ሰላዩ ንጉሠ ነገሥት

0
66

በካፋ የሚለው ስም ትርጉም ቆራጥ፣ ከወሰነ ወደኋላ የማይል፣ ብርቱ ሰው ማለት መሆኑን በመልአከ ብርሃን ብርሃኑ ብስራት የተጻፈው የመጠሪያ ስሞች መዝገብ ይገልጻል:: ንጉሠ ነገሥት ዐፄ በካፋ ወደ ሥልጣን ከመውጣታቸው በፊት በወህኒ ተረር ታስረው በነበረበት ወቅት፣ ከዚያ አምልጠው በየጁ (ወሎ) አካባቢ ከሚኖሩት ኦሮሞዎች ጋር ለተወሰነ ጊዜ ተደብቀው ኖረዋል። በዚያ ቆይታቸው ነው ይህንን “በካፋ” የሚለውን መጠሪያ ወይም ቅጽል ስም ያገኙት። የዐፄ በካፋ ትክክለኛ ሥም አፅመ ጊዮርጊስ ነው።  በኋላ ወደ ጎንደር ተመልሰው ንጉሥ ሲሆኑ መሽገው በነበር ጊዜ የሸሸጓቸውን ሥልጣን ሰጥተዋቸዋል ወይም ሾመዋቸዋል። እነሱም አይበገሬው (የማይሸነፈው) ሲሉ በካፋ ብለው ሥም አውጥተውላቸዋል።

አፅመ ጊዮርጊስ እና መሲሕ ሰገድ በሚለውም ሥመ መንግሥት ይጠራሉ ሲሉ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን “Wax and Gold” በሚለው መጽሐፋቸው ጽፈዋል።

ዐፄ በካፋ ከዐፄ ልብነ ድንግል ሐረግ፣ ከቤተ ዐፄ ፋሲል የተወለዱ ንጉሠ ነገሥት ናቸው። ትውልዱም የሚከተለው ነው፤  ዐፄ ልብነ ድንግል አቤቶ ያዕቆብን፣ አቤቶ ያዕቆብ አቤቶ ገራም ፋሲልን፣ አቤቶ ገራም ፋሲል ዐፄ ሱስኒዮስን፣ ዐፄ ሱስኒዮስ ዐፄ ፋሲለደስን፣ ዐፄ ፋሲለደስ ዐፄ አዕላፍ ሰገድን (ፃዲቁ ዮሐንስን)፣ ዐፄ አዕላፍ ሰገድ ዐፄ አዲያም ሰገድን (ታላቁ ኢያሱን)፣ ዐፄ አዲያም ሰገድ ዐፄ አፅመ ጊዮርጊስን (በካፋን) ይወልዳሉ።

ዐፄ በካፋ በጎንደር ዘመነ መንግሥት ካለፉት ነገሥታት መካከል በጠንካራ አመራራቸውና ለየት ባሉ የግል ባሕርያቸው ጎልተው የሚታወቁ ንጉሠ ነገሥት ናቸው። የዐፄ ቀዳማዊ ኢያሱ ልጅ የሆኑት እኚህ ንጉሥ ወደ ሥልጣን ከመውጣታቸው በፊት በነበረው የቤተመንግሥት ሽኩቻ ምክንያት በወህኒ ተረር ታስረው ቆይተው ነበር። በ1713 ዓ.ም ወንድማቸው ዐፄ ዳዊት ሣልሳዊ ሲሞቱ በቤተመንግሥት ጠባቂዎች አማካኝነት ከእስር ተፈትተው በዙፋኑ ላይ ተቀመጡ። በንግሥና ስማቸውም መሲሕ ሰገድ ተባሉ።

የዐፄ በካፋ አገዛዝ በዋናነት የሚታወሰው የኢትዮጵያን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር በወሰዷቸው ጥብቅ እርምጃዎች መሆኑን ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን እንደገና “Greater Ethiopia” በሚለው መጽሐፋቸው ያስረዳሉ። በወቅቱ የነበረውን የባላባቶችና የጦር መሪዎች መጠላለፍ ለመቆጣጠር በወሰዱት የኃይል እርምጃ ምክንያት “በካፋ” (የማይመለስ ወይም ጨካኝ) የሚል ቅጽል ስም እንደተሰጣቸው ይነገራል። ይሁን እንጂ ንጉሡ ለፍትሕ የቆሙና የሕዝብን ችግር በቅርብ ለመረዳት የሚጥሩ ነበሩ። ማንነታቸውን ደብቀውና እንደ ተራ ሰው ተመስለው በየገበያውና በየመንደሩ በመዘዋወር ባለሥልጣናት የሚያደርሱትን በደል በጆሯቸው ይሰሙ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት እንዲህ ባለ ጉዞ ላይ ሳሉ ታመው በቆዩበት ቤት ውስጥ የምታስታምማቸውን ወጣት ብርሃን ሞገሳን (በኋላ እቴጌ ምንተዋብ) አግኝተው እንዳገቧት በታሪክ ይነገራል።

በህንፃ ግንባታ ረገድም በፋሲል ግቢ ውስጥ ሰፊና ውብ የሆነ የግብዣ አዳራሽ (Banqueting Hall) አስገንብተዋል። ይህ አዳራሽ በወቅቱ የነበረውን የኪነ-ህንፃ ጥበብ ዕድገት የሚያሳይ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ ከ10 ዓመታት የግዛት ዘመን በኋላ በ1723 ዓ.ም ሲያርፉ  ባለቤታቸው እቴጌ ምንተዋብ ልጃቸው ዐፄ ዳግማዊ ኢያሱ እስኪያድግ ድረስ በሞግዚትነት ሥልጣኑን ተረክበው የጎንደርን ሥልጣኔ በሌላ ምዕራፍ አስቀጥለውታል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ንጉሡን ከሌሎቹ ነገሥታት ለይተው የሚያሳውቋቸው  የሚያደርጓቸው ምስጢራዊ ጉዞዎች ናቸው። ንጉሡ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት የሚያቀርቡላቸውን ሪፖርት ብቻ አምኖ ከመቀበል ይልቅ እውነቱን በአካል ማየትና መስማት ይመርጡ ነበር። ለዚህም ሲሉ የንጉሥ ልብሳቸውን አውልቀው፣ እንደ ተራ መንገደኛ፣ ነጋዴ ወይም ድኃ በመምሰል ማንነታቸውን ደብቀው በየገበያውና በየመንደሩ ይሰርጉ ነበር።

እነዚህ ጉዞዎች ንጉሡ በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን እውነተኛ ስሜት እንዲረዱ ከማድረጋቸውም በላይ በሕዝብ ላይ ግፍ የሚፈጽሙ ሹማምንትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል አስችሏቸዋል። በአንድ የታወቀ ታሪካቸው ላይ ንጉሡ ተራ ሰው መስለው በአንድ የገበያ ቦታ ሲዘዋወሩ አንድ ባለሥልጣን አንድ ድኃ ገበሬን ሲበድልና ንብረቱን ሲቀማ  ያያሉ። በነገታው ያንን ባለሥልጣን ወደ ችሎት አስጠርተው ትላንት ያዩትን ድርጊት በዝርዝር በመናገርና ባለሥልጣኑን በማሳፈር ፍትሕ እንደሰጡ ይነገራል። ይህም በሹማምንቱ ዘንድ “ንጉሡ በየቦታው አለ” የሚል ፍርሃትን ስለፈጠረ ሙስናና ግፍ እንዲቀንስ አድርጓል።

የእነዚህ ምስጢራዊ ጉዞዎች ሌላው ትልቅ ውጤት የትዳር አጋራቸውን ያገኙበት መንገድ ነው። በአንድ ወቅት ማንነታቸውን ደብቀው ሲጓዙ በጠና ታመው ኩዋራ በሚባል ቦታ በአንድ ገበሬ ቤት ለማረፍ ይገደዳሉ። በዚያም የገበሬው ልጅ የነበረችው ወጣት ወይዘሮ ብርሃን ሞገሳ (በኋላ እቴጌ ምንተዋብ) ንጉሥ መሆናቸውን ሳታውቅ በቅንነትና በጥንቃቄ ታስታምማቸዋለች። ንጉሡ ከሕመማቸው ካገገሙ በኋላ የልጅቷን ደግነትና አስተዋይነት ተረድተው ወደ ጎንደር ወስደው በማግባት ንግሥት አድርገዋታል። ይህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ የነበራቸውን እቴጌ ምንተዋብን ወደ ሥልጣን እንዲመጡ መንገድ ከፍቷል።

ንጉሡ በዚህ ተግባራቸው ምክንያት በሕዝብ ዘንድ እንደ “ፍትሐዊ ሰላይ” ይታዩ ነበር። ይህ አሠራራቸው መንግሥታቸው ጠንካራና የተረጋጋ እንዲሆን ቢረዳውም በባለሥልጣናቱ ዘንድ ግን ከፍተኛ ጥርጣሬና ፍርሃት እንዲነግሥ አድርጓል።

ዐፄ በካፋ በፍርድ አሰጣጣቸው ረገድ “ጥብቅ ግን ደግሞ ሚዛናዊ” ተብለው ይታወቃሉ። ፍርዳቸው በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ላይ የተመሠረተ ነበር:: መጀመሪያ፣ በምስጢራዊ ጉዞዎቻቸው ያገኙትን መረጃ እንደ ማስረጃ ይጠቀሙ ነበር። ንጉሡ ማንነታቸውን ደብቀው በሕዝብ መካከል ስለሚዞሩ አንድ ባለሥልጣን ጉቦ ሲቀበል ወይም በድኃ ላይ ግፍ ሲፈጽም  ካዩ ያንን ሰው ችሎት አቁመው “እንዲህ ስታደርግ አላየሁህም ወይ?” በማለት በማያሻማ ሁኔታ ይፈርዱበት ነበር።

ሁለተኛ “የዐፄ በካፋ በግ” የሚባለው ዝነኛ ታሪካቸው የእሳቸውን የፍርድ ጥበብ ያሳያል። ታሪኩ እንደሚለው አንድ ሰው የንጉሡን በግ ሰርቆ አርዶ በላ ተብሎ ይከሰሳል። ንጉሡም ሰውየውን አስጠርተው “በጉን በላኸው?” ብለው ሲጠይቁት ሰውየው በፈጠራ ሳይሆን በእውነት “አዎ ጌታዬ፣ በጣም ርቦኝ ስለነበር በላሁት” ብሎ አመነ። ንጉሡም በሰውየው እውነተኝነት ተደስተው “እውነትን ስለተናገርክ ምሬሃለሁ” በማለት በነፃ አሰናብተውታል። ይህ ድርጊት ንጉሡ ከቅጣት ይልቅ ለእውነትና ለንስሐ ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጡ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል።

የዐፄ በካፋ ፍርድ ለሐሰተኞችና ለግፈኞች እጅግ መራራና የማያዳግም (በካፋ/የማይመለስ) ነበር። ለእውነተኞችና ለተበደሉ ደግሞ መጠጊያና ሩኅሩኅ ነበሩ። በዚህም ምክንያት በዘመናቸው በጎንደር መንግሥት ውስጥ ሥርዓትና ሕግ እንዲከበር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

የዐፄ በካፋ የህንፃ ግንባታ አሻራዎች በዋናነት የሚገኙት በታሪካዊቷ የጎንደር ፋሲል ግቢ ውስጥ ነው። ንጉሡ በኪነ-ህንፃ ረገድ ከቀድሞ ነገሥታት የተለየና ለየት ያለ ጥበብ የታየበት ሥራ ጥለው አልፈዋል።

ዋና ዋናዎቹ ግንባታዎች የሚከተሉት ናቸው፤ ትልቁ የግብዣ አዳራሽ (Banqueting Hall) አንዱ ነው:: ይህ በዐፄ በካፋ ዘመን የተገነባው ሰፊ አዳራሽ በግቢው ውስጥ ካሉ ህንፃዎች እጅግ ረጅሙና ትልቁ ነው። አዳራሹ ለንጉሣዊ ግብዣዎች፣ ለትልልቅ በዓላትና ለዲፕሎማሲያዊ መስተንግዶዎች ያገለግል ነበር። የህንፃው ግድግዳዎች በወቅቱ በነበረው የድንጋይና የኖራ ጥበብ የታነጹ ሲሆን ሰፊ መስኮቶችና በሮች ያሉት በመሆኑ ለብርሃንና ለንፋስ አመቺ ነበር።

ንጉሡ ለባለቤታቸው ለእቴጌ ምንትዋብ በፋሲል ግቢ ውስጥ የተለየና ውብ መኖሪያ ቤተ-መንግሥት አስገንብተውላቸዋል። ይህ ህንፃ ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በንግሥት የሚመራ በመሆኑ የራሱ የሆነ የግል ምቾትና ጥበብ የተላበሰ ነበር። ሌላው የፈረሰኞችና የጥበቃዎች መቆያ ሲሆን በግቢው ዙሪያ ለንጉሡ የክብር ዘበኞችና ለፈረሰኛ ጦራቸው የሚሆኑ መጠለያዎችንና ቢሮዎችን አስገንብተዋል። ይህም የቤተ-መንግሥቱን ደህንነትና ሥርዓት ለማጠናከር የነበራቸውን ፍላጎት ያሳያል።

አያሌ አብያተ ክርስቲያናት በዐፄ በካፋ እንደ ቀድሞ ነገሥታት ሁሉ ለሃይማኖት ትልቅ ቦታ ይሰጡ ስለነበር በጎንደርና በዙሪያዋ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳደስና አዳዲስ በመገንባት ይታወቃሉ። በተለይም የቁስቋም ማርያም ገዳም ግንባታ በእሳቸው ዘመን ተጀምሮ በባለቤታቸው በእቴጌ ምንተዋብ ተጠናቋል።

 

 

ሳምንቱ በታሪክ

ዐፄ ሱስኒዮስ ዘውድ ጫኑ

ዐፄ ሱስኒዮስ መጋቢት 23 ቀን 1601 ዓ.ም በአክሱም በይፋ ዘውድ ጫኑ። ወደ ሥልጣን የመጡትም ከቀዳሚዎቻቸው ጋር በተደረገ ረጅም የእርስ በእርስ ጦርነት ነው።

በታሪክ በብዛት የሚታወቁት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ትተው የካቶሊክ እምነትን በመቀበላቸውና የሀገሪቱ ይፋዊ ሃይማኖት እንዲሆን በማወጃቸው ነው። ይህ ውሳኔ ከፖርቱጋል ጋር ወታደራዊ ግንኙነት ለመፍጠር ታስቦ የተደረገ ነበር፡፡

የሃይማኖት ለውጡን ተከትሎ በሀገሪቱ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ተከሰተ። ሕዝቡና መኳንንቱ “ሃይማኖታችንን አንለቅም” በማለታቸው ንጉሡ ከገዛ ሕዝባቸው ጋር ለዓመታት ተዋግተዋል።

በመጨረሻም በጦርነቱ ያለቀውን ሕዝብ ብዛትና የደረሰውን እልቂት ሲመለከቱ ሰኔ 7 ቀን 1624 ዓ.ም “የቀድሞው ሃይማኖታችሁ ይመለስ” የሚል ዐዋጅ አውጥተው ሥልጣናቸውን ለልጃቸው ለዐፄ ፋሲለደስ አስረከቡ።

በጎንደር አካባቢ የሚገኙት የደንቀዝ እና የጉዛራ ቤተ መንግሥታት ፍርስራሾች የእሳቸው ዘመን የሕንጻ ጥበብ ውጤቶች ናቸው። ዐፄ ሱስንዮስ ሥልጣን ከለቀቁ ከጥቂት ወራት በኋላ በ1625 ዓ.ም አርፈው በደንቀዝ ተቀብረዋል።

ምንጭ፡- ፍስሃ ያዜ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከኖህ እስከ ኤሐዴግ”“ (ቁ-1)

የመጀመሪያው ሞባይል ሽያጭ

የመጀመሪያው የሞባይል ስልክ ሽያጭ የተጀመረው ከጥሪው አሥር ዓመታት በኋላ በ1983 እ.ኤ.አ ሲሆን ዋጋውም 3,995 ዶላር ነበር። ይህ ዋጋ በዛሬው የገንዘብ ምንዛሬ ሲሰላ ከ11,000 ዶላር በላይ ወይም ከአንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ ይሆናል። ስልኩ በጣም ግዙፍና ከባድ በመሆኑ በወቅቱ “ጡቡ” (The Brick) የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት ነበር። ማርቲን ኩፐር ይህን ስልክ የሠራው ሰዎች በሄዱበት ቦታ ሁሉ መገናኘት እንዲችሉ በማሰብ ሲሆን የቤል ላብራቶሪስ ኩባንያ ግን በወቅቱ ትኩረቱ የመኪና ስልኮች ላይ ብቻ ነበር።

ምንጭ፡-ቢቢሲ

 

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመጋቢት 21  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here