30 ዓመታት – በትጋት

0
28

ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የታለመለትን ዓላማ እና ግብ ለማሳካት ለሦስት አስርት ዓመታት ያለመታከት ተግቷል:: ለዚህ ትጋቱ የመንግሥታዊ እና ህዝባዊ እውቅና ሽልማቶችን በተቀኛጀበት በዚሁ ዓመት እነሆ የ30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር ታድሏል:: “ለህብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!” በሚል ድርጅታዊ መርሁ የሚታወቀው የህዝብ ልሳን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አሚኮ! የተመሰረተው ፌዴራላዊ ሥርዓት የወለደው የክልል መዋቅር በተዘረጋበት 1985 ዓ.ም ነው:: በፌደራል ደረጃ ሚኒስቴር የሚባሉት መንግሠታዊ መስሪያ ቤቶች ክልል አንድ ፣ ክልል ሁለት፣ ክልል ሦስት…  የሚል መጠሪያ ወደ ተሰጣቸው ክልሎች ሲወርዱ “ቢሮ” የሚል አዲስ ስያሜ አገኙ:: እናም እንደ ጤና ቢሮ፣ ግብርና ቢሮ እና ትምህርት ቢሮ… ሁሉ ክልል ሦስት ማስታወቂያ ቢሮ በሚል መጠሪያ ነው ፅንሰቱ::

ከዚህ ምስረታው በኋላ ቢሮው ከባህል እና ቱሪዝም ቢሮ እንዲዋሃድ በተደረገ ጊዜ “ባቱማ” ተብሎ፣ እንደገና ራሱን እንዲችል ሲደረግ ደግሞ አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጀት /አብመድ/ በሚሉ ስያሜዎች ሲጠራ ከቆየ በኋላ ወደ ኮርፖሬት ባደገበት በዚህ ዘመን ደግሞ እነሆ “አሚኮ” ወደ ተሰኘው መጠሪያ ተሸጋግሯል::

አሚኮ ያፈራረቀው መጠሪያውን ብቻ አይደለም፤ ዛሬ የሚጠቀምበት የሚዲያ ኮምኘሌክስ ዘመናዊ ህንፃ ባለቤት ከመሆኑ በፊት ከኢዜአ ጋር  ተዳብሎ የቢሮውን መሠረት የጣለበትን የትውስት ባለ ሁለት ክፍል ጽ/ቤት ጨምሮ በአምስት መንግሥታዊ እና አንድ የግለሰብ መኖሪያ ቤት በመከራየት ሲሰራ ከቆየ በኋላ እነሆ ዛሬ በክልሉ  ስድስት ከተሞች እና አዲስ አበባ ላይ ሰባት ደረጃቸውን የጠበቁ የሚዲያ ህንፃዎችን ለመገንባት በቅቷል፤

እየገነባም ይገኛል::

መንግሥት በሾማቸው የመጀመሪያው ቢሮ ኃላፊ እና ፀሀፊያቸው “ሀ” ብሎ ህልውና ያገኘው የያኔው ማስታወቂያ ቢሮ ክልሉን ሥራ እንዲያስጀምሩ እና እንዲያጠናክሩ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መድቦ ከአደስ አበባ በላካቸው ደርዘን የማይሞሉ ጋዜጠኞች እና የአስተዳደር ሰራተኞች ነው መደበኛ ተግባሩን የጀመረው- ዜና እየሰራ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ በስልክ በመላክ::

በዚህ መንገድ በጥቂት የሰው ኃይል፣ በደባል ቢሮ ውስጥ፣  መቶ ሺ በማትሞላ ዓመታዊ በጀት፣ በትውስት (የልመና) የሬዲዮ ማሰራጫ ጣቢያ በሥልክ ዜና በማቀበል የተጀመረ ተግባር እነሆ ዛሬ ለሽልማት የበቃ ግዙፍ ተቋም ለመሆን ችሏል::

የግዝፈቱ እና ሽልማቱ መንስኤ ደግሞ ትጋቱ ነው- የ30 ዓመታት ያልታከተ ትጋት:: ገና በተመሠረተ በሁለት ዓመታት ውስጥ ራሱን በሰው ኃይልና ቁስ አደራጅቶ የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ውይይት እና ውሳኔዎችን ለህዝብ ያደረሰባትን በክልል ደረጃ ቀዳሚ እና የመጀመሪያ የሆነችውን በኩር ጋዜጣ አሳትሞ በማሰራጨት በራሱ “ሚዲያ” ህዝቡን የመረጃ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባሩን ጀመረ- ህዳር 7/1987::

ከሁለት ዓመታት በኋላም  “ይህ የአማራ ድምፅ ነው!” በሚል  የጣቢያ መለያ ድምፅ ወደ ህዝብ የደረሰውን የአማራ ራዲዮ አቋቋመ – ግንቦት 16/1989 ዓ.ም:: ትጋቱ አልበረደም፤ ከሦስት ዓመታት ዝግጅት  በኋላ ደግሞ የአማራ ቴሌቪዥን ስርጭት በቴሌቪዥኖቻችን መስኮት ላይ ቦግ አለ -1992 ዓ.ም::

ባለሰፊ ራእዩ አሚኮ  ጋዜጣ፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የምንላቸውን መደበኛ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤት በመሆኑ ብቻ ረክቶ የሚቆም አልሆነም፤ በኩር ጋዜጣን ወደ በኩር መጽሔት ጭምር አሳደገ፤ ዘመን የወለደውን ኤፍ ኤም ፌዲዮ በባ/ዳር ኤፍ ኤም 96 ነጥብ 9 የአየር ሞገድ “አንድ!” ብሎ ሸዋን፣ ወሎን፣ ጐንደርን፣ ጐጃምን እና አዲስ አበባን የየራሳቸው ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት እንዲሆኑ  አደረገ፤ ሰቆጣ ላይም የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ገነባ::

የማይገታው የአሚኮ ትጋት ዘመን በፈጠራቸው የማህበራዊ የብዙሃን መገናኛ በሁሉም አማራጮች ወደ ህዝብ በመድረስ በክልሉ ለሚኖሩ የኽምጣና፣ የኦሮሞኛ፣ የአዊኛ እና አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚዲያ አገልግሎት በማበርከት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ “አሚኮ ህብር የተሰኘ” 2ኛ “የቴሌቪዥን ቻናል” በመክፈት እንግሊዝኛን እና አረብኛን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች መረጃዎቹን ለህዝብ የሚያደርስ ኢትዮጵያዊ ብቸኛ ተቋም ለመሆን በቃ::

ይህ ሁሉ የሆነው የክልሉ መንግሥት በበጀተው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተቋማቱን ገንብቶ፣ በዘመናዊ ቁስ አደረጅቶ፣ በሁለት ሰው የተመሰረተውን ተቋም ወደ 850 ሰራተኛ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን በትምህርት እና ስልጠና ጭምር አብቅቶ፣ አመታዊ በጀቱንም በመቶ ሚሊዬኖች መድቦ ነው::

እስካሁን ያየነው የአሚኮን ቁመና ነው:: ለመሆኑ የአሁኑ አሚኮ፣ የያኔው ማስታወቁያ ቢሮ የተቋቋመበት ዓላማ እና ግብ ምንድ ነው? አተገባበሩስ?

የ30 ዓመታት ጉዞን በአንዲት ገፅ መቀንበብ “ዓባይን በጭልፋ” አይነት ይሆናል እና በዓሉን ለመዘከር ያህል ተልእኮውን ከመወጣት አንፃር ጉልህ ከምንላቸው ተግባራቱ ጥቂቱን በወፍ በረር እንይ::

አሚኮ በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት የተቋቋመ የክልሉ  ህዝብ እና መንግሥት መገናኛ አውታር ነው፤ ተጠሪነቱ ደግሞ የክልሉ ህዝብ እንደራሴ ለሆነው የክልሉ ምክር ቤት ነው::

በዚህ መሰረታዊ ምክንያት የሚያገለግለው የክልሉን ህዝብ እና መንግሥት መሆኑ ተፈጥሯዊ ግዴታው ይሆናል::

በዚህም መሰረት የክልሉን ህዝብ የመረጃ ፍላጐት ማሟላት፣ በህዝብ እና መንግሥት መካከል እንደመገናኛ ድልድይ ሆኖ ማገልገል፣ ህዝቡ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ፓለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ መረጃዎች እንዲያገኝ፣ ግንዛቤ እና እውቀቱ እንዲዳብር፣ የድህነት መውጫ መንገዶችን እንዲማር፣ ኑሮውን የሚለወጡ አዳዲስ አሰራሮችን እንዲገበይ፣ ከተጠባቂ እና ያንዣበቡ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ፣ እንዲጠበቅ መብት እና ግዴታዎቹን እንዲያውቅ ህግ፣ ደንብ እና መመሪያዎችን ተፈፃሚ እንዲያደረግ፣ ባህል እና ትውፊቱን ጠብቆ በስነምግባር እንዲታነፅ፣ በሽታን እንዲከላከል ጤናውን እንዲጠበቅ፣ እንዲማር፣ ሀገሩን እንዲወድ ከጠላት እንዲከላከል እና በመሳሰሉት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እንዲያገኝ እያዝናና መረጃ መስጠት እና ማስተማር ዋነኛ ተልዕኮዎቹ ናቸው::

አሚኮ እነዚህን ተለዕኮዎች ሲያሳካ የክልሉን ሁለንተናዊ እድገት በማፋጠን ረገድ የበኩሉን  ድርሻ ይወጣል፤ የክልሉ ህዝብ በልፅጐ የማየት ራዕዩንም ያሳካል::

ይህንን ከመተግበር አንፃር ያለፉትን 30 ዓመታት የአሚኮ አፈፃፀም ስንገመግም ታዲያ ድርጅቱ ከሞላ ጐደል ስኬታማ እንደነበር አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል:: እንደ አብነት በጤናው ዘርፍ ክልሉን እና ሀገሪቱን ከፈተኗቸው ችግሮች ዋነኛውን የኤች አይቪ ኤደስ ችግር በመቆጣጠር ረገድ የሚዲያው አስተዋፅኦ ባይታከልበት ኖሮ ካጣነው ዜጋ በላይ ዋጋ እንከፍል እንደነበር መጥቀስ ብቻ በቂ አስረጅ ነው::

በኮረና፣ በወባ፣ በኮሌራ፣ በአተት ወረርሽኞች ወቅት በሚድረግ ቅደመ ማስጠንቀቂያ መረጃም እንዲሁ::

ከጤናው ባሻገር ድንገት ደራሽ የጐርፍ አደጋ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ግሪሳወፍ እና ተምች የመሳሰሉ አውዳሚ ወረርሽኞች  ሊከሰቱ እንደሚችሉ ሳይንሳዊ ትንበያዎች ሲያረጋግጡ ወደ ህዝብ እንዲደርስ በሚሰጠው መረጃ የመከላከል ቅድመ ዝግጅቶች በመደረጋቸው ይከሰቱ የነበሩ ኢከኖሚያዊ እና የህልውና አደጋዎች መከላከልም ችሏልና ሳይጠቀስ የማይታለፍ የድርጅቱ ስኬት ነው::

የልማት ዘርፍን ብንገመገም ግብርና መር ኢኮኖሚ እንደመከተላችን የአርሶ አደሩን የአመራረት ስልት የሚያዘምኑ አዳዲስ አሰራሮችን በማስተዋወቅ፣ መልካም ተሞክሮዎችን ወደ ብዙሃኑ በማሸጋገር፣ ሥራ ፈጣሪዎችን፣ ኢንቨስተሮች፣ ማህበራትን እና ሞዴል ፈፃሚዎችን እውቅና እንዲያገኙ፣ ለሌሎችም ተነሳሽነት እንዲፈጥሩ በማድረግ በኩል የምርት እድገት እንዲጨምር አድርጓል::

የክልሉን የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች በማስተዋወቅ፣ እንደ አውራአምባ ማህበረሰብ ያሉ አዳዲስ የአሰራር ባህል እና ልማዶች ወደ ሰፊው ህዝብ በማዳረስ በኩልም ትልቅ ድርሻ ነበረው::

የሴቶችና ህፃናት መብቶች እንዲከበሩ፣ ልዩ ፍላጐት ያላቸው ዜጐች ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ለአካባቢ ጥበቃ በየአመቱ የማያቋርጥ የዘመቻ ልማት እንዲከናዎን ወ.ዘ.ተ በማድረግ በኩልም ግምባር ቀደም ነበር::

ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገር አደጋ በሚጋረጥባት ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገር ሉዓላዊነት በጋራ እንዲቆም በመዘመር በኩል ሁሌም እንደ ወታደር በተጠንቀቅ የሚቆም እና በግንባር ቀዳሚነት የሚገኝ ተቋም እንደነበር በየዓውደ ክስተቶቹ ላይ የተገኘ ሁሉ  የሚመሠክረው እውነት ነው::

በዚህ ወሳኝ ተግባሩም ነው አሚኮ ለአገር አቀፍ እውቅናና ሽልማት የበቃው። እናም ዛሬም፣ ነገም፣ ሁሌም ለኅብረተሰብ ለውጥ መትጋቱን ይቀጥላል::

(ጌታቸው ፈንቴ)

በኲር የነሐሴ 19  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here