ምክክርና ንግግር ለኢንቨስትመንት ዕድገት

0
88

ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኘው የአማራ ክልል ብዙ ዓይነት ስብራቶች ገጥመውታል፡፡ በዚህ ግጭት መካከል ብዙ ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል፣ የጤና ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ክልሉን ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርሱና ተስፋ የተጣለባቸው በርካታ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተቋርጠዋል፡፡

የክልሉ መውጫ መንገድ ትምህርት በ2017 ዓ.ም እንዲመዘገብ በእቅድ ከተያዘው 7 ሚሊዮን ተማሪ ወስጥ እስካሁን ተመዝግበው በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙት ተማሪዎች ቁጥር 2 ሚሊዮን 8 መቶ ሺህ አካባቢ ነው፡፡ ይህም 40 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸው በትውልድ መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት ከወዲሁ ለመገመት አያዳግትም፡፡

ይህንንና መሰል ዘላቂ ጉዳቶችን እያስከተለ ያለውን ግጭት ለማስቆም የክልሉ መንግሥት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ ቢገኝም አሁንም ብዙ አቅም የሚጠይቅ ሥራ ከፊት እንደሚጠብቅ እሙን ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ሁኖ ሥራዋችን እየሰራ ያለው የክልሉ መንግሥት በተለይም ለትውዱ መውጫ መንገድ ለሆነው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ብዙዎችን ከነህልማቸው ያስቀረው ግጭት መጥፎ ጥላ ካጠላባቸው መካከል  ኢንቨስትመንት ዘርፉ አንዱ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ሰላማዊ አማራጮች እንዲፈጠሩ እያከናወነ  ካለው ሥራ ጎን ለጎን የክልሉን የኢንቨስትመንት መዳረሻነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞኗ ኮምቦልቻ ከተማ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ካሉ አካባቢዎች መካከል ትገኝበታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ 124 ፋብሪካዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ ከተማዋ ከንቲባ መሀመድ አሚን የሱፍ ገለጻ ከእነዚህ ውስጥ 57ቱ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች  ሲሆኑ፡ ሌሎቹ በአነስተኛ ደረጃ የሚፈረጁ ናቸው፡፡

የእንደነዚህ ዓይነት ፋብሪካዎች ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባለፈ ሀገርን ከከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እስከ መታደግ የሚደርስ አበርክቶ እየተወጡ ስለመሆናቸው ኮምቦልቻን እንደማሳያነት  መውሰድ ይቻላል፡፡

ከተማዋ ለኢንቨስትመንት የሰጠችው ትኩረት በኢንዱስትሪ መንደርነት እንድትታወቅ ከማድረጉም በላይ ለሀገር ውስጥ ከፍተኛ ተኪ ምርት እየተመረተ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ በዚህም ከውጭ የሚገባውን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተከናወነው ሥራ በ2016 በጀት ዓመት 45 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

በተለይም እንደነዚህ ዓይነት ፋብሪካዎች በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ረገድም ከፍተኛ ሚና ይወጣሉ፡፡ ለአብነትም ባለፈው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከተቻለው ምርት ውስጥ 48 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

በተለይም በሥራ ዕድል ፈጠራ በከተማዋ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከ10 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውም ተመላክቷል፡፡

ኢንቨስትመንትን የዕድገታቸው ምሰሶ አድርገው የሠሩ ሀገራት የተረጋጋ እና ሊገመት የሚችል የንግድ አካባቢን የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አልሚዎችን ለመሳብ እንደ ምቹ አጋጣሚ መጠቀማቸውን የህንዱ ጃዬን ዩኒቨርሲቲ (jainuniversity.ac.in) የመረጃ አውታር አስታውቋል፡፡

ፖለቲካዊ መረጋጋትን መሰረት አድርገው ለኢንቨስትመታቸው ዕድገት አድርገው ተጠቅመዋል፡፡ ይህም ባለሐብቶች በሚያለሙበት አካባቢ እምነት ኖሯቸው በተለያዩ ዘርፎች እንዲሠማሩ የሚያበረታታ ነው፡፡ ይህም የሥራ ዕድል ፈጠራው በዘላቂነት እንዲቀጥል፣ ወጥ የሆነ ምርታማነትን በማረጋገጥ በምርት አቅርቦት ሊያጋጥም የሚችልን የኑሮ ውድነት ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡

ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከርና ሰላማዊ አካባቢን መፍጠር ሀገርን ለባለሐብቶች መዳረሻ ለማድረግ ዋናው መፍትሔ ነው፡፡

ክልሉ ውስጥ ያለው ግጭት በንግግርና በውይይት እንዲፈታ በተለይም የምክክር ኮሚሽን የጀመረውን ተግባር ሁሉም በቀናነትና በባለቤትነት ስሜት በመተባበር እውን እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት፡፡

በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here