ኢትዮጵያ ከልዕልናዋ ዝቅ ያለችበት መድረክ
ነሀሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም
በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ከተሳተፉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ሀገራችን በ33ኛው ኦሎምፒያድ 34 አትሌቶችን በሁለት የስፖርት ዓይነቶች ማሳተፏ አይዘነጋም። በአትሌቲክስ እና በውሃ ዋና ስፖርት ኢትዮጵያ በ33ኛው መድረክ የተሳተፈችባቸው የስፖርት ዓይነቶች ናቸው።
በቅርቡ በተጠናቀቀው የፓሪሱ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንድ ወርቅ፣ እና ሦስት ብር በድምሩ ከአራት ሜዳሊያዎች ጋር ተመልሰዋል። በወንዶች የማራቶን ውድድር ታምራት ቶላ አዲስ ክብረወሰን በማስመዝገብ ጭምር የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ አምጥቷል። ታምራት ቶላ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜ ሁለት ስዓት ከስድስት ሴኮንድ ከ26 ማይክሮ ሴኮንድ ነው።
በፈረንጆች ሚሊኒየም በሲዲኒ ኦሎምፒክ በማራቶን ውድድር አትሌት ገዛህኝ አበራ ለመጨረሻ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ካሸነፈ በኋላ በርቀቱ የታምራት ድል የመጀመሪያው ነው። በሴቶች ማራቶንም አትሌት ትዕግስት አሰፋ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በወንዶች ዐስር ሺህ ሜትር ርቀት በሪሁ አረጋዊ የብር ሜዳሊያ አስመዝግቧል።
በ800 ሜትር ሴቶች ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ ገብታ ያጠናቀቀችበት ነው። አትሌት ጽጌ ዱጉማ የብር ሜዳሊያ በማምጣት ለሀገሯ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ችላለች። ከቤንሻንጉል ጉምዝ የተገኘችው ይህቺ ድንቅ አትሌት፤ ኢትዮጵያውያን በአጭር እና በመካከለኛ ርቀት ተፎካካሪ መሆን አይችሉም የሚለውን እሳቤ እና ግምት ፉርሽ አድርጋለች።
በአጠቃላይ ግን በፓሪሱ ኦሎምፒክ ልክ እንደ ቶኪዮ ኦሎምፒክ ደካማ ውጤት የተመዘገበበት ነው። ከአትሌቶች ምርጫና ዝግጅት ጀምሮ ከፍተኛ ውዝግብ ሲነሳበት የነበረው አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ እና ኦሎምፒክ ኮሚቴ በፓሪስም በአትሌቶች እና በአሰልጣኞች ቅሬታ አስነስቷል።
ለወትሮ በኦሎምፒክ ዝግጅት በተለይ ደግሞ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ዓለም በጉጉት ከሚጠብቃቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች- ሀገራችን። ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ታሪክ ውስጥ እስካሁን 15 ጊዜ ተሳትፋለች። በእነዚህ ጊዜያት 62 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። ከእነዚህ መካከል 24 ወርቅ፣ 15 ብር እና 23 የነሐስ ሜዳሊያዎች ይገኙበታል። ኢትዮጵያ ከተሳተፈችባቸው የኦሎምፒክ መድረኮች ሁሉ በፈረንጆች ሚሊኒየም በተደረገው የሲዲኒ ኦሎምፒክ የተመዘገበውን ውጤት ያህል እስካሁን አልተመዘገበም።
በሲድኒ ኦሎምፒክ አራት ወርቅ፣ አንድ ብር እና ሦስት የነሐስ በድምሩ ስምንት ሜዳሊያዎችን ሀገራችን ያስመዘገበችበት ወቅት እንደነበር የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። ከፈረንጆች ሚሊኒየም ወዲህ በተለይ በሪዮ፣ በቶኪዮ እና በፓሪስ ኦሎምፒኮች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶች ዝቅ ብለዋል። ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሎምፒክ አንድ ወርቅ፣ ሁለት ብር እና አምስት ነሐስ ማስመዝገቧ አይዘነጋም።
ታዲያ በእነዚህ ሦስት ተከታታይ ውድድሮች የኢትዮጵያን ልዕልና የማይመጥን ውጤት በመመዝገቡ፣ ውዝግቦች አልጠፋባቸውም፣ የስልጠና መንገድ ላይም የበዛ ጥያቄ እንዲነሳባቸው አድርገዋል። የአሠራር ስርዓት መጓደል እና መርህ መጣስ፣ የመዋቅር ችግሮችም አሉባቸው ተብሏል።
አትሌቶችን መምረጥ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ኃላፊነት ቢሆንም ኦሎምፒክ ኮሚቴው እጁን አስገብቷል። አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ፅጌ ገብረሰላማ፣ ሱቱሜ ታደሰ እና ሂሩት መሸሻ ከውድድሩ በፊት በአትሌቶች ምርጫ ቅሬታ ከነበራቸው አትሌቶች መካከል እንደነበሩ ይጠቀሳል።
አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ በአንድ ሺህ 500፣ በአምስት ሺህ እና ዐስር ሺህ ሜትር ርቀቶች እንድትወዳደር የተፈቀደው የፍሬወይኒ ኃይሉ ዕድል ተዘግቶ እንደሆነ አይዘነጋም። አትሌት ጉዳፍ ምንም እንኳ ድንቅ አትሌት መሆኗን ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ብታሳይም በፓሪስ ኦሎምፒክ ግን ደካማ አቋም ነው ያሳየችው።
በወንዶች ማራቶን ውድድር ቀነኒሳ በቀለ፣ ዴሬሳ ገለታ እና ሲሳይ ለማ ነበሩ፤ በፓሪሱ መድረክ ሀገራችንን እንዲወክሉ የተመረጡት። ታምራት ቶላ ደግሞ በተጣባባቂነት ተይዞ እንደነበር አይዘነጋም። ቀኑ ሲቃረብ ግን አትሌት ሲሳይ ለማ በጉዳት ምክንያት ከማራቶን ቡድኑ ራሱን አግሏል። በምትኩም ተጠባባቂ የነበረው ታምራት ቶላ እንዲሳተፍ በደብዳቤ ለኦሎምፒክ ኮሚቴው አሳውቋል። ተጠባባቂ የነበረው ታምራት ቶላም ለሀገራችን ብቸኛውን ወርቅ ይዞ ከፓሪስ አዲስ አበባ ገብቷል። ይህም የአትሌቶች ምርጫ ትክክል አለመሆኑ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ተገፍቶ በተደረገው የቶኪዮ ውድድር ሀገራችን አንድ ወርቅ፣ አንድ ብር እና ሁለት ነሐስ ይዛ መመለሷ አይዘነጋም። በቶኪዮ ኦሎምፒክ ብቸኛው የወርቅ ሜዳሊያ ያገኝችው በአትሌት ሰለሞን ባረጋ አማካኝነት ነው። በለሜቻ ግርማ ብር፣ በለተሰንበት ግደይ እና ጉዳፍ ፀጋዬ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ መገኝቱ የሚታወስ ነው። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ እና ኦሎምፒክ ኮሚቴው አለመግባባት ምክንያት፤ የአትሌቶች ምርጫ እንደነበር አይዘነጋም። አትሌቶች ለኦሎምፒክ የሚመረጡበት መስፈርት ወረቀት ላይ ቢሰፍርም ሁለቱ ተቋማት ግን ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ አለመሆናቸው ውዝግቦችን አስነስቶ እንደነበር አይዘነጋም። በውጤቱ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ አልፏል።
ከአራት ዓመታት በፊት ከተፈጠረው ውዝግብ ያልተማሩት እነዚህ ተቋማቱ እና አመራሮች ዘንድሮም ኦሎምፒኩ ሊጀመር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት አዲስ የውዝግብ አጀንዳ በአትሌቶች እና አሰልጣኞች ዘንድ እንዲከፈት አድርገዋል። አሰልጣኞች የሚያሰለጥኗቸውን አትሌቶች ጥቅም ለማስከበር የሚሄዱበት መንገድ ሽኩቻን ፈጥሮ ሀገራችንን ዋጋ አስከፍሏታል።
ኦሎምፒክ እና ዓለም ሻምፒዮና በደረሰ ቁጥር የማያባራ ውዝግብ እየተፈጠረ ኢትዮጵያውያን የሚሸማቀቁበት ሆኗል። ይህ ደግሞ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ እና ኦሎምፒክ ኮሚቴው ደካማ እና መርህ አልባ አሠራር የመነጨ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል።
ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ሦስት ተከታታይ በኦሎምፒክ መድረኮች በአትሌቲክሱ ዘርፍ እንደ ታሪኳ ማደር ተስኗት ታይታለች። በደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝ የሆኑት አማረ ሙጬ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አትሌቲክሱ ላይ አሁን የሚታየው ለሀገር ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ ሳይሆን ግለሰብ ተኮር መሆኑን ይናገራሉ።
የቡድን መንፈሱ ጥሩ አለመሆን እና የሚመለከታቸው አካላት የኦሎምፒክ ቡድኑን በሚገባ መቆጣጠር አለመቻላቸው በውጤቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፎ አልፏል። ኢትዮጵያ በ33ኛው ኦሎምፒያድ ውጤት ካጣችባቸው አስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት ባሻገር የአትሌቶች የታክቲክ ችግርም እንደንደነበር አሰልጣኝ አማረ ተናግረዋል።
የአጨራረስ ችግር አትሌቶችን ዋጋ ያስከፈለ ሌላኛው ችግር ነው። ትንፋሽን ሰብስቦ የመጨረሻዎቹን መቶ እና ሁለት መቶ ሜትር ርቀት ፈጥኖ መውጣት ሌሎችን አሸናፊ ያደረገ ታክቲክ ነው። በቀደሙት ዓመታት ስንጠቀምበት የነበረውን ይህን የአጨራረስ ዘዴ አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ የተናገሩት አሰልጣኙ፤ ሌሎች ሀገራት ያንን ተግባራዊ በማድረጋቸው ውጤታማ ሆነዋል ብለዋል።
የአሰልጣኞች የእርስ በእርስ ሽኩቻ እና አለመግባባት ችግሩ አትሌቶች ላይ አለፍ ሲልም ቡድኑ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፎ አልፏል። አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ላይ የተወሳሰበ ችግር እንዳለ የጠቆሙት አሰልጣኝ አማረ ሙጬ፤ ከወዲሁ መፍትሄ ካላገኝ በቀጣይም ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። አትሌቲክስ የረጅም ጊዜ የሥራ ውጤት በመሆኑ ከወዲሁ ጠንካራ አመራር ሊኖረው ይገባል፤ ባይ ናቸው አሰልጣኙ። የስልጠና እና የውድድር እንዲሁም የአመራር ክፍተት ስላለ ይህ በጊዜ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል፤ የአሰልጣኙ አስተያየት ነው።
ኢትዮጵያ ለአትሌቲክስ ስፖርት የማይነጥፍ የተፈጥሮ ፀጋ ያላት ሀገር ናት። በየ ርቀቱ እንደ አብሪ ኮከብ የሚወረወሩ አትሌቶች የሚፈለፈሉባት ሀገር ጭምር ናት። ይሁን እንጂ ዛሬም በቆየው ባህላዊ የስልጠና ሂደት እና አስተሳሰብ መመራታችን ዓለም ከደረሰበት የስልጠና መንገድ ለመጓዝ በብዙ ወደ ኋላ ቀርተናል።
ከዚህ በፊት ነጮች በአትሌቲክሱ ዘርፍ ኢትዮጵያውያንን፣ ኬኒያውያንን፣ ዩጋንዳውያንን እና የመሳሰሉትን ሀገራት አትሌቶችን፤ በገንዘብ በማስኮብለል ነበር ውጤታማ ሲሆኑ የሚስተዋሉት። አሁን ላይ ግን የስልጠና ደረጃቸውን እጅግ በማዘመን አትሌቶቻቸው ከምስራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች ቀድመው እንዲታዩ ሲያደርጉ እኛ ግን ባለንበት ተቸክለን ቀርተናል።
ታዲያ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተቋማዊ ለውጥ፣ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፣ የስልጠና መንገዱን እንደገና ማጤን እና ሳይንሳዊ መንገድን መከተል እንደሚገባ ባለሙያው ምክረ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም