63 ዓመታት መድረክ ላይ…

0
185

ፈጣሪ የእድሜ ጸጋ ሰጥቷቸው በሕይወት ካሉት ቀደምት የ1930ዎቹ ትውልድ ግዙፍ ዋርካ አንዱ ነው። ዘንድሮ 84 ዓመቱ ነው። ከጥላሁን ገሰሰ ጎን ለጎን ወይም ቀጥሎ የሚጠቀስ ተወዳጅ ዘፋኝ ነው። በዓለም መድረክ ከፍተኛ ዝና ካላቸው ዘፋኞች ቀዳሚው ነው። 63 ዓመታትን በሙዚቃ ቀጥሎ ከሰሞኑ ስንብት እና ምስጋና እየተደረገለት ይገኛል። እስኪ ስለማህሙድ እናውራ።

ከደሀ ቤተሰብ መወለድ ለዝነኛ ሰዎች ብርቅ አይደለም፤ የትዝታው ንጉሥም ዝቅተኛ ገቢ ከነበራቸው ቤተሰቦች ነው የተወለደው። አዲስ አበባ መርካቶ ውስጥ አሜሪካን ግቢ የሚባል ሰፈር 1933 ዓ.ም ተወለደ። ትምህርት ቤት ቶሎ አልገባም፤ ዘጠኝ ወይ ስምንት  ዓመት ሲሆነኝ ገባሁ ይላል ማህሙድ። የመርካቶ ልጅ ሆኖ ደሀ መሆን ቅድሚያ ከገንዘብ ጋር መጨባበጥን ያስገድዳል። መርካቶ የሥራ ቦታ ነው። ከሁለት ሃይማኖት ተከታዮች የተገኘው ማህሙድ በልጅነቱ ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ ነበር። ከቄስ ትምህርቱ በፊት ደግሞ የሙስሊም ትምህርት ቤት ተምሯል።

አባቱ ግሪክ ክለብ ውስጥ ይሰሩ ነበርና በልጅነቱ አትክልት በመንከባከብ እና ውኃ በማጠጣት ያግዛቸው ነበር። በ15 ዓመት ዕድሜው የግሪክ ክለብ መዘጋቱ አባቱ ስራ ፈት እንዲሆኑ አደረጋቸው። ያን ጊዜ ነው የበለጠ ቤተሰብን የማስተዳደር፤ ገንዘብ የማምጣት ኀላፊነት ትክሻው ላይ የወደቀው። እናቱ ጉሊት ቁጭ ብለው እንጀራ ይሸጣሉ፤ እሱም ይህን ያግዛቸው ነበር። ወደ ጫካ ሄዶ  ለእንጀራ መጋገሪያ ማገዶ እንጨት እና ጭራሮ ለቅሞ ያመጣ ነበር። በዚህ ሁኔታ ከትምህርት ጎን ለጎን ለስድስት ዓመታት ቀጠለ።

የሊስትሮ ስራም ጀመረ። ማህሙድ አህመድ በታህሳስ 2005 ዓ.ም ከቁም ነገር መጽሔት ጋር ባደረገው ቆይታ “ከጓደኞቼ መካከል ሰነፉ ተማሪ እኔ ነበርኩ” ሲል ተናግሯል። ቤተሰብ ለማስተዳደር ገንዘብ ለመሥራት ይሯሯጥ ስለነበር ትምህርቱ ዋና ትኩረቱ አልነበረም። በትምህርቱ ብዙም አልቀጠለም። ከስምንተኛ ክፍል በላይ አልተማረም።

ሙዚቃ በሰው ልጅ ውስጥ ያለ ነገር ነው። ጉዳዩ ማን ይጠቀምበታል የሚለው ነው እንጂ። የብዙ ዘፋኞች ታሪክ ውስጥ የእናቶች እንጉርጉሮ እና ዘፈን አድጎ ሙዚቃ ሆኗል። የማህመድ እናትም ማታ ማታ ታንጉራርጉር ነበር። በልጅ ልቦናው እሷን በመስማት ከሙዚቃ ውጪ ሌላ ነገር ማሰብ አልቻለም። ከጠቅል ሬዲዮ የሚተላለፉ ዝግጅቶችን በሬዲዮ ይሰማ ነበር።

በልዩነትም ማክሰኞ እና ሀሙስ የሚተላለፉ የሙዚቃ ግብዣ ዝግጅቶችን ቁጭ ብሎ ይከታተል ነበር።  የወቅቱ ወጣት ድምጻዊያን ካሳ ተሰማ፣ ተዘራ ኀይለ ሚካኤል፣ መቶ አለቃ ኑሩ ወንድ አፍራሽ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ አየለ ማሞ፣ እሳቱ ተሰማ እና ሌሎችም በሬዲዮ ዘፈኖችን በሳምንት ሁለት ቀን በቀጥታ ስርጭት  ያቀርቡ ነበር። ማህሙድ ሊስትሮ እየሰራ እነዚህን ዘፋኞች ያደምጥ ነበር። ሲነጋም ዘፈኖችን ለጓደኞቹ ይዘፍንላቸው ነበር።

ማህሙድ ሊስትሮ በሚሰራበት ጊዜ አርዓያ የሚያደርገው ጥላሁን ገሰሰን ነበር። የኤልቪስ ፕሪስሊን ዳንስ እና ዘፈኖች ይወዳቸው ነበር። የጀምስ ብራውንም አድናቂ ነበር። እንደ ኤልቪስ ፕሪስሊ እግሩን በማንቀጥቀጥ ይደንስ እንደነበርም ያስታውሳል። የማህሙድ ቤተሰቦች ቤት አልነበራቸውም ነበር። የሺ ሐረግ የሚባሉ የጎረቤት ሴት አንዲት ጠባብ ክፍል ቤት ሰጥተዋቸው ይኖሩ ነበር። ከጎረቤት ደግሞ አንድ ግብጻዊ ጠበቃ ይኖር ነበር፤ ያ ጠበቃም “በራስ ኀይሉ ግቢ ውስጥ ቡና ቤት ሊከፍት ነው” መባሉን ማህሙድ ይሰማል።

ማህሙድ ስራ እንዲያሰራው እናቱን አማላጅ ላከ። ቤቱ ሲገነባ ማህሙድ ቀለም በመቀባት እና አናጺ በመሆን ሰርቷል። ያ ምሽት ቤት 1954 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቆ አሪዞና ክለብ በሚል ሥራ ጀመረ። ከግንባታው በኋላም ማህሙድ በዚህ ክለብ ውስጥ የወጥ ቤቱ ረዳት ሆኖ ነበር የተቀጠረው።

አሪዞና ክለብ ውስጥ እሳቱ ተሰማ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ተፈራ ካሳ፣ ታምራት ሞላ፣ አባይ በለጠ እና ሌሎችም ይዘፍኑ ነበር። በጊዜው ማህሙድ አህመድ ወጥ ቤት ውስጥ ሆኖ ይከታተል ነበር፤ በትኩረትም ያደምጣቸው ነበር። ድምጻዊያኑ ዘፍነው ሲቀመጡ ሳንድዊች በሻይ የሚያቀርብላቸው እሱ ነበር።

አንድ ቀን ጥላሁን ገሰሰ እና ሌሎች የክለቡ ዘፋኞች ድሬዳዋ ለሥራ በክብር ዘበኛ በኩል ተልከው ነበርና የምሽት ቤቱ ውስጥ የሚዘፍን ሰው ጠፋ። የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ብቻ በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ ማቅረብ ጀመሩ። የተፈራ ካሳን “አልጠላሽም ከቶ” ዘፈንን ባንዱ በመሳሪያ ብቻ ሲያቀርበው ማህመድ ከወጥ ቤቱ ድንገት ላፍ ብሎ እኔ ልዝፈነው ሲል ጠየቀ።  ቀጭን ወጣት ነበር ማህሙድ፤ ሙዚቀኞችም ሲዘፍን ዓይተውት አያውቁምና ተደናገጡ። “ትችይዋለሽ እንዴ”?  ሲሉ ጠየቁት። ማህሙድ ልሞክረው ብሎ መዝፈን ጀመሩ። በወቅቱ የምድር ጦር ኦርኬስትራ እና የኮንጎ ዘማች ሰራዊት አባላት ቤት ውስጥ ነበሩ። ማህሙድ ዘፈኑን አስደናቂ አድርጎ አቀረበው።

በዘመኑ አንድ የሙዚቃ ሥራ አሪፍ ሲሆን “ቢስ” ይባል ነበር። ይህም ይደገም እንደማለት ነበር። ማህሙድ ቢስ እየተባለ የተፈራ ካሳን አልጠላሽም ከቶ ሙዚቃ   ሦስት ጊዜ ዘፈነው።

ማህሙድ ከመድረክ አልወረደም። የተዘራ ኀይለ ሚካኤልን “ይህም አለ ለካ” ዘፈን አቀረበ። ይህም ዘፈን ቢስ እየተባለ ተደጋገመ። ማህሙድ ከመድረክ ሲወርድ ግብጻዊው የክለቡ ባለቤት “ያ ኣላህ መዝፈን ትችላለህ እንዴ” ብሎ ተገረመበት። ማህሙድ ውስጡ በደስታ ተሞልቶ እሞክራለሁ አለ። “በል ከነገ ጀምሮ ወደ ወጥ ቤት እንዳትመለስ፤ እነ ጥላሁን ከድሬዳዋ እስኪመለሱ እዚሁ ዝፈን” ብሎ ትዕዛዝ ሰጠው። በማግስቱም መርካቶ ወስዶ ሱፍ ልብስ፣ ጫማ እና ሸሚዝ ከተለዋጭ ልብስ ጋር ገዛለት።

ጥላሁን ከድሬዳዋ ሲመለስ ያ ሳንድዊች በሻይ የሚያቀርብለት ቀጭን ወጣት መድረክ ላይ ዘፋኝ ሆኖ አገኘው። ደንግጦ “መዝፈን ትችያለሽ እንዴ?” ብሎ ጠየቀው። ማህሙድ እሞክራለሁ አለው። ጥላሁን ሙሉ የሙዚቃ ግጥም የያዘ ደብተር አምጥቶ ለማህሙድ ሰጠው። በደንብ አጥና ብሎም መከረው። የጥላሁን፣ የተፈራ ካሳ፣ የእሳቱ ተሰማ፣ ዘፈኖችን ማጥናቱን ቀጠለበት። ወጣት ድምጻዊያንን የያዘው የምሽት ክለብ ስራው ተሟሟቀ። ብዙም ሳይቆይ በ1954 እቴጌ መነን በአጋጣሚ ሲያርፉ ሙዚቃ መሰራት አቆመ። ለሦስት ወራት ከባድ ኀዘን ሆነ። በኋላ ቀዳማዊ አጼ ኀይለ ሥላሴ ህዝቤ ኀዘኔን ተጋርተሃል ይበቃሃል ወደ ስራህ ግባ ብለው አወጁ። ክለቡ እንደገና ስራ ጀመረ። ሆኖም ከአራት ወራት በኋላ አሪዞና ክለብ ፈረሰ።

ማህሙድ ወደ ሌሎች ሙዚቃ ክፍሎች ማማተር ጀመረ። ፓሊስ ሰራዊት ሄደ፤ የሙዚቃ ትምህርት ከሌለህ አንቀጥርህም አሉት። ወደ ምድር ጦር ኦርኬስትራ ሄደ። እዛም ደብረ ብርሃን ሄደህ ወታደር ከሆንህ በኋላ ነው በሙዚቀኛነት የምትቀጠረው አሉት። የሙዚቃን ሀሁ  በአድናቆት የጀመረው ማህሙድ ተስፋ ባጣ ስሜት ውስጥ ቀጠለ። አንድ ቀን መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ። የክብር ዘበኛ፣ የጦር ሰራዊት፣ የፓሊስ፣ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሙዚቃ ክፍሎች ለወታደሩ ገቢ ለማሰባሰብ የሙዚቃ ዝግጅት ያሰናዳሉ። በዚህ ዝግጅት ላይ ማህሙድ የሙዚቃ ስራውን አቅርቦ ሕዝቡ ፈርዶ እንዲፈተን ተደረገ። ምርጥ አድርጎ አቀረበ፣ ተጨበጨበለት፣ ሕዝቡ ይለፍ ብሎ ምስክር ሰጠለት።

የክብር ዘበኛ ባልደረባ የነበሩት ሻለቃ ግርማ ሀድጎ “አንተ ልጅ ስማ በወታደርነት እንቅጠርህ ቢሉህ እሺ እንዳትላቸው፤ በሲቪል ቢሉህ እሺ በላቸው” ሲሉ መከሩት። ታህሳስ 15 ቀን 1955 ዓ.ም የክብር ዘበኛ አባል በመሆን በወር 60 ብር ደመወዝ  ተቀጠረ። 11 ዓመታትን በክብር ዘበኛ ሰርቷል።  ሻለቃ ግርማ ሃድጎ ለመጀመሪያ ጊዜ በራሱ ዘፈን እንዲመጣ በር የከፈቱለት ሰው ናቸው። “ካንቺ በቀር ሌላ” የሚለውን ግጥም እና ዜማ ሰጡት፤ ጉሮሮውን በራሱ ዘፈን አሟሸ። “ቅላጼ እና አፍ አከፋፈት ያስተማረኝ ወንድሜ ጥላሁን ነው” ሲል ማህሙድ ያስታውሳል።

ክብር ዘበኛ ሙዚቃን የተማረበት ቤት ቢሆንም ማህሙድ ከ11 ዓመታት በላይ መቀጠል አልቻለም። የሚከፈለው ገንዘብ  ቤተሰቡን ለማስተዳደር አልበቃውም። ራስ ሆቴል ውስጥ አይቤክስ ባንድ ሙዚቃ ያቀርብ ነበር። ማህሙድም እዚያው እየተደበቀ ማታ ማታ ይሰራ ነበርና ገቢው ጣፈጠው። በዚያውም ለመደ። ጠቅልሎ ገባ። በ1966 ማህሙድ ክብር ዘበኛ ሲሰራ ደመወዙ 250 ብር ነበር። በዚሁ ዓመት አይቤክስ ባንድን ተቀላቀለ። አይቤክስ ባንድን ከተቀላቀለ በኋላ የማህሙድ ሕይወት ተሻሽሏል። ዝናውም ጨምሯል።

በድብቅ ይሁን እንጂ ማህሙድ ከአይቤክስ ባንድ ጋር መስራት የጀመረው በይፋ ከመቀላቀሉ  1966ዓ.ም በፊት ሦስት ዓመታትን ቀደም ብሎ ነበር። ከአይቤክስ ጋር ሆኖ ኩሉን ማን ኳለሽ፣ አምባሰል፣ ትዝታ፣ ችቦ አይችልም ወገቧ፣ አልማዝ ምን እዳ ነው የተሰኙት ዘፈኖችንም ብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ስቱዲዮ ተቀዱለት። ሕዝቡ ወደደው።  ጋዜጠኞች ምን አዲስ ዘፈን አቀረብህና ነው ብለው ፍራሽ አዳሽ ሲሉ ጠየቁት። ማህሙድ ግን አሻሽዬ መዝፈኔ ምን ክፋት አለው ብሎ ስራውን ቀጠለበት።

ማህሙድ ዓለም አቀፍ አድማጭ ያለው ግዙፍ ዘፋኝ ነው። ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ እጁን ይዞ ያስገባው ደግሞ ፍራንሲስ ፋልሴቶ ነው። ይህ ሰው የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያጠና፣ ያደነቀ እና ያሳተመ የሙዚቃ አስተዋዋቂ ነው። “መላ መላ” የሚለውን የማህሙድን ዘፈን በሬዲዮ ሰምቶ ነበር ይህ ሰው ማነው ብሎ ተደንቆ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ ያገኘው። ማህሙድ በወቅቱ ራስ ሆቴል ይሰራ ነበር። “አንተ ጋር መስራት እፈልጋለሁ” አለው። ማህሙድ አይቤክስ ባንድን ይዞ ፈረንሳይ፤ ከፍራንሲስ ፋልሴቶ ጋር ሄደ። ፍራንሲስ ፋልሴቶ የማህመድ፣ አስናቀች ወርቁ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ሙሉቀን መለሰ እና ሌሎችንም ተወዳጅ ሙዚቃዎች ኢትዮጲክስ በሚል  ስብስብ አሳትሟል።

የሸክላ ዘመን እንዳለፈ ማህመድ በ1972 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ካሴት አሳተመ። ይህ ካሴት ደራ እና አሽቃሩ የተሰኙ ዘፈኖች የተካተቱበት ነበር። ማህሙድ በርከት ያሉ ዘፈኖችን ለአድማጭ አድርሷል። አንዳንድ እውነተኛ ታሪክ ጋር የተገናኙም ዘፈኖች አሉት። አታውሩልኝ ሌላ፣ እና አልማዝ እንዲሁም አንቺን የሚሉ ዘፈኖቹ ማህሙድ ለሚስቱ አልማዝ ይልማ የተጫዎታቸው ናቸው። አልማዝ የመጀመሪያ ፍቅረኛው ነበረች። ጥላው ውጪ ሀገር በሄደችበት ጊዜ “አታውሩልኝ ሌላ ከእሷ ዜና በቀር፤ አስራኝ ትብትብ አርጋኝ ርቃለች ከሀገር” ብሎ ዘፍኗል። ፍሬው ኃይሉ አንድ ቀን አልማዝዬ የሚል ግጥም እና ዜማ ሰርቶ ለማህሙድ እንዲዘፍን ሰጠው። የማህሙድን ፍቅረኛ የሚያሞግስ ነው።

“የሺ ሐረጊቱ” የሚለው የማህሙድ ሙዚቃ ሌላው ትልቅ ታሪክ የተሸከመ እውነተኛ የፍቅር ታሪክ ነው። የአንድ ወታደር የፍቅር ታሪክ። መቶ አለቃ ፍቅሩ ገብረ ሥላሴ ይባላል። የሺሐረግ ወራሳን  ወደዳት። ቤተሰቦቿ ግን አይሆንም ወታደር አታገቢም ብለው ከለከሏት።  ከሐረር ጦር አካዳሚ ግጥሙን ጽፎ አዲስ አበባ መጣ። ክብር ዘበኛ ገብቶም  ማህሙድ የሚባለው ዘፋኝ ይዝፈንልኝ አለ። ግጥም እና ዜማውን የሰራው ራሱ ባልታሪኩ ወታደር ነበር። ማህሙድ አጠናው ተዘፈነ። በቴሌቪዥን ተሰራጨ።  በኋላም የሺሐረግ ፍቅሩን ማግባት ነው የምፈልገው ብላ አሻፈረኝ በማለት ሁለቱ ተጋቡ። ማህሙድ የመልስ ዝግጅቱ ላይ ዘፈነ። ፍቅር አሸነፈ። ወታደሩ ቀድሞ በዘፈኑ ውስጥ የልጅቱን ስሜት ያውቅ ነበርና “አማረኛ እንዳለሽ አስረጃቸው ውስጡን ተንትነሽ፤ ፍቅሩ አሸንፎኛል መሄድ ነው እረፉት ብለሽ” ሲል ፍቅሩ አንድም የእሱ ስም ሁለትም የኀያሉ ስሜት ፍቅር መገለጫ ነው። እሷም ፍቅሩ አሸንፎኛል ብላ ለወላጆቿ በመንገር ሁለቱ በትዳር ተጣምረዋል።

 

“ስንቱን ደጅ ልጽና ልማድ

ይዤሽ እስክነጉድ፤

የሺ ሀረጊቱ ስሚኝ ፍቅሬ የኔ ዘረ ብዙ

በጨረቃ ይዤሽ እንዳልጠፋ ብዙ ነው መዘዙ፤

እናትሽን ባስጠይቅ ስለ ፍቅር አይገባኝም አሉ

አባትሽ ሰው ብልክ እንደገና በእኔ ያሾፋሉ፤

አማረኛ እንዳለሽ አስረጃቸው ውስጡን ተንትነሽ

ፍቅሩ አሸንፎኛል መሄድ ነው እረፉት ብለሽ፤

አምናለሁ በእናትንሽ በአባትሽ ቤት ጮማ ሰልችቶሻል

አትስጊ ከእኔ ዘንድ  አይገጥምሽም ልብ ይቀርብልሻል”

…    ይቀጥላል

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የታኅሳስ 14  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here