48 ሺህ 929 ተማሪዎች አልፈዋል – ትምህርት ሚኒስቴር

0
75

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ መስከረም 04 ቀን 2018 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መግለጫ ሰጥተዋል። በሰጡት መግለጫም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ በሚገኘው ከስርቆት የፀዳ የተማሪዎች የፈተና አሰጣጥ ሂደት ዘንድሮ ከፍተኛ መሻሻሎች መታየታቸውን ገልጸዋል። እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ አንድ ሺህ 249 ትህርት ቤቶች ዘንድሮ ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ሲሆን 50 ትምህርት ቤቶች ደግሞ መሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን አሳልፈዋል።

የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በዚህም በ2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ፈተናውን ከወሰዱት 585 ሺህ 882 ተማሪዎች መካከል 48 ሺህ 929 (ስምንት ነጥብ አራት) በመቶ ያህሉ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት በማስመዝገብ አልፈዋል ብለዋል። ባለፈው ዓመት ለሀገር አቀፍ ፈተና ከተቀመጡ 684 ሺህ 372 ተማሪዎች ውስጥ 36 ሺህ 409 ወይም አምስት ነጥብ አራት በመቶ ማለፋቸውን አስታውሰዋል።

በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ረገድ በተፈጥሮ ሳይንስ ትልቅ ውጤት መመዝገቡን አስታውቀዋል። በዚህም ከ600 ከፍተኛ ውጤት የተገኘው 591 መሆኑን ገልፀዋል። በማኅበራዊ ሳይንስም ከፍተኛው ውጤት 562 ሆኖ መመዝገቡን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ፈተና የወሰዱት 585 ሺህ 882 ተማሪዎች ሲሆኑ 308 ሺህ 66ቱ ወንዶች  እንዲሁም 277 ሺህ 816 ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here