ፊተኞች ኋላ

0
118

በኢትዮጵያ የባሕል ስፖርቶች መከናወናቸው ጥሩ ነገር ቢሆንም ስፖርቶቹ ወይም ውድድሮቹ ባሕላዊ ሆነው መቅረታቸው ግን በየትኛውም መስፈሪያ ልክ ሊሆን አይችልም፡፡

በሀገራችን በውድድር መልክ እየተካሄዱ የሚገኙትም ሆኑ  ከውድድር ውጪ ለመዝናኛነት የሚካሄዱት የባሕል ስፖርቶቻችን የተጀመሩበትን ጊዜ አመላካች ሠነዶች የሉም፤ ያም ኾኖ ግን እንደፈረስ ግልቢያ፣ ሠንጠረዥ ጨዋታ፣ ገበጣ፣ ሻህ፣ ቡብ እና የመሳሰሉ ባሕላዊ ስፖርቶቻችን ከተጀመሩ ብዙ አስርት ዓመታት እንዳስቆጠሩ ጠቋሚ መረጃዎች አሉ፡፡

 

በንጉሣዊያኑ የአሥተዳደር ዘመን የኢትዮጵያ ነገሥታት እና እቴጌዎች እንደ ሠንጠረዥ ባሉ ጨዋታዎች የላቀ ክህሎት እንደነበራቸው የታሪክ ድርሳናት እማኝነታቸውን አስፍረዋል፤ በተለይ ደግሞ ሴቶች እንደ ሠንጠረዥ ላሉ የአእምሮ ጨዋታዎች ከወንዶች በተሻለ ውጤታማ እንደነበሩ  እነዚሁ የታሪክ ድርሳናት ከትበዋል፡፡

የፈረስ ግልቢያ በኢትዮጵያ እንደ አንድ የባሕል ስፖርት ይቆጠር እንጂ ፈረስ ለኢትዮጵያዊያን የውድድር ማካሄጃ እንስሳ ብቻ አይደለም:: ኢትዮጵያዊያን የአድዋን ድል ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ጠላቶቻቸውን በመከቱባቸው ደማቅ ታሪኮቻቸው ውስጥ የፈረሶች ሚና የጐላ እንደነበረም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

በቀደመው ዘመን የነበሩት ነገሥታት እና የሀገር አሥተዳዳሪዎች በፈረሶቻቸው ስም እስከመጠራት የደረሱትም ለፈረሶቻቸው ካላቸው ትልቅ ፍቅርና ክብር የተነሳ እንደሆነም ገድሎቻቸው ያወሳሉ:: ለአብነትም አፄ ቴዎድሮስ  አባ ታጠቅ፣ አፄ ዮሐንስ አባ በዝብዝ፣ አፄ ምኒልክ አባ ዳኘው፣ አፄ ኃይለሥላሴ አባ ጠቅል እና ሌሎችም የተለያዩ ነገሥታት የፈረስ ስሞች ነበሯቸው::

በኢትዮጵያ ውስጥ የፈረስ ውድድር በቂ የውድድር መስፈርት ወጥቶለት የማይካሄድ ቢሆንም በተለያዩ ክብረ በዓላት ወቅት የተለያዩ የፈረስ ትርዒቶች እንደሚታዩ እና የሽምጥ ግልቢያ ውድድሮች እንደነበሩ የሚጠቁሙት እርሾዎች በዛ ያሉ ናቸው:: ለአብነትም የአገው ፈረሰኞች ማኀበር በዓመት አንዴ የሚያከናውናቸው የፈረስ ትርዒቶች እና ውድድሮች፣ በደብረ ታቦር የመርቆሪዮስ በዓል ሲከበር የሚከናወኑ የፈረስ ትርዒቶችና ውድድሮች እንዲሁም በኦሮሚያ እና በሌሎችም ክልሎች የሚታዩት ከፈረስ ጋር የተቆራኙ ስፖርቶች፣ የፈረስ ስፓርት በባሕላዊ መልኩም ቢሆን ከተጀመረ ስለመቆየቱ አስረጂዎች ናቸው፡፡

 

የኛው ሀገር የገና ጨዋታ በገና በዓል ሰሞን ብቻ የሚከናወን ባሕላዊ ስፖርት ሆኖ ሲቀር  በአውሮፓዊያኖቹ ዘንድ ግን “ክሪኬት” የሚባል ስያሜን ይዞ በዘመናዊ ስፖርትነት በኦሎምፒክ ውድድሮች ሳይቀር የሚሳተፉበት እና ሜዳሊያዎችን የሚያስመዘግቡበት ስፓርታቸው አድርገውታል፡፡

ሠንጠረዥ፣ ሻህ እና ቡብን የመሳሰሉት ባሕላዊ ጨዋታዎቻችን ዛሬ ላይ “ቼዝ” የሚባለውን ስያሜ ይዞ በኦሎምፒክ ውድድሮች ጭምር ተሳትፎ የሚደረግባቸው ስፓርቶች ሆነዋል፡፡

በኛ ሀገር ለቀደሙት ስፖርቶቻችን “ባሕላዊ ስፖርቶች” የሚል ጐታች ስያሜ ሰጥተን በዓመት አንዴ ብቻ እንደ አውደ በዓል (ፊስቲቫል)  ማከናወናችን ለስፖርቶቹ ወደ ኋላ መቅረት አሳማኝ ምክንያት ሆኗል:: በዚህ ጐታች ምክንያት የተነሳም ቀድመን የጀመርናቸው የፈረስ ስፖርት፣ የገና ጨዋታ፣ ሻህ እና ቡብ (ቼዝ መሰል ባሕላዊ ጨዋታዎቻችን) ባሉበት እየዳከሩ በሌላው ዓለም ሌላ ዓይነት ስያሜ ተሰጥቷቸው እና የመወዳደሪያ መስፈርቶች ወጥቶላቸው ብዙ ሜዳሊያ እና ገንዘብ የሚያሸልሙ ውድድሮች ሆነዋል፡፡

ይህንኑ ጉዳይ ለአማራ ክልል የባሕል ስፓርቶች ፌዴሬሽን ኘሬዚዳንት አቶ አፈወርቅ ተፈራ አንስተንላቸው የባሕል ስፖርቶቻችን ትኩረት የተነፈጋቸው ስለመሆኑ ምላሽ ሰጥተውናል:: “የባሕል ስፖርቶቻችን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካትተው የማይሰጡ በመሆኑና ከታዳጊዎች ጀምሮ ውድድር የማይካሄድባቸው በመሆናቸው ስፖርቶቹ ከመዝናኛነት አልፈው የውድድር ስፓርት  ናቸው  ማለት አይቻልም” ብለውናል፡፡

አቶ አፈወርቅ ተፈራ ለአብነት የትግል ስፓርትን አንስተው ክልላችንን ጨምሮ በሌሎችም ክልሎች ጠንካራ የትግል ስፖርተኞች ቢኖሩም ለስፖርቱ ልዩ ትኩረት ያልተሰጠው በመሆኑ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል:: ከትግል ስፖርት በተጨማሪ የፈረስ ስፓርት ላይም ጠንካራ ሥራዎች ቢሠሩ ሀገራችንን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የሚወክሉ ፈረስ ጋላቢዎችን ማውጣት እንደሚቻልም አንስተዋል፡፡

የፈረስ ስፖርትን ለማዘመን በሀገራችን ጥቂት የፈረስ ስፖርት ማኀበራት (አሶሴሽን) የተቋቋሙ ቢሆንም ማኅበራቱ ጠንክረው ባለመሥራታቸው ስፖርቱን ማሳደግ አልተቻለም፡፡

በሳኡዲ አረቢያ፣ በአሜሪካ እና በሌሎችም የዓለም ሀገራት ትላልቅ የፈረስ ውድድሮች እየተካሄዱ ፈረሶቹ እና ጋላቢዎቻቸው ረብጣ ዶላሮችን ሲዝቁ ማየትም የተለመደ ሆኗል:: ለብዙ ክፍለ ዘመናት ከፈረስ ጋር ቁርኝት ያለን እኛ ኢትዮጵያዊያንስ መቼ ይሆን በፈሶቻችን እና በጋላቢዎቻቸው  ዓለም አቀፍ እውቅናን  የምናገኘው? ብለን መጠየቃችን ፍትሐዊ የሚሆነው በብዙ ምክንያቶች ነው፡፡

የአማራ ክልል የባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ኘሬዚዳንቱ አፈወርቅ ተፈራ ለባሕል ስፓርቶች የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን ቀዳሚው ምክንያት ቢሆንም ለዘርፉ እንደሌሎች ስፖርቶች በጀት ስለማይመደብለትም ስፖርቶቹን እንደስማቸው ባሕላዊ ሆነው እንዲቀሩ አስገድዷቸዋል የሚል ትዝብታቸውን አጋርተውናል፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ በርካታ የባሕል ስፖርት ፌዴሬሽኖች ቢኖሩም ተቀናጅተው ስፖርቶቹን ለማሳደግ ጥረት እንደማያደርጉም ነው አቶ አፈወርቅ የገለፁልን፡፡

“በዓመት አንድ ጊዜ የባሕል ስፖርቶች ውድድር ማካሄድ ለስፖርቶቹ ውድቀትን እንጂ እድገትን አያመጣም” ያሉት አቶ አፈወርቅ ይልቁንም ስፖርቶቹን  በአግባቡ በመከታተል እና በመደገፍ ከስፖርቶቹ ተጠቃሚ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት ይቻላል የሚል ሃሳባቸውንም አጋርተውናል፡፡

አቶ አፈወርቅ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ለባሕል ስፖርቶች የሰጠው ትኩረት በሌሎች አካባቢዎችም መለመድ ያለበት ተግባር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ገበጣ፣ ሻህ እና ቡብን በመሳሰሉ ባሕላዊ ስፖርቶች ላይ ታዳጊዎችን በማሰልጠን እና የውስጥ ውድድር በማካሄድ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የባሕል ስፖርቶች ውድድር ላይ ውጤታማ ስለመሆናቸውም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አብዛኞቹ የባሕል ስፖርቶች በቀደሙት ዘመናት የተጀመሩ ቢሆኑም እስካሁን ድረስ አንዳችም እድገት ሳያስመዘግቡ አሁንም “ባሕላዊ” እየተባሉ መቀጠላቸው ለእድገታቸው ማነቆ ሆኖባቸዋል:: ይህንን ችግር ለመሻገር ለስፖርቶቹ ልዩ ትኩረት መስጠት፣ በጀት መመደብ፣ በርከት ያሉ ውድድሮችን ማዘጋጀት እና ሌሎች ሂደቶችን መከወን ቢያንስ ለስፖርቶቹ መነቃቃት ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሆን ይችላል እንላለን፡፡፡፡

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የሚያዝያ 20  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here