የነዳጅ እጥረት ስጋት እና መፍትሔዎቹ

0
62

በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ የመጣው ቀውስ በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ መስተጓጎልን ፈጥሯል። ኢትዮጵያም የዚህ ተጽዕኖ ሰለባ ሆናለች። በግብይት ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፣ ባለማደያዎች አጋጣሚውን በመጠቀም አቅርቦቱን መደበቅ ወይም በጥቅም ትስስር መሥራት፣ በፍጆታ ምርቶች ላይ ያልተገባ ዋጋ መጨመር፣ ነዳጅን በጥቁር ገበያ መሸጥ እና መሰል ችግሮች በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተከሰቱ ነው። በዚህም አገልግሎት ፈላጊው እና አገልግሎት ሰጪዎች ምሬታቸውን ሲገልጹ ይሰማሉ::

አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የመኪና አሽከርካሪዎች እንደተናገሩት የነዳጅ እጥረቱ ከቀን ወደ ቀን ተባብሷል:: ነዳጅ ለመቅዳት ተራ ይዘው እስከ ሁለት ቀን ሊጠብቁ ይችላሉ:: ይህም ሆኖ መቶ ሰው እንኳን ሳይቀዳ ”አለቀ!” ተብለው ይሰናበታሉ:: ነዳጅም ሳያገኙ መኪናቸው ተራ ይዞ ላደረበት ለጥበቃ ሁለት መቶ ብር ይከፍላሉ:: እናም አሁን ላይ ለተጨማሪ እንግልት እና ወጭ እየተዳረጉ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ማደያዎች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጠይቀዋል::

በአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፣ ማደያዎች አጋጣሚውን በመጠቀም አቅርቦቱን መደበቅ ወይም በጥቅም ትስስር መሥራት፣ በፍጆታ ምርቶች ላይ ያልተገባ ዋጋ መጨመር፣ ነዳጅን በጥቁር ገበያ መሸጥ እና መሰል ችግሮች ቀውሱን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች ናቸው ተብሎ በስጋትነት ተለይተው የተያዙ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደነበሩ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ፈንታው ፈጠነ አስታውሰዋል:: በአሁኑ ወቅትም በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ የመጣውን ቀውስ ተከትሎ ችግሩ መከሰቱን ጠቁመዋል:: ይህን ተከትሎም በችግር ፈጣሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተጠቁሟል።

ከነዳጅ እጥረቱ ጋር ተያይዞ በኑሮ ውድነቱ ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ እና የችግሩ መውጫ መንገዶችን በተመለከተም ምክትል ቢሮ  ኃላፊው ሀሳባቸውን አካፍለውናል:: አቶ ፈንታው እንደሚሉት የነዳጅ ዋጋ እና የኑሮ ውድነት በቀጥታ ተያያዥነት አላቸው:: ምክንያቱ ደግሞ ማንኛውም የምርት እንቅስቃሴ ከነዳጅ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው:: በዚህም  የነዳጅ ዋጋ መጨመር ለኑሮ ውድነቱ ማሻቀብ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል::

በሀገራችን ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታው ጋር ሲነጻጸር ጭማሪው ዝቅተኛ መሆኑን ያነሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ይህም በኑሮ ውድነቱ ላይ ጫና እንዳያሳድር መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ አድርጓል:: ነገር ግን በነዳጅም ሆነ በቤንዚን ላይ የተጨመረው ዋጋ ዝቅተኛ ሆኖ እያለ ኅብረተሳቡ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ እንዲከፍል እየተደረገ ነው:: ይህንን ያለ አግባብ የመጓጓዣ ዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ እንዲሁም  ከጸጥታ ተቋማት ጋር  መድረክ በመፍጠር እንዲስተካከል አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል:: ይህንን መሰረት በማረግም የመንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ የዋጋ ተመን ማውጣቱን አቶ ፈንታው ጠቁመዋል:: የተተመነው ዋጋ በትክክል እየተተገበረ ነው? የሚለውን በመገምገምም በኑሮ ውድነቱ ላይ ጫና እንዳይፈጠር እየተሠራ  ነው::

የሀገር ውስጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚው ዕድገት ወሳኝ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ ተገቢ ያልሆኑ አሠራሮች በኅብረተሰቡ ላይ ጫና እየፈጠሩ  እንደሚገኙም  የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አሳውቋል። መምሪያው የነዳጅ ዋጋ መስተካከልን ምክንያት በማድረግ ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩንም ለአሚኮ ጠቁሟል። ለአብነትም ማደያዎችን ማሸግ፣ ያልተገባ የታሪፍ ጭማሪ ያደረጉ አሽከርካሪዎችን  ከመስመር ማገድን ጨምሮ ሌሎች የእርምት ርምጃዎች  መወሰዳቸውን መምሪያው አስታውቋል።

በሕግ ከተወሰነው ታሪፍ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም የዋጋ ጭማሪ በዝቅተኛው ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ የሚያስከትል በመሆኑ ይህን ሕገ-ወጥ ተግባር ለመከላከል ፖሊስ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝም ነው የገለጸው።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ በተለይ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፤ ቢሮው ይህንን በማገናዘብ  አምራች እና ሸማች የሚገናኙበት የገበያ ማዕከል እየገነባ ነው:: በዚህም አምራቾችን በቀጥታ በመለየት እና ድጋፍ በማድረግ ወደ ገበያ ማዕከላቱ እንዲገቡ በማመቻቸት ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሕበረሰቡ እንዲያቀርቡ እና ከሸማቹ ላይ አላስፈላጊ ዋጋ እንዳይጨምሩ የማድረግ ሥራም እየተሠራ ነው::

ምክትል ቢሮ ኃላፊው ሌላው የጠቆሙት  መፍትሔ ቢሮው ከእሁድ እስከ እሁድ  ገበያን በማቋቋም በምርት ዋጋ ላይ በደላሎች የሚፈፀም አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን  በማስቀረት ሸማቹ በቀጥታ ከአምራቹ ግብይት እንዲፈጽም የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው:: በዚህም ከትራንስፖርት ወጭ ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በምርቶች ላይ ዋጋ እንዳይጨመር እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል::

በዚህም አርሶ አደሮች አምራቾች በመሆናቸው የመጣውን ነዳጅ በፍትሐዊነት ምርታቸውን ለማምረት የሚያስችላቸውን ነዳጅ እንዲያገኙም ቅድሚያ በኩፖን እንዲያገኙ ተደርጓል:: ከዚህ በተጨማሪ አምራቾችን ከየቀጠናው በመለየት ምርታቸውን የሚያደርሱበት ነዳጅ ማደያዎች ቅድሚያ እንዲሰጧቸው በማድረግ ምርታቸውን መዳረሻ ላይ እንዲያደርሱ የማድረግ ድጋፍም  እየተደረገ ነው::

“የነዳጅ ዋጋ መጨመር በኑሮ ውድነቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አላሳደረም ማለት አይቻልም” ያሉት አቶ ፈንታው፤  ከቅርብ የጎረቤት ሀገራትንም ሆነ ከዓለም ገበያ ጋር ያለው ሲታይ ግን በኢትዮጵያ ላይ ያለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በእጅጉ የቀነሰ ነው:: “ይህንኑ መሠረት ያደረገ ጭማሪ እንኳን ቢኖር አሳማኝነቱ ተረጋግጦ በመንግሥት ተቀባይነት ሲኖረው ብቻ ቀጣይነት ይኖረዋል” ነው ያሉት:: የተጨመረው ዋጋ ደግሞ ሕገ ወጥ ሆኖ ሲገኝ ወደ ነበረው እንዲመለሱ ሕግ ያስገድዳቸዋል::

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ  የንግዱ ማኅበረሰብ፣  አምራቹም ሆነ ሌላው የክልሉ ነዋሪ ጭምር ይዞት ከመጣው እሳቤ አኳያ ”ዋጋ ጨመረ” ሲባል ምን ያክል ጨመረ? የሚለውን አነጻጽሮ ምን ያክል አሳማኝ ነው? የሚለውን በማስተዋል ከመንግሥት ጎን ሆኖ አጋዥ ከመሆን ይልቅ ለሕገ ወጥ ተባባሪ ሲሆኑ ይስተዋላል:: እነዚህ ችግሮች ከተፈቱ ደግሞ አሁን የተጨመረው የነዳጅ ዋጋ  ለተባባሰ የዋጋ ጭማሪ የሚዳርግ አይደለም::  በተመሳሳይ የመካለኛው ምሥራቅ ጦርነት ቢራዘም ነዳጅ ሊጠፋ ይችላል በሚል ሰበብ ነዳጅ የሚከዝኑ አካላት እንዳይኖሩም መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው::

በሀገሪቱ የነዳጅ መጠባበቂያ ዲፖዎች በመኖራቸው ከዚህ ለባሰ ችግር እንዲያገለግሉ ይሆናል፤ ችግሩ እስኪፈታ ግን በቁጠባ የመጠቀም ሁኔታ ግድ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስገንዝበዋል::

ከዚህ ባለፈ በሕገ – ወጥ መንገድ ነዳጅም ሆነ በነዳጅ እጥረት ምክንያት ሊወደድ ይችላል በሚል ምርቶችን እና የፋብሪካ ውጤቶችን ከዝኖ የተገኘ ከጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ሕጋዊ ርምጃ በመውሰድ የተከዘኑ ምርቶች እና ነዳጅ ውርስ እንደሚደረጉም ነው የጠቆሙት::

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ፣ የዓለም ባንክ፣ የፔትሮሊየም ላኪ ሀገራት ድርጅት በድረ ገፆቻቸው እንዳስቀመጡት የነዳጅ እጥረት ወይም ችግር ሲከሰት ሀገራት በተለያዩ መንገዶች ለችግሩ መፍትሔ ወይም ርምጃ ይወስዳሉ። ከእነዚህም መካከል ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በመኪና ቁጥር (even/odd plate system) የሚጠቀሙበትን ነዳጅ በቀን ወይም በሳምንት በመከፋፈል መጠኑን መገደብ፣ አማራጭ የኃይል ምንጮችን መፍጠር እንደ የፀሐይ  እና  የነፋስ ኀይል እንዲሁም የኤሌክትሪክ መኪናዎችን መጠቀም፣ የግል መኪና በመተው  የሕዝብ መጓጓዣን መጠቀም፣ የሥራ ሰዓትን ማስተካከል፣ ነዳጅን ለአጣዳፊና ወሣኝ ጊዜም መጠቀም፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር ስምምነት መፍጠር እና ሀገራት ነዳጅ የሚያገኙበትን አዲስ ንግድና ግንኙነት ከሌሎች ሀገራት ጋር መመሥረት ተጠቃሾች ናቸው::

በአጠቃላይ ሀገራት የነዳጅ ችግር ሲኖር አጠቃቀምን መቆጣጠር፣ አማራጭ የኃይል ምንጭ መፍጠር እና ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎችን መውሰድ ሊከተሏቸው የሚገቡ ዋና ዋናዎች የምፍትሔ ሀሳቦች ናቸው::

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)  በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክትም በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ቀውስ ምክንያት ሀገራችን የተጽዕኖው ሰለባ መሆኗን ጠቁመዋል። በመሆኑም ነዳጅን እንደልብ ለማግኘት አዳጋች እየሆነ በመምጣቱ ኅብረተሰቡ ያለውን ክምችት በከፍተኛ ጥንቃቄ፣ በኃላፊነት ስሜት እና በቁጠባ እንዲጠቀም አስገንዝበዋል።

ችግሩ ተፈትቶ አቅርቦቱ ወደ መደበኛ ሁኔታው እስኪመለስ ድረስ ነዳጅ አከፋፋዮች፣ ማደያዎችና ተጠቃሚዎች ቅድሚያ ለሚያስፈልጉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ብቻ ትኩረት እንዲሰጡም ነው ጠቅላይ ሚኒሥትሩ ያሳሰቡት። ሁሉም ዜጋ ነዳጅን ያለአግባብ ከማባከን ተቆጥቦ ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠቅላይ ሚኒሥትሩ አስገንዝበዋል።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመጋቢት 21  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here