አፍሪካ እና የነዳጅ ሀብቷ

0
69

የዓለም የኢነርጂ እና የንግድ ደም ሥር የሚባለው የሆርሙዝ ሰርጥ በግጭት፣ በጦርነት ምክንያት መዘጋቱ የሚያስከትለው ችግር በማዕከላዊ ምሥራቅ ብቻ አይቆምም፡፡ ተጽእኖው እስከ አፍሪካ ድረስ የተዘረጋ ነው፡፡

ሰርጡ በዓለም ላይ  የድፍድፍ ነዳጅ እና ፈሳሽ ጋዝ በከፍተኛ መጠን የሚያልፍበት ዋና የባሕር መንገድ ነው፡፡ ይህ መስመር ሲዘጋ ወይም ችግር ሲፈጠርበት፣ ዓለም አቀፍ ገበያዎች በፍጥነት ይናወጣሉ፤ የነዳጅ ዋጋ እና የመርከብ መድን ክፍያ ይጨምራል፣ የማጓጓዣ ወጪ ከፍ ይላል፡፡ ከዚያም ይህ ሁሉ በቀጥታ በአፍሪካ የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል፡፡ አሁን የሆነውም ይህ ነው፡፡

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ነዳጅ አምራች ቢሆኑም እንኳን የተጣራ ነዳጅ ማለትም ፔትሮል፣ ዲዝል እና የጄት ነዳጅ (petrol, diesel, jet fuel) ከውጭ ሀገራት የሚያስገቡ  ናቸው፡፡ ለአብነትም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ እና ሌሎች ብዙ ሀገራት የነዳጅ ምንጫቸው በውጭ ሀገራት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡

ታሪካዊ ዳራ

አፍሪካ ዛሬ በዓለም የነዳጅ ካርታ ላይ በጠንካራ ሁኔታ የምትታይ አህጉር ናት፡፡ ሊቢያ፣ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ጋቦን… ያሉ ሀገራት በዘመናት ውስጥ የአህጉሪቱን የነዳጅ ኢኮኖሚ ቅርጽ ቀይረዋል፡፡

በታሪክ ማስረጃዎች መሠረት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ የነዳጅ አምራች ሀገራት ከጎርጎሮሳዊያኑ ከ1950ዎቹ መጨረሻ እስከ 1970ዎቹ ባሉት ጊዜያት መካከል ነው ከነዳጅ ምርታቸው  መጠቀም የጀመሩት፡፡ በአጭሩ 1960ዎቹ የመነሻ ዘመን ሲሆን 1970ዎቹ ደግሞ የነዳጅ ገቢ በአፍሪካ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ እውነተኛ ኀይል የሆነበት ዘመን ነው፡፡

ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ በአፍሪካ የነዳጅ ፍለጋ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሙከራዎች ብዙውን ጊዜ በፍለጋ ደረጃ ላይ ብቻ ነበሩ፤ ሀገራቱ ከነዳጅ በግልጽ ሁኔታ ገቢ ማግኘት የጀመሩት ግን ከነፃነት ዘመናቸው ጋር ይያያዛል፡፡

ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት መካከልም ሊቢያ በጎርጎሮሳዊያኑ በ1970ዎቹ እና በ2000 የአፍሪካ ከፍተኛ አምራች ነበረች፡፡ ሊቢያ በከፍተኛ ደረጃ በቀን ከሦስት ሚሊዮን በርሚል በላይ ምርት አስመዝግባለች፡፡ ሌላ የአፍሪካ ሀገር ይህንን ያሳካ አልነበረም፡፡ ይህም በአፍሪካ ከፍተኛ ምርት እንድታስመዘግብ አድርጓታል፡፡ ግብፅ ቀደም ብላ ታመርት ነበር፤ ነገር ግን ትልቁን ለውጥ ያመጣችው እ.አ.አ በ1950ዎቹ መጨረሻ እና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡

አሁን ላይ

በአፍሪካ ኢነርጅ ኮሚሽን ላይ(au-afrec.org) ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው በአፍሪካ የድፍድፍ ዘይት ምርት በቀን ወደ 10 ሚሊዮን በርሜል የሚጠጋ ሲሆን ይህም 10 በመቶውን የዓለም ድፍድፍ ዘይት ምርትን ይወክላል፡፡ 75 በመቶው የሚሆነው የድፍድፍ ነዳጅ ወደ ውጭ የሚላክ ሲሆን  አብዛኛው የነዳጅ ምርቶችም ከውጭ የሚገቡ ናቸው፡፡ ይህም አፍሪካን በዓለም ላይ ብቸኛዋ የድፍድፍ ዘይት ወደ ውጭ የምትልክ እና የተጣራ የነዳጅ ምርቶችን አስመጪ ያደርጋታል፡፡

በተጨማሪም አፍሪካ ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝ የተጎናጸፈች ሲሆን ይህም በዋናነት በአልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ሊቢያ፣ ናይጄሪያ እና ግብፅ ይገኛል፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው የዓለም አዲስ የተፈጥሮ ጋዝ ግኝቶች በአፍሪካ በተለይም በሴኔጋል፣ በሞሪታኒያ፣ በሞዛምቢክ፣ በታንዛኒያ እና በሌሎችም ተገኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከ45 በመቶ በላይ የሚሆነው የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ወደ ውጭ የሚላክ ሲሆን የተፈጥሮ ጋዝ በአፍሪካ የኢነርጂ ሚዛን ውስጥ ያለው አስተዋፅኦ አነስተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ተፈጥሮ ጋዝ ያሉ ሀብቶች የአየር ንብረት ለውጥን እና የኢነርጂ ሽግግርን ዓለም አቀፋዊ ስጋትን ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ጋር በተያያዘ የረጅም ጊዜ ደኅንነትን ለማራመድ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ፡፡

ይሁንና የአፍሪካ የነዳጅ ሀብት በጣም ትልቅ፣ በስፋት የተበተነ እና ለዓለም ኢኮኖሚ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አፍሪካ በዓለም ላይ ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ (crude oil) እና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ያላት አህጉር ስትሆን በተለይም ሰሜን  እና ምዕራብ አፍሪካ በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ፡፡

የአፍሪካ የነዳጅ ሀብት አጠቃላይ ሁኔታ

በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ካላቸው ሀገራት መካከል ሊቢያ አንዷ ናት፡፡ በአፍሪካ ከፍተኛውን የድፍድፍ ነዳጅ ክምችት ባለቤትም ናት፡፡ በመቀጠል ናይጄሪያ ስትሆን ትልቅ ክምችት እና ትልቅ ምርት ያላት ሀገር ናት፡፡

በነዳጅ እና በተፈጥሯዊ ጋዝ በሀብት በጣም  የበለፀገችው ሦስተኛዋ ሀገር ደግሞ አልጄሪያ ናት፡፡ አንጎላ በባሕር ውስጥ (offshore) የተለያዩ የነዳጅ መስኮች ባለቤት በመሆን  ቀዳሚ ስትሆን  በነዳጅ እና በጋዝ  ደግሞ ግብጽ ትከተላለች፡፡ በአጭሩ አልጀሪያ፣ ግብጽ እና  ሊቢያ በሰሜን አፍሪካ የታላቅ የነዳጅ ሀብት ማዕከላት ናቸው፡፡

ሰሜን አፍሪካ፡- ከፍተኛ የነዳጅ እና የጋዝ ሀብት ያለበት ክልል ነው፡፡ ሰሜን አፍሪካ በተለይ ለአውሮፓ ቅርብ ስለሆነ ለነዳጅ እና ጋዝ ንግድ በጣም ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው፡፡ ሊቢያ፣ አልጄሪያ፣ ግብጽ  በቅደም ተከተል ባላቸው ሀብት ሲገለጹ፤ በቱኒዚያ አነስተኛ መጠን፣ በሞሮኮ ደግሞ በጣም አነስተኛ እና በፍለጋ ደረጃ ላይ የሚገኝ  ነው፡፡

ምዕራብ አፍሪካ፡- የአፍሪካ በጣም አስፈላጊ የነዳጅ ቀበቶ በመባል የታወቃል፡፡ ናይጄሪያ  በጣም ትልቅ ድፍድፍ ነዳጅ አምራች ሀገር ናት፡፡ ጋና  አዲስ በባሕር ውስጥ ነዳጅ ሀብት ታዋቂ ሆናለች፡፡ ኮትዲቯር እና ሴኔጋልም በቅርብ ዘመን የተገኘ ሀብት አላቸው፡፡ ሞሪታኒያ  በተለይ በጋዝ፣ ጋቦን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ካሜሩን በባሕር ውስጥ ያለ (offshore) ነዳጅ ሀብት እንዳላቸው ይነገራል፡፡

ምሥራቅ አፍሪካ፡- ይህ ክልል ቀድሞ ከነዳጅ ጋር ብዙ ያልታወቀ ቢሆንም በቅርብ ዓመታት ትልቅ ግኝቶች ብቅ ብለዋል፡፡ ዩጋንዳ በአልበርት ሐይቅ (Lake Albert) አካባቢ ትልቅ የድፍድፍ ነዳጅ ክምችት እንዳላት ታውቋል፡፡ በታንዛኒያ እና ሞዛምቢክ ጋዝ ተገኝቷል፤ በሶማሊያ ገና ፍለጋ እና ምርመር እየተደረገ ነው፡፡

በኢትዮጵያም በኦጋዴን አካባቢ የጋዝ ምርመራ እና አንዳንድ ግኝቶች ተጠቅሰዋል፡፡ ሱዳን  እና  ደቡብ ሱዳን ጦርነት እና ግጭት ቢፈትናቸውም የነዳጅ ሀብት ባለቤት ናቸው፡፡

ማዕከላዊ አፍሪካ፡- ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ስናመራ ደግሞ ቻድ፣ ኮንጎ፣ ጋቦን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ አብዛኛው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የመሠረተ ልማት እጥረት ሀብቱን ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀሙበት አድርጓል፡፡

አፍሪካ ለምን ተጠቃሚ አልሆነችም?

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የነዳጅ ሀብት ቢኖራቸውም ይህን ሀብታቸውን አውጥተው ሕዝባቸውን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በዋነኛነት ከፍተኛ የሆነ የሀገር ውስጥ የማጣራት አቅም ባለመኖሩ አፍሪካዊያን  ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ የውጭ ነዳጅ ላይ ጥገኛ ሆነዋል፡፡ እንደ ናይጄሪያ ያሉ ዋና ዋና አምራቾች ድፍድፍ ዘይትን ወደ ውጭ የሚልኩት  እንደ ቤንዚን ያሉ የተጣራ ምርቶችን ለማስመጣት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የራሳቸው ማጣሪያዎች    ስለሌላቸው ነው፡፡ ይህ የመሰረተ ልማት እጥረት ከፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ከክልላዊ ውህደት እጦት እና ከደካማ ጥገና ጋር ተዳምሮ አህጉሪቱ በሌሎች ላይ ጥገኛ እንድትሆን አድርጓታል፡፡

ሙስና፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የውጭ ኩባንያዎች በጣም ከፍተኛ ቁጥጥር መኖር፣ የነዳጅ ገቢ እኩል አለመከፋፈል፣ የአካባቢ ብክለት…ለችግሩ መከሰት ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡  ለአብነትም  ናይጄሪያ ብዙ ነዳጅ ቢኖራትም የናይጀር ዴልታ አካባቢ በብክለትና በድህነት የተጎዳ ነው፡፡ የፖለቲካ ቀውስ ሀገሪቱን ቁልቀል ወደ ታች እያንደረደራት ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን ነዳጅ ዋና የገቢ ምንጯ ቢሆንም ጦርነት መለያዋ ሆኗል፡፡

ለአብነትም ከኢንተርናሽናል ኢነርጅ ኤጀንሲ (www.iea.gov) ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ናይጄሪያ በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት አምራች ነበረች፤ ነገር ግን መስተጓጎሎች የምርት ስጋት ፈጥረዋል፡፡ ለብዙ ዓመታት በናይጄሪያ ውስጥ ከማንኛውም የአፍሪካ ሀገር በበለጠ ብዙ የድፍድፍ ነዳጅ ይመረታል፡፡ ሆኖም ግን በናይጄሪያ ውስጥ ያልታቀደ የምርት መቆራረጥ ወይም መስተጓጎል ያጋጥማል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የድፍድፍ ነዳጅ ምርቷ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ከፍተኛ አምራች ሀገር ከሆነችው ከአንጎላ በታች እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

የአፍሪካ የነዳጅ ሀብት የወደፊት አቅጣጫ

አፍሪካ ወደ ፊት ከነዳጅ ዘርፉ እንድትጠቀም የአካባቢ ማጣሪያ ፋብሪካዎች (refineries) መገንባት፣ ድፍድፍ ነዳጅ ብቻ ሳይሆን  እሴት ጨምራ   ምርቱን መላክ፣ የሚገኝ ገቢን ወደ ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ፣ ኢንዱስትሪ መቀየር ሙስናን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ከነዳጅ በተጨማሪ ወደ ንፁህ ታዳሽ ኀይል የ(solar, wind, hydro) መሻገር እና በአፍሪካ ውስጥ የኀይል ገበያ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

የአሊኮ ዳንጎቴ የሰሞኑ ማስጠንቀቂያ የአፍሪካን አሳሳቢ ተጋላጭነት አጉልቶ ያሳያል፡፡ ምንም እንኳን የተትረፈረፈ የድፍድፍ ዘይት ክምችት ቢኖርም አህጉሪቱ የተጣራ ምርቶችን እያስገባች ጥሬ እቃ ትልካለች፡፡ ይህ ጥገኝነት አፍሪካን ለዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል እና በጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች ለሚመጣ ለዋጋ ግሽበት ያጋልጣል፡፡ አፍሪካ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ፣ ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማጎልበት እና በራስ የሚተማመን የኢኮኖሚ ኀይል ለመፍጠር የረጅም ጊዜ የኢነርጂ ነፃነት ስትራቴጂ መንደፍ ያስፈልጋታል፡፡

 

 

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 21  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here