84 ሺህ ዶላርን በዜሮ ያባዛዉ

0
71

በጃፓን ኪዮቶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የህዝብ መጓጓዣ አውቶቡስ አሽከርካሪ ከተሳፋሪዎች የሰበሰበውን ሰባት ዶላር ወደ ኪሱ በማስገባቱ ከስራው ተባሮ 84 ሺህ ዶላር ጥቅል የጡረታ ገንዘቡ እንዳይሰጠው በፍርድ ቤት መወሰኑን ኦዲቲ ሴንትራል  ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባባ አብቅቶታል::

በ2022 እ.አ.አ የኪዮቶ ማዘጋጃ ቤት የትራስፖርት ቢሮ ባለሙያዎች በከተማ አውቶቡሶች በሾፌሩ ፊት ለፊት ካለው ሰሌዳ ላይ የተገጠመን የቁጥጥር ካሜራ በመፈተሽ ላይ ሳሉ አንዱ ሾፌር ከመደበኛው አሰራር ውጪ 1000 ዬን ወይም ሰባት ዶላር ወደ ኪሱ ሲያስገባ ተመልክተዋል- ስለሁኔታው ሾፌሩን ሲጠይቁት ሊያምንላቸው አልቻለም::

የከተማው ማዘጋጃ ቤት በመጀመሪያ ደረጃ  ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ባደረገው ክርክር  ግለሰቡ ገንዘቡን በታሪፍ ማስቀመጫ ማሽን ውስጥ ማስቀመጥ ሲገባው  ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመውጣቱ እና ድርጊቱን በመካዱ በቢሮው በሰራባቸው 39 ዓመታት የተሰበሰበው የጡረታ መዋጪ እንዲሰረዝ እና ከስራ እንዲባረር ይወሰንበታል::

በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተወሰነበት ውሳኔ ወይም ፍርድ ቅር የተሰኘው ስሙ ያልተጠቀሰው ሾፌር ለይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በማቅረቡ ቅጣቱ ከመጠን ያለፈ ነው በሚል የመጀመሪያውን ውሳኔ ሊሽርለት ችሏል::

በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለ በያዝነው የሚያዝያ ወር መጀመሪያ የጃፓን ጠቅላይ ፍርድ  ቤት የተፈፀመው ድርጊት ህዝቡ በስርዓቱ ላይ ያለውን እምነት ሊያሳጣው፣ ሊሸረሽረው እንደሚችል በመግለጽ ውሳኔውን ወደ ነበረበት ማለትም የጡረታ ገንዘቡ እንዳይሰጠው ወደ ተወሰነበት መልሶታል::

በግዛቱ የሚታተመው “ሚንቺ” የተሰኘው ጋዜጣ የኪዮቶ የትራንስፖርት ጽ/ቤት ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ለሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ምስጋና አቅርቧል::

በመጨረሻም በኪዮቶ የህዝብ ማመላለሻ ጽ/ቤት ባለስልጣን ሺንቺ ሂራይ ለኤ ኤፍ ፒ (AFP) የፈረንሳይ የዜና ወኪል በሰጡት መግለጫ የትራንስፖርት ማጓጓዣ ጽ/ቤቱ የሚወስዳቸው ጠንካራ ውሳኔዎች ተቀባይነት የማይኖራቸው ከሆነ በተቋማቸው ውስጥ ግድ የለሽነት  ነግሶ የህዝብ አመኔታ ሊያሳጣቸው እንደሚችል ነው በማደማደሚያነት ያሰመሩበት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here