደውን ዋንጫ ሲነጠቅ በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም::

ይህ የካፍ ወሳኔ በእግር ኳሱ ዓለም አዲስ ገጽ የከፈተ፣ ታሪካዊ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠ እና ወደፊት በስፖርቱ በጉልህ የሚሰፈር የመጀመሪያው ልዩ ክስተት ነው:: ሜዳ ላይ የተሸነፈ ቡድን በካፍ የቢሮ ጠረጴዛዎች ላይ አሸናፊ ሲሆን ማየት የስፖርቱን ተፈጥሯዊነት  በእጅጉ ይፈታተናል::

ታዲያ የዚህ ሁሉ ውዝግብ እና ታሪካዊ ውሳኔ መነሻው ምንድነው?  ወደ ራባት ስታዲየም መለስ ብለን ስናስታውስ በፍጻሜው ጨዋታ ማብቂያ ላይ የተፈጠረው የጥቂት ደቂቃዎች  ድራማዊ ክስተት ነው:: ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ደቂቃ ሲቀሩት የሞሮኮው አጥቂ ብራሂም ዲያዝ በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በመውደቁ ለሞሮኮ የፍጹም ቅጣት ምት ውሳኔ ተሰጠ:: ይህ ውሳኔ የሴኔጋልን ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ ፓፔ ቲያውን እጅግ አስቆጣ:: ተጫዋቾቻቸው ተበድለናል፤ ፍትሕ ተጓድሎብናል በማለት ሜዳውን ለቀው ሲወጡ ተመልክተናል:: ከአምበሉ ሳዲዮ ማኔ በስተቀር ሙሉው የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል፤  ጨዋታውም ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ለመቋረጥ ተገዷል::

ምንም እንኳን ድጋሚ ወደ ሜዳ ገብተው ጨዋታውን አሸንፈው ዋንጫውን ቢያነሱም  ጨዋታውን አቋርጠው ከሜዳ መውጣታቸው ከሁለት ወራት በኋላ ዋንጫውን እንዲነጠቁ ምክንያት ሆኖባቸዋል:: በአፍሪካ ዋንጫ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 82 እና 84 መሠረት “ያለ ዳኛ ፈቃድ ሜዳን ለቆ መውጣት” የሚለው የካፍ ሕግ ሴኔጋላውያንን ዋንጫውን አሳጥቷቸዋል:: ካፍም ከሁለት ወራት በኋላ የሞሮኮን ይግባኝ ተቀብሎ  “የትኛውም ቡድን ጨዋታውን በራሱ ፈቃድ ካቋረጠ በፎርፌ ሦስት ለባዶ  ይሸነፋል” የሚለውን ከባድ የሕግ መዶሻ አሳርፎባቸዋል::

የሜዳ ላይ ውጤትን ከሁለት ወራት በኋላ በቢሮ ውሳኔ መቀልበስ ለአፍሪካ እግር ኳስ ገጽታ ፈጽሞ የማይመጥን እና የውድድሩን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት በመሆኑ እየተተቸ ይገኛል:: የዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ  ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖን ጨምሮ አንዳንድ ከፍተኛ የስፖርት መሪዎች ተጫዋቾቹ የዳኛን ውሳኔ በመቃወም ሜዳ ጥለው መውጣታቸውን ተቀባይነት የሌለው እና ሊወገዝ የሚገባ ፀረ ስፖርታዊ ድርጊት በማለት የካፍን ውሳኔ ደግፈዋል:: የስፖርቱ ቤተሰብ ግን ሜዳ ላይ የተጠናቀቀን ጨዋታ በጠረጴዛ ዙሪያ መቀልበስ ኢ ፍትሐዊ ነው በሚል ስሜቱን እያንጸባረቀ ይገኛል::

የሴኔጋል መንግሥት የካፍን ውሳኔ ሕገ ወጥ፣ ኢ ፍትሃዊ እና አሳፋሪ ነው ሲል ኮንኖታል:: ይህንን አወዛጋቢ ውሳኔ በመቃወምም ጉዳዩን በቀጥታ በስዊዘርላንድ ለሚገኘው ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (CAS) ወስዶታል:: የዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (CAS) በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) እና በሰኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ሰኔጋል የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮንነቷን ለጊዜው ይዛ እንድትቀጥል ትዕዛዝ ማስተላለፉን ዘ ጋርዲያን አስነብቧል:: ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ሰኔጋል ያቀረበችውን ይግባኝ መነሻ በማድረግ እንደሆነ መረጃው ጠቁሟል::

የካፍ ውሳኔ የብሔራዊ ቡድኑን ተጨዋቾችም አስቆጥቷል:: የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስቂኝ ቀልድ በሚል ተሳልቀውበታል:: የብሔራዊ ቡድኑ ተከላካይ የሆነው ሙሳ ኒያካቴ የዋንጫውን ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ በማጋራት “መጥታችሁ ውሰዱት፤ አብደዋል!” የሚል ስላቅ የተቀላቀለበት ጽሁፍ አስነብቧል::

ካፍ ለሰሜን አፍሪካ አረብ ሀገራት በተለይም ለሞሮኮ ያደላል የሚለው ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ዘንድ ሲብላላ የቆየው ጥርጣሬ ነው:: አሁን በይፋ ወደ አደባባይ ወጥቶ አህጉራዊ መቃቃርን መፍጠሩን መረጃው ያስነብባል:: እናም ውሳኔ በአህጉሪቱ ላይ የፖለቲካ እና የዘር ክፍፍልን እንዳያመጣ በእጅጉ ያስፈራል ሲል ዘ ጋርዲያን አስነብቧል::

የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሕግ ባለሙያዎች የካፍን እርምጃ አወድሰዋል::  የእነዚህ አካላት ዋና መከራከሪያ “ማንም ከስፖርቱ ሕግ በላይ ሊሆን አይችልም” የሚል ነው:: ተጫዋቾች በዳኛ ውሳኔ ባልተስማሙ ቁጥር ሜዳ ጥለው የሚወጡ ከሆነ ይህ ድርጊት ወደፊት ዳኞችን ለማስፈራራት እና በውሳኔያቸው ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና ለመፍጠር ያገለግላል ይላሉ፤ የካፍ ደጋፊዎች:: ዋና የመሀል ዳኛው ጨዋታውን በድጋሚ ለማስጀመር የወሰኑት በስታዲየም ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን የጸጥታ ችግር፣ የደጋፊዎች ሁከት እና የስታዲየም ብጥብጥን በመፍራት ሰብዓዊ እልቂትን ለማዳን እንጂ ጨዋታው በሕጉ መሰረት ሜዳ ጥለው በወጡበት ቅጽበት ተጠናቆ  እንደነበር የካፍን ውሳኔ የሚደግፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል::

የሕግ ፍልሚያው በዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (CAS) ለወራት፣ ምናልባትም ለዓመታት ሊጓተት ይችላል ተብሏል:: የዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (CAS) የመጨረሻ ብያኔ ምንም ይሁን ምን ይህ ክስተት ደረቅ ሕግን የማስከበር እና የሜዳ ላይ ስፖርታዊ ፍትህን የማስጠበቅ ሚዛን ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ በማሳየት በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የማይፋቅ ጠባሳ ጥሎ ማለፉ አይቀርም::

ይህን ያልተለመደ የካፍ ውሳኔ ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት ወደ ኋላ በመመለስ የቆዩ የታሪክ ማህደሮችን መፈተሽ እና የይገባኛል ጥያቄዎችን ማንሳት እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፤ ይህም እግር ኳስን ከስፖርታዊ ውድድርነት ይልቅ ወደ ሕጋዊ ንትርክ እንዳያወርደው ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል::

እ.አ.አ በ1976 ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ሞሮኮ ከጊኒ ጋር በነበራት ወሳኝ ጨዋታ ላይ በተመሳሳይ ሞሮኮ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሜዳ ጥላ ወጥታ ነበር:: ያኔ ሞሮኮ ያነሳችው ዋንጫ ተነጥቆ ለኛ ሊሰጠን ይገባል የሚል የጊኒ ደጋፊዎች ድምጽ በስፋት እየተስተጋባ ነው:: ምንም እንኳን ይህ የጊኒ ጥያቄ በፌዴሬሽኑ በኩል እውቅና ያልተሰጠው ቢሆንም የካፍ የቅርብ ጊዜ እርምጃ ምን ያህል የስፖርቱን ዓለም ወደማያልቅ አዙሪት ሊያስገባው እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ነው::

ለምሳሌ እንግሊዝ እ.አ.አ በ1986ቱ የዓለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ዲያጎ ማራዶና በታዋቂዋ “የእግዚአብሔር እጅ” (Hand of God) ማጭበርበር ያስቆጠራት ግብ ውጤት እንዲቀለበስ እና ፍትሕ እንዲሰጣት ልትጠይቅ ትችላለች:: በተመሳሳይ ጀርመንም በ1966ቱ የዓለም ዋንጫ እንግሊዝ ያስቆጠረችው ግብ ኳስ መስመሩን አላለፈችም የሚል ውዝግብ ያስነሳል:: አየርላንድ በ2010 እ.አ.አ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በቲዬሪ ኦንሪ የእጅ ኳስ ምክንያት ከውድድር መውጣቷን በማንሳት ጥያቄ ልታቀርብ ትችላለች:: ካፍ አሁን ላይ እየሄደበት ያለው መንገድ ስፖርቱን የጦርነት አውድማ እንዳያደርገው ብዙዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል::

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here