ለአፈሩ ሳይበቃ…

0
131

”አንዳንድ የኢትዮጵያ ሰዓሊዎች አጭር የሕይወት ታሪክ” በሚል በታየ ታደሰ የተሰናዳው መጽሐፍ የሰዓሊ እና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታን ታሪክ በአጭሩ አስፍሯል፡፡

ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ በ1924 ዓ.ም በሐረር ከተማ ነው የተወለደው፡፡ የሰዓሊ ገብረክርስቶስ አባት አለቃ ደስታና የአያቱ  ደብተራ ነገዎ መሠረታቸው ሰሜን ሸዋ ውስጥ በአንኮበር አካባቢ ነው፡፡ አለቃ ደስታ ወደ ሐረር የሄዱትም ልዑል ራስ መኰንን ወልደ ሚካኤልን ተከትለው እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ሁለቱም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ነበሩ፡፡

አለቃ ደስታ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሀይማኖታዊ ትምህርት ሊቅ እና በብራና የእጅ ጽሑፎቻቸው፣በ ባህላዊው ሥዕሎቻቸው የተደነቁ ሰው ነበሩ ይባላል። የብራና ላይ ስዕላትን በመሳል የታወቁ ነበሩ። ገብረ ክርስቶስ ስራውን ከቤተሰቡ ነው የወረሰው። አባቱ እና አያቱን እያዬ ነው ያደገው።  ገብረክርስቶስ እድሜው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ በአዲስ አበባ ኮተቤ እና ዊንጌት ትምህርት ቤቶች ተምሯል።

በተወለደ በስድስት ወሩ ለተለየችው እናቱ  በ6 ዓመቱ “እናትነት” የሚል ስዕል ሰርቷል። ገብረ ክርስቶስ ካደገ በኋላ በአዲስ አበባ ለስዕል በወቅቱ የነበረው አመለካከት ያደገ ስላልነበር የሚፈልገውን ትምህርት በሀገር ውስጥ  ለመከታተል አልቻለም። በ1943 ዓ.ም በቀድሞ ስሙ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲከፈት የመጀመሪያው የሳይንስ ተማሪ በመሆን ነበር የተቀላቀለው፡፡ የግብርና ትምህርትን መማር ጀምሮ ነበር፡፡  ይሁን እንጂ የልቡ መሻት ስዕል ነበርና ሁለተኛ ዓመት ላይ ትምህርቱን አቋረጠ።

ከዩኒቨርሲቲ ከወጣ በኋላ የተለያዩ ስራዎችንም ሰርቷል። በአውራ ጎዳና ባለስልጣን የአፈር ምርምር ባለሙያ ሆኖ ተቀጥሮ  ነበር፡፡ ጥሎት ወጥቶ ቤቱ ተቀመጠ፡፡ ኦጋዴን በሚገኝ የነዳጅ ድርጅት ተቀጥሮም ብዙ አልሰራም፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሒሳብ ባለሙያ ሆኖ ሰርቷል፤ በአዲስ አበባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሆኖም አስተምሯል፡፡

በሁሉም የጀመራቸው ስራዎች ጸንቶ መቆየት አልቻለም፡፡ የሕይወቱን ጥሪ ለማግኘት አምስት ዓመታትን ወስዶበታል፡፡ በኋላም የስዕል ስራው ላይ ብቻ አተኩሮ መስራት ጀመረ፡፡ ስራዎቹን በአዲስ አበባ ለሕዝብ አሳየ፡፡

ገብረ ክርስቶስ በውጭ ሀገር ሥነ ጥበብን ለመማር ከ1949 ዓ.ም ወደ  ጀርመን አቀና፡፡ በዚህም በኮሎኝ የሥዕል አካዳሚ ውስጥ በመግባት ሥዕልና ግራፊክስ አጥንቷል፡፡ በዚያም ከፍተኛ ውጤት በማምጣቱ የስዕል ስቱዲዮ ተበርክቶለት ሥራዎቹን ለሕዝብ ለአንድ ዓመት ያህል አሳይቷል።

ወደ አገሩ ተመልሶም በመምህርነት ሙያ ተሠማርቶ ብዙ የረቂቅ አሳሳል ስልትን መሠረት በማድረግ የተሳሉ ስዕሎችን በአገር ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭ በሚዘጋጁ አውደ ርዕዮች እያቀረበ አሳይቷል፡፡

ከአውሮፓ በተመለሰበት በ1955 ዓ.ም  ገብረ ክርስቶስ የሰለጠነውን ዓለም የስዕል እና ስነ ጽሑፍ ጥበብ ተምሮ ተመልሷል። በተለይም ከዚህ ቀደም ከተለመደው የቤተ ክርስቲያን አሳሳል ጥበብ በተለየ የአብስትራክት (የረቂቅ) ስዕል ስራዎችን በማቅረቡ  ብዙ ነቀፌታዎች እና ትችቶች ቀርበውበታል፡፡ በስዕል ጥበብ ላይ  የሚስተዋሉ አመለካከቶችን  ለማሰተካካል በብዙ ጥሯል።

በ1956 በኢትዮጵያ የስዕል አውደ ርዕይ ያዘጋጀው ገብረ ክርስቶስ ንጉሥ አጼ ኃይለ ሥላሴም እንዲታደሙለት አድርጓል። ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላም በወቅቱ ከፍተኛ ግምት ይሰጠው የነበረውን ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ለማግኘት  የቻለውም በውጪ በቀሰመው ዘመናዊ እውቀት ነበር።

ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ከኢትዮጵያ ውጭ የስዕል አውደ ርዕይ አሳይቷል፡፡ በጀርመን፣ ቼኮዝላቫኪያ፣ ግሪክ፣ ስፔን፣ ጋና፣ ሶቭየት ህብረት፣ ህንድ፣ ብራዚል፣ ሴኔጋል፣ ካናዳ፣ ቤልጅግ፣ ዩጐዝላቪያ፣ ጣሊያን፣ ናይጄሪያ፣ ኮሪያና አሜሪካ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ አንዳንድ የኢትዮጵያ ሠዓሊዎች አጭር የህይወት ታሪክ በሚለው መፅሐፍ ተጽፏል፡፡ ሰዓሊ ገብረክርስቶስ በሙያው ላበረከተው አስተዋፅዖ በ1958 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡

የዘመናዊ ሥዕል ሲነሳ ገብረ ክርስቶስ አብሮ ይነሳል፡፡ አብስትራክት ተብሎ በሚጠራው የአሳሳል ዘዴ ይታወቃል፡፡ ገብረ ክርስቶስ ስዕል  አስተማሪ ነበር።  አንድ ቀን የስዕል ተማሪዎቹን የኢየሱስ ክርስቶስን ስዕል ሰርታችሁ አምጡ ብሎ ያዝዛቸዋል።

ከተማሪዎቹ መሐል አንድ ልጅ ከዚህ ቀደም ከተለመደው ውጪ የክርስቶስን ስዕል በጥቁር ቀለም ስሎ አመጣለት። ተማሪው ክርስቶስ አፍሪካዊ ነው የሚል መነሻ ሐሳብ ነበረው። በዚህ የተገረመው ገብረ ክርስቶስ ተማሪውን ለምን ይህን እንዳደረገ ጠየቀው። “ክርስቶስ  ጥቁር አፍሪካዊ ነው። ፈረንጅ አይደለም። ፈረንጆች ጨካኝ ናቸው” ብሎ መለሰለት።

በዚህ ጊዜ ገብረ ክርስቶስ የኢየሱስ ክርስቶስን ስዕለ  ስቅለት በቀይ ቀለም ሳለው። ከዘር፣ ከነገድ እንዳይወሰን አድርጎ በቀይ (በደም) መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለው።

ገብረ ክርስቶስ ኢየሱስ ክርስቶስ  የሰው ልጆችን ለማዳን ዘር፣ ቀለም፣ አካባቢ፣ ሀብት እና ስልጣን ሳይመርጥ በደሙ አድኗል ሲል ነው በስዕሉ የገለጸው፡፡ ሰዓሊ እና  ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ በስዕሉ ፍቅር ዘር የለውም፤ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ እንጅ የአንድ ወገን አይደለም የሚለውን ሐሳብ አሳይቶበታል። ፍቅር ከቀለም፤ ነገድ እና ማንነት እንደሚሻገር ያሳየበት ብዙ የሚያመራምር እና ረቂቅ ስራው ነው።  ክርስቶስ ሲያድነን ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ አልመረጠም።

የቆዳ ቀለም የሰው ልጆች የመረዳት መጠን እንጂ ያዳነው በደሙ ነው፡፡ ዓለም ሁሉ በማንነት ሊጣላበት አይገባም ሲል የደም መስዋእትነት መክፈሉን ስዕሉ ያሳያል፡፡ ይህ ስዕል ያደገ ፍልስፍናዊ ሐሳብ የተሸከመ ስራው ነው፡፡ በርካታ የስዕል ሥራዎችን ሰርቷል። ደሀ ቤተሰቦች፣ ያፈነገጡ አጥንቶች፣ እናትነት፣ ጎለጎታ እና ሌሎችም ስዕሎቹ ጎልተው ይጠቀሱለታል፡፡

ሌላው የገብረ ክርስቶስ መልክ የግጥም ችሎታው ነው። የሥነጽሑፍ ሐያሲያን ግጥሞቹን አፈንጋጭነት አላቸው። ከተለመደው የግጥም ዝንባሌ የተለዩ ናቸው ይላሉ። ግጥሞቹን ስዕላዊ ናቸው ሲሉ ከስዕል ችሎታው ጋር አገናኝተው የሚተነትኑ አሉ።  ግጥሞቹ ሲነበቡ ምስል የመከሰት አቅም አላቸው።

የገብረ ክርስቶስ ሕይወት ኀዘን የበዛበት ነው። እናቱ በተወለደ  በስድስት ወሩ ነበር የሞተችበት፡፡ አያቱ እማሆይ ብርቅነሽ ሳሳሁ ልክ እንደ እናት  ሆነው አሳድገውታል።  አባቱን በጣም ይወድ ነበር ይባላል። አባቱ ደግሞ በ1956 ዓ.ም በአዲስ አበባ የስዕል አውደ ርዕይ ባሳየበት ሰሞን ሞተበት፡፡ ለአባቱ ብሎ “ረፍት አድርግ አሁን”  በሚል ርዕስ ግጥም ጽፎለታል።

“እንደገና” እና “ሀገሬ” የሚሉት የገብረ ክርስቶስ ግጥሞች ምን ያህል የሀገር ናፍቆት ልክፍት እንደነበረበት ያሳያሉ። መጀመሪያ ለትምህርት ብሎ ሄዶ በተቀመጣባቸው አምስት ዓመታት የደረሰበትን ናፍቆት፤ በኋላም በስደት ከጀርመን ወደ አሜሪካ የሄደበትን ታሪክ እና አኗኗር ብሎም አሟሟት ለሚያውቅ ሰው የኀዘን ስሜት ውስጥ ይከታሉ። ሁለቱ ግጥሞች የሀገር ፍቅር ስሜትን እና ናፍቆትን የተሸከሙ ናቸው። ብቻቸውን ታሪክ የሚሆኑ። ግጥሞቹ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በሚል ርዕስ 252 ገፆች ባሉት መጽሐፍ ታትመውለታል።  ሀገሬ ከሚለው ግጥሙ ቀጣዩን ቀንጭበን እናንብብ።

“ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ

እዚያ ነው አፈሩ የ’ማማ ‘ያባባ

ሳስብ እሄዳለሁ ቢሰበርም እግሬ

አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ

አለብኝ ቀጠሮ

ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ”

ከዚህ ግጥም ሐሳብ እና ከገብረ ክርስቶስ የኪነ ጥበብ አሻራ በመነሳትም ብዙዎች ይህን ሰው ለሀገሩ አፈር እናብቃው ብለው ስራ ከጀመሩ ዓመታት አልፈዋል። እንደቃሉ፣ እንደ ምኞቱ  ባይሆንም ቢያንስ አጽሙን በሀገሩ እንዲያርፍ ከአሜሪካ ለማምጣት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አሉ።

በደርግ መንግሥት ገብረ ክርስቶስ ሀገሩን ለማገልገል ሰርቷል። የመንግሥትን እንቅስቃሴ የሚደግፉ ሥራዎችንም አበርክቷል። ስዕሎችንም አቅርቧል። ሶሚሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት በዚያድባሬ ጦርነት ጊዜም ለሀገሩ ዘምቷል። ሜዳሊያም ተሸልሟል።

ውሎ ሲያድር ገብረ ክርስቶስ በደርግ መንግሥት ብዙም አልተደሰተም፡፡ ኬኒያ የስዕል እግዚቢሽን ለማሳየት በወጣበት ወደ ጀርመን ተሰደደ፡፡ ጀርመን ጥገኝነት አልቀበለው አለች፡፡ በ1971 ዓ.ም ወደ  አሜሪካ ተሻግሮ  በኦክላሆማ ጥገኝነት አግኝቶ  የስዕል ስራውን በመስራት፣ አውደ ርዕይ በማሳየት ሳለ ታሞ መጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም ሞተ፡፡ ሥርዓተ ቀብሩም በዚያው ተፈጸመ፡፡ በወቅቱ አስክሬኑ ጭምር ሀገር የከዳ ተብሎ ለአገሩ መሬት ሳይታደል ግብአተ መሬቱም እዚያው ተፈጸመ።

ገብረ ክርስቶስ በ20ዎቹ መጀመሪያ  እድሜ ውስጥ የፊት ገጹ ላይ ለምጽ ወጥቶበታል፡፡ ይህም የስነ ልቦና ቀውስ ጥሎበታል፡፡ የፊት ገጽታው ተለውጦ መላላጥ ጀመረ። በኋላም ፊቱ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለምጽ ሆኖበት ነበር። ለዚህ ሕመም ማከሚያ ብዙ ሙከራዎችን ማድረጉን ታሪክ ይነግረናል። እንደ ልፋቱ ከህመም ሳያገግም ሞት ቀደመው።

 

በርከት ያሉ የግጥም ስራዎችን በራሱ ድምጽ አንብቧቸዋል። ገብረ ክርስቶስ በግጥሙ በይበልጥ የታወቀው ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ ነው። በዚህ ዓመት መጨረሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ገብረ ክርስቶስ፤ መንግስቱ ለማና ጸጋዬ ገብረመድህንን ጨምሮ ሌሎች በወቅቱ በግጥም ሥራቸው የታወቁ ጥበበኞች በታደሙበት መድረክ የግጥም ስራዎችን አቅርቧል። ዛሬም የግጥም አነባበብ ስልቱን ስንሰማው ለየት ያለ ነው። በዚያን  ጊዜም በአጻጻፉና በዜመኛ አነባቡ ታዳሚውን ያስደንቅ ነበር።

ገብረ ክርስቶስ ደስታ እንደገና በሚል ስለ ሀገሩ የጻፈውን ግጥም ቀንጨብ አድርጌ አቅርቤው በዚሁ እሰናበታለሁ። ምናልባት ይህ ግጥም ለትምህርት ጀርመን ደርሶ ከተመለሰ በኋላ  ሀገሩ ውስጥ ሆኖ የጻፈው ይመስላል። ወደ ሀገሩ ከገባ በኋላ በደስታ እና ትዝታ ውስጥ ሆኖ ሳይጽፈው አልቀረም።

 

ይናፍቀኝ ነበር…..

ዞሮ ዞሮ ከቤት

ይላል የኛ ተረት

አቧራው ፀሀዩ ይናፍቀኝ ነበር

አፈሩ ጠጠሩ ይናፍቀኝ ነበር

የመንደር ጭስ ማታ……

ያገር ሰው ነበር እኔን የናፈቀኝ

የቀይ ዳማ ነበር ጥቁር ቆዳ ነበር

ቁርንጫጭ ከርዳዳ ዞማ ጠጉር ነበር

ያገራችን ቋንቋ

ያገሬ ሙዚቃ

ያገራችን ዜማ

ጥበብ እጀ ጠባብ ያገራችን ሸማ

ነበረ ናፍቆቴ ለሁሉም ለሁሉ

ለሸዋ ለወሎ

ለትግራይ ቤጌምድር

ለጎጃም ወለጋ ‘ላሩሲ ኢሉባቡር

ኤርትራ ጋሞጎፋ

ለሲዳሞ ከፋ

ለሁሉም ለሁሉም ነበረ ናፍቆቴ

አለብኝ ትዝታ

ዘመዶቼ ሳሙኝ

ጉዋደኞቼ ጋብዙኝ

ሊስትሮ ጨብጠኝ

ባለጋሪ ንዳ መንገዱን አሳየኝ

ያገሬ ልጅ ቆንጆ ቤት ለእንግዳ በይኝ

አለብኝ ትዝታ…

አዲስ አበባ ላይ ነበረ ናፍቆቴ

መናገሻ ነበር እንጦጦ ነበረ

ኤረር ጋራ ነበር ዝቋላ ነበረ

ገፈርሳ ነበረ ጉለሌም ነበረ

አዲሱ ከተማ

መርካቶ ዲጅኖ ችምችም ያለው መንደር

የከተማው እንብርት ደጃች ውቤ ሰፈር

የችርቸር ጎዳና

የባቡሩ ጣቢያ

ቢሾፍቱ ነበረ ናዝሬት ሞጆ አዋሽ

ድሬዳዋ ነበር

አለማያ ነበር

ሐረርጌ ነበር የተወለድኩበት

እናትና አባቴን ጥዬ የሄድኩበት

የሚካኤል ጓሮ

ሐረርጌ ነበረ

ዞሮ ዞሮ ከቤት……..

ሃገሬ ነበረ እኔን የናፈቀኝ

ኢትዮጵያ ነበረች፡፡

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here