… ካለፈው የቀጠለ
በ2017 ዓ.ም 84ኛ ዓመቱን ስላስቆጠረው ስመገናና አቀንቃኝ ማህሙድ አህመድ የህይወት ታሪክ እና የሙዚቃ አጀማመር ዙሪያ በመጀመሪያው ክፍል፤ ከብዙ በጥቂቱ አስነብበናል። ቀጣዩን እና የመጨረሻው ክፍልም ዛሬ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ!
የትዝታው ንጉሥ
“የትዝታ ዘፈን ስሰማ ቆዳዬ ይነዝራል” የሚለው ማህሙድ በትዝታ ዘፈኖቹ ንግሥና አግኝቷል። ትዝታ የውስጤን የምገልጽበት ዘፈን ነው፤ በጣም የምወደው የዘፈን ዐይነት ነው ይላል ማህሙድ። የትዝታዎች ትዝታ በሚል ርዕስ ትዝታ ወዳጅ እና አዚያሚ ድምጻዊያን ተሰባስበው አልበም ሰርተዋል። በዚህ አልበም ውስጥ ግዙፉ ዋርካ ማህሙድ አህመድ ነው። ጌታቸው ካሳ ይከተለዋል። ሌላኛዋ የትዝታ ንግሥት ደግሞ በዛወርቅ አስፋው አለች። በአጭር የተቀጩት ማዲንጎ አፈወርቅ እና ታምራት ደስታም አሉበት። ጸጋዬ እሸቱ፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ሕብስት ጥሩነህ እና ትዕግስት ፋንታሁን በጋራ ስለ ትዝታ አዚመዋል። ናሆም ሪከርዲንግ በ23ኛ የአልበም ስብስብ ይህንን ዘፈን ሲያቀርብ፤ ኢትዮጵያዊያን ለትዝታ ያላቸውን መብሰልሰል እና ናፍቆት ያጠና ይመስላል። ማህሙድ ከዘፈኖቹ ሁሉ አብልጦ የሚወደው የትዝታ ዘፈኖቹን ነው። ለዚህ ደግሞ ትዝታ የውስጥ ስሜቴን እና ብሶቴን የሚናገርልኝ ስለሆነ ነው ይላል። ማህሙድ በትዝታ ዘፈኖቹ ውስጥ ከፍቅረኛው መለየቱ ያመጣበትን ናፍቆት እና ፍቅር እንደገለጸበት እናያለን።
“ትዝታሽን ለእኔ ትዝታዬን ለአንቺ
የሚሏት ዘፈን ታጫውተኛለች ብቻዬን ስሆን፥
ፍቅርንስ ሸኜሁት ወጥቼ እስከ ደጅ
መውደድን ሸኘሁት ወጥቼ እስከደጅ፥
ማባረር ያቀተኝ ትዝታን ነው እንጂ”
የትዝታ ዘፈን በአንድ በኩል የቁስል ስሜት አለው፤ ውስጥን በማከክ ያስደስታል። ወዳጅ ይመስላል ጠላትም ጭምር ነው። ያብሰለስላል። በዛሬ ላይ ናፍቆትን ጭሮ እድሜን ያባክናል። ለዚህ ነው ማህሙድ ትዝታን ጠላት የሚለው። “በልቼ ርቦኛል ጠጥቼ ጠምቶኛል፤ ሌሊት እየመጣ እንቅልፍ ይነሳኛል፤ ጠላቴ ትዝታን ማን ሰው ያስጥለኛል” ይልና እንደገና መልሶ ደግሞ ፍቅርን ከትቦ የሚያስቀምጥ መልካም ማህደር ያደርገዋል። “ምንኛ ባጠረ እድሜው የፍቅር መዝገበ ቃላቱ ትዝታ ባይኖር” ሲል መልካም ጎኑን ይነግረናል። “ትዝታ ጋረደው” በሚለው ዘፈን የትዝታን ነገር ለፍቅረኛው ለማጫወት ያዜማል።
“ቀን ያላንቺ ሲመሽ ሌቱ በሐሳብ ሲያዝ
ኮቴውን አጥፍቶ ትዝታሽ ሲጓጓዝ፥
ደጁ ሲንኮሻኮሽ ብቸኝነት ነግሶ
ባይተዋሩ ልቤ ሄደ ተመልሶ፥
እህህ ለፍቅር እህህ ለመውደድ
ትዝታ ጋረደው ምነው ያንቺን መንገድ”
ቤት ውስጥ ብቻውን ተቀምጦ ፍቅረኛውን የሚናፍቅን በትዝታ የሚብሰለሰል ሰው በዚህ ዘፈን ውስጥ እናያለን። መጣች ብሎ በኮሽታ የሚደነግጥ፣ ብርዱን ለመቋቋም ፍቅረኛውን የሚሻ፣ እንቅልፍ እምቢ ብሎት ኮከብ የሚቆጥርን ሰው እናያለን።
በ1974 እ.አ.አ የወጣው ትዝታ የሚል ርዕስ ያለው የማህሙድ ዘፈን በትዝታ ምክንያት ረፍት ያጣችን ቃታች ልብ ያሳያል። ሁልጊዜም በልጅቱ እና በእሱ መካከል የነበረን ፍቅር በማስታወስ የሚንገላታን ወጣት በሙዚቃው ውስጥ እናያለን። ኑዛዜው ለተለያት ፍቅረኛው ነው። “ታዝኚልኝ ነበረ ብታይኝ በእውነቱ፤ ከሰውነት ወጣሁ ትዝ ብሎኝ የጥንቱ” ሲል ማህሙድ ድምጹ የማሳዘን ቅላጼ አለው። ውስጡ ብዙ ናፍቆት እና ሐሳብ አለበት። ኑሮ እና ፍቅር። ውስጤስ ብዙ ነገር ነበር፤ እኖር ብዬ በዘዴ ያዝሁት እንጂ ይለናል። ትዝታ ውስጥ ተስፋ አለበት። ትዝታ የትናንት ጊዜ ቢሆንም እንኳን የትናንቱ ፍቅር እርሾ ለነገ መልካም እንጀራ ያስገኛል ብሎ መመኘት አለ። “ሁልጊዜ ከላይ ታች እኔ ምባዝነው፤ የጎደለው ሞልቶ ይሆናል ብዬ ነው” የሚለው ለዚህ ነው።
“ሰው ሁሉ እንቅልፉን ተኝቶ ይልፋል
ልቤ ሰው ቤት ገብቶ መውጫ አጥቶ ይለፋል፥
ጠይም ባየሁ ቁጥር አንቺ ነሽ እያልሁኝ
በጉጉት ርሀብ ተጠብሼ አለቅሁኝ፥
እንደ ምነው አይንሽ ጥቁር እና ነጩ
እንደ ባለስልጣን ፈላጩ ቆራጩ፥
በተልባ እየበላሁ ጮማ እየተመኘሁ
በሽታ ሆንሽብኝ ጤናም አላገኘሁ”
ማህሙድ በዚህ ዘፈን ውስጥ ብዙ ይለፋል። ሐሳቡን፣ ምኞቱን ይናገራል። ሁሉም ግን ድካም ነው። የማይጨበጥ ቅዠት መሳይ ምኞት ነው። እንዲያውም ሰቀቀን እና ናፍቆት የወለደው በሽታ ይመጣበታል በእሷ ትዝታ ምክንያት። “ትዝታሽ ዘወትር ወደ እኔ እየመጣ፤ እፎይ የምልበት ሕይወቴ ጊዜ አጣ” ብሎ የጀመረው ዘፈን ከረፍት ማጣት አልፎ በሽታ ያመጣል።
ማህሙድ ከዚህ በፊት ስለ ትዝታ ዘፍኗል፤ ሌሎችም ዘፍነዋል። ግጥሙም ይሁን ዜማው ረቂቅ ሆኖ የቀረበው ዘፈን በትዝታዎች ትዝታ ውስጥ ያለው የማህመድ ዘፈን ነው ብዬ በስሜቴ እፈርዳለሁ። የሆነ የማላውቀው መንደር፣ ዘመን እና ሁኔታ ውስጥ የሚያስገባኝ ዘፈን ነው። ለማህሙድም በቅንብር ደረጃ የመጨረሻው የትዝታ ዘፈኑ ነው። እድሜውን፣ ያለፈበትን መንገድ፣ ሕይወቱን፣ ትዝብቱን፣ አኗኗሩን እና የዘመን ስንክሳሩን ያስቀመጠበት ነው።
“በትዝታ ቅኝት በሐሳብ ተጉዤ
ይኼው ለዚህ በቃሁ ስንቱን ነገር ይዤ፥
የትውስታን ባህር የናፍቆት ዳገቱን
በትዝታ ብርታት ተሻገርሁት ስንቱን”
ትዝታ ከሕይወት ባህር የሚጨለፍ፣ በጊዜ የሚጠነጠን የጉዞ ክር ነው። በቦታም ይሁን በጊዜ ትዝታ አይሻርም፤ አይቀየርም። ለሰው ልጅ ሁሉ በጋራ የተሰጠች ሀብት ናት። ትዝታ የሌለው ሰው የለም፤ መጥፎም ይሁን ጥሩ ሁሉም ወደ ኋላ ተመልሶ የሚያጠነጥነው ታሪክ አለው። ረጂም ርቀት በሐሳብ ወደ ኋላ ተጉዘን እናስባለን። የትዝታ ስሜት በማጣት እና ብቸኝነት ውስጥ ይገዝፋል። ትዝታ ስዕል እየሰራች ታብሰለስላለች። የስነ አዕምሮ ምሁራን የሰው ልጅ ከ80 በመቶ በላይ ስለ አለፈው ጉዳይ ያስባል ይላሉ። ከዚህ ውስጥም 90 በመቶው ድግግሞሽ ሐሳብ ነው ይሉናል። ትዝታ አታረጅም ሁልጊዜ ሞቃት እሳት ናት። “የናፍቆት እሳቱ ልብ ላይ ቢነድም፥ትዝታ ብትሞቅም አመድ ሆና አታውቅም” የሚላት ማህሙድ ከወጣትነት እድሜ እስከ እርጅና የምትከተል በመሆኗ ነው። ማህሙድ ወጣትነቱን አሳልፎ ዛሬ በእርጅና ዘመኑ ትዝታን ትናንትን ያልረሳች አስታወሽ፤ ዘላለማዊት ሐሳብ ናት ይላታል።
“የክረምት ፀሐይ የበግ ጥላ ናት
ትዝታ መተኪያ አምሳያ እንኳን የላት፥
አይቶ ሲያልፍ የዛሬን ዓይን የፊት ለፊቱን
ትዝታ ብቻ ናት አስተዋይ የጥንቱን፥
የጊዜ መድኀኒት ሐኪም ናት ትዝታ
የተከዙ ሰሞን የተጎዱ ለታ፥
የልጅነት ጊዜን አሁን እየሳለች
የዘላለም ኗሪ ትዝታ ብቻ ነች”
ማህሙድ አህመድ አሁን 84 ዓመቱ ነው። ክብር ዘበኛን በ1955 ተቀላቅሎ ሙዚቃን ጀምሯል። ያለፉትን 63 ዓመታት በሙዚቃ ሕይወት አሳልፏል። ለሙዚቃ ሥራ ከጃፓን እና ብራዚል በቀር ያልሄድሁበት ሀገር የለም የሚለው ማህሙድ በርካታ የዓለም ሀገራት በመዘዋወር ኢትዮጵያን አስተዋውቋል። ከሰሞኑ በአሜሪካ ከሙዚቃው ዓለም የስንብት ዝግጅቶች ተደርገውለታል። ላበረከተው የሙዚቃ አሻራ ምስጋና፣ አድናቆት፣ የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቶታል። ከዚህ ቀደም ብሎም የፈረንሳይ መንግሥት የኦፊሰርነት ማዕረግ ሰጥቶታል። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቶታል። ቢቢሲ ሚዩዚክ አዋርድ ሸልሞታል። በአሜሪካ ቀን በስሙ ተሰይሞለታል። በሀገርም ውስጥ ብዙ ሽልማቶች ተበርክተውለታል።
ሙዚቃ ደግ ነሽ ብሎ በሕይወት የተለዩትን ወዳጆቹን እና የስራ ባልደረቦቹን አስታውሶ ዘፍኗል። አሰፋ አባተ፣ ካሳ ተሰማ፣ ሽሽግ ቸኮል፣ እዮኤል ዮሀንስ፣ ሰይፉ ዮሀንስ፣ ሜሪ አርምዴ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ተፈራ ካሳ፣ ፍሬው ኀይሉን አስታውሷል። ሙዚቃን አንቺ ነሽ ታሪኬ የእኔ መታወሻ እንዳላትም ማህሙድ ይሄው ዛሬም ነገም የሚወሳው በሙዚቃ ስራዎቹ ነው።
ማህሙድ በሙዚቃዎቹ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን ዳስሷል። ፍቅር ሰላም፣ ትዝብት፣ ናፍቆት፣ ትዝታ፣ ዝምታ፣ ጊዜ፣ ዘመን፣ ወዳጅነት፣ ማግኘት፣ ማጣት፣ ሙዚቃ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። ማህሙድ በሰርግ ዘፈኖቹ ጎልቶ የሚታወቅ አንጋፋ አቀንቃኝ ነው። ብዙዎችን ዘፍኖ የዳረ ሰው ነው። በርከት ያሉ ጉራጊኛ ዘፈኖችንም ሰርቷል። ብዙነሽ በቀለ እና ማህሙድ “አያሳየኝ ጭንቁን” ብለው ዘፍነዋል። ተው ዘገየህ እየተባባሉ ማህሙድ እና ሒሩት በቀለ በጋራ ዘፍነዋል። “አደራ” በሚል ደግሞ ማህሙድ እና ጎሳዬ ተስፋዬ ዘፍነዋል።
“ጥላሁንን የሚያክል ዘፋኝ አልተፈጠረም፤ አይፈጠርም” ብሎ የሚያምነው ማህሙድ ከጥላሁን ጋር የወንድምነት ያህል ወዳጅነት ነበረው። የሕይወት ዘመን ወዳጆች ነበሩ። ሁለቱ አንጋፋዎች የምግብ ዓይነቶች እና አባት ደስ ይለዋል የሚሉ ዘፈኖችን በጋራ አብረው ዘፍነዋል።
ዘከሪያ መሀመድ “የጥላሁን ገሰሰ የሕይወቱ ታሪክና ምስጢር” በሚል ባሰናዳው መጽሐፍ ማህሙድ የጥላሁን የሕይወት ባለአደራ እንደነበር ጽፏል። የጥላሁን ልጅ ምንያህል ጥላሁን አንድ ዓመት የሞላው ሰሞን ጥላሁን ማህሙድን ቤቱ ወስዶት ነበር። ከዚያም ጥላሁን ካያቱ ከወይዘሮ ነገዬ አብደላ ጋር ማህሙድን አስተዋውቆት ነበር።
በሌላ ቀንም ወይዘሮ ነገዬ ማህሙድን “ልጄ ቆይ የምነግርህ ነገር አለኝ” አሉት። እርጥብ ሳር ነጭተው ዘለላዎችን በእጁ አስጨበጡት። ቀጥሎም “ልጄ ስማኝ፤ ጥላሁን ወንድም እህት የሌለው ብቸኛ ልጄ ነው። እባክህ አንተ ወንድም ሁነው። አደራህን እንደ ወንድም ሁነህ ጠብቀው” ብለው አደራ ሰጡት። ይህንን ቃሉን ለማክበር ሲል ማህሙድ ጥላሁንን በብዙ ሕይወቱ እና አጋጣሚው ሁሉ ይጠብቀው ነበር። ይህንን አደራ እንደተቀበለ የነገረውም ከዓመታት በኋላ በ1993 ዓ.ም ነበር። ጥላዬ በማለት ነበር የሚጠራው።
ተዘራ ኀይለ ሚካኤል፣ ሃምሳ አለቃ ገዛኸኝ ደስታ፣ የሸዋ ልዑል መንግሥቱ፣ ታምራት አበበ፣ አበበብ ብርሃኔ፣ አበበ መለሰ፣ ይልማ ገብረአብ፣ ተስፋዬ ለሜሳ፣ ግርማ ሃድጎ፣ አየለ ማሞ፣ ተስፋ ለማ፣ ዓለም ፀሐይ ወዳጆ እና ሌሎችም በግጥም እና ዜማ ስራዎች ተሳትፈዋል።
ማህሙድ አህመድ ስለ ትዳር ሕይወቱ ሲያወራ አይሰማም። አልማዝን እንደሚወዳት ከመናገር እና ስለ እሷ ከመዝፈን በቀር። ወይዘሮ እጅጋየሁ በየነን አግብቶ ሦስት ልጆችን አፍርተዋል። በኋላም እሷን ፈትቶ ወደ ቀድሞ ፍቅረኛው አልማዝ ይልማ ሄዷል። እጅጋየሁ በየነ በ1963 በኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ እና ቆንጆ ሴት ነበረች። ማህሙድ ደግሞ በወቅቱ ዝነኛ ዘፋኝ ነበር። ክብር ዘበኛ ውስጥ ስሙ ገናና ሆኗል። እናም እጅጋየሁ በየነ ከሚስቱ ከአልማዝ አፋትታ አገባችው። ይህንንም ራሷ በቅርቡ እግረኛው ሚዲያ ላይ ቀርባ አውርታዋለች።
የፊታችን ጥር ወር ማህሙድ አህመድ ለስንብት ኮንሰርት አዘጋጅቷል፡፡።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም