ፔንጉዊን የከሰከሰዉ

0
162

ሦስት ተሳፋሪዎችን ይዞ በዝቅተኛ ከፍታ ላይ ሲበር የነበረ ሄሊኮፕተር በተገቢ ሁኔታ ባልታሰረ ካርቶን ውስጥ የጫነው ፔንጉዊን ወፍ ሾልኮ በበረራ መቆጣጠሪያ ሰሌዳው ላይ በመውጣቱ ከአብራሪው ቁጥጥር ውጪ ሆኖ መከስከሱን ሲቢኤስ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል::

የሄሊኮፕተሩ አብራሪ እና ሦስቱ ተሳፋሪዎች ጥር 29 ቀን 2025 እ.አ.አ በደቡብ አፍሪካ ምስራቃዊ ከርሰ ምድር (ኬፕ) ወጣ ባለች ደሴት ላይ የቅኝት በረራ ሲያካሂዱ ነበር:: በዚሁ ሂደት ላይ ሄሊኮፕተሯ “በርድስ አይላንድ” ላይ ታርፋለች:: አጋጣሚውን በመጠቀም አንደኛው ተሳፋሪ ለአብራሪው ከደሴቲቱ አንድ ፔንጉዊን ወፍ ይዞ መመለስ እንደሚፈልግ ይነግረዋል- አብራሪውም ይስማማል::

እንዲጭን የተፈቀደለት ባለሙያም በካርቶን ውስጥ የያዘውን የፔንጉዊን ወፍ ከአብራሪው በስተግራ ጭኑ ላይ ይዞ ይቀመጣል:: አብራሪው ቅድመ በረራ ፍተሻ ቢያደርግም ፔንጉዊን ወፉን የበረራው እቅድ አካል አለማድረጉ ነው በምርመራ መግለጫው ላይ ያሰፈረው::

አብራሪው ሄሊኮኘተሩን  አስነስቶ 20 ሜትር ያህል ከፍታ እንደወጣ ፔንጉዊኑን የያዘው ካርቶን  ተንሸራቶ በበረራ መቆጣጠሪያ ሰሌዳው ላይ ይወድቃል:: የተፈጠረውን ክስተት አብራሪው መቆጣጠር ባለመቻሉም በስተቀኝ ጐኑ ቁልቁል ይምዘገዘጋል:: ቀድመው መሬት የመቱት በሄሊኮፕተሩ አናት ተገጥመው የሚሽከረከሩት ስለታም ቢላዎች እንደነበሩ የመርማሪዎቹ መግለጫ አመላክቷል::

አደጋው በሄሊኮፕተሩ ላይ ከፍተኛ ውድመት ቢያስከትልም አብራሪው፣ ተሳፋሪዎቹ እና የፔንጉዊን ወፉ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ነው የድረ ገጹ ጽሁፍ ያስነበበው::

በመጨረሻም የደቡብ አፍሪካ የዓየር መጓጓዣ ባለስልጣን በሰጠው መግለጫ ለአደጋው መንስኤ የሆነው ፔንጉዊን ወፍ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ካርቶን መጓጓዙ ከጥንቃቄ ስምምነቶች ውጪ መሆኑን ነው ያሰመረበት:: አብራሪው የበረራ ደህንነት መጠበቂያ ስምምነቶችን በመጣሱ ምን እንደሚወሰንበት ባይገለጽም የበረራ ደህንነት መጠበቂያ ስምምነቶችን ማክበር ግድ መሆኑን ነው ድረ ገጹ ያሰፈረው::::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here