የትምህርት ሚኒሥቴር በፈተና አሰጣጥ ሂደቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ይፈቱልኛል ብሎ ከተከተላቸው የመፍትሔ አማራጮች መካከል ፈተናዎችን ከትምህርት ቤቶች ውጪ በዩኒቨርሲቲዎች እና በበይነ መረብ በቀጥታ /ኦንላይን/ መስጠትን ነው፡፡ እነዚህ አማራጮችም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናም በዩኒቨርሲቲዎች በኦንላይን ይሰጣል፡፡ ለዚህም በርካታ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው የተሻለ የቴክኖሎጂ ዕውቀት እና ክህሎት ኖሯቸው ፈተናውን በብቃት እንዲወስዱ ትኩረት አድርገው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሥራ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ተጠቃሽ ነው፡፡
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ትበይን ባንቲሁን እንዳስታወቁት የኮምፒውተር እጥረት ከነበረባቸው ትምህርት ቤቶች ለሚመጡ እና በቂ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ለሌላቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የኮምፒዩተር አጠቃቀሙ ፈታኝ እንዳይሆን በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ከዙሪያ ወረዳዉ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች መሠረታዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተት ሊኖርባቸው ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ወይዘሮ ትበይን ያምናሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህን እና ሌሎች ተማሪዎች መሠረታዊ የኮምፒውተር ዕውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ትምህርት መምሪያ በ2017 የትምህርት ዘመን አራት ሺህ 429 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈትናል፡፡ ፈተናው በበይነ መረብ ታግዞ ይሰጣል ያለው መምሪያው ለዚህም ከወዲሁ ተማሪዎችን በክህሎት እና በሥነ ልቦና ከማዘጋጀት ጀምሮ ለ‘አይሲቲ’ ባለሙያዎች እና ለትምህርት ቤት አመራሮች የአሠልጣኞች ሥልጠና መስጠቱን አስታውቋል፡፡
‘ሳይረስ አሰስመንት’ (cirrusassessment.com) ተማሪዎች የኦንላይ የፈተና ዘግጅት ላይ አተኩሮ የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ የዓለም ሀገራት የፈተና አሰጣጥ ሂደት ከወረቀት ወጥቶ ወደ ኦንላይን መሸጋገሩን አስታውቋል፡፡ ለዚህ ገፊ ምክንያት ናቸው ካላቸው መካከል ቀዳሚው የዓለም አቀፉ የኮቪድ ወረርሽኝ ነው፡፡
ወረርሽኙ አብዛኛዎቹን የዓለም ሀገራት ማዳረሱን የሚጠቁመው መረጃው፣ የወረርሽኙን ተጽእኖ ለመቀነስ በሚል ትምህርት ተቋማት ተዘግተው መማር ማስተማሩ በኦንላይን እንዲሰጥ መደረጉን ተከትሎ ዛሬ ላይ በርካታ ሀገራት ዲጅታላይዜሽንን ምርጫቸው ማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡
ሀገራት የኦንላይን አማራጭን እንዲከተሉ ካደረጓቸው ወሳኝ ምክንያቶች መካከል ሌላኛው ፈተናዎችን በወረቀት እና እርሳስ በመስጠት ሂደት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ለማዳን ነው፡፡
ለመሆኑ የኦንላይ ፈተና ጥቅም እና ጉዳቱ ምንድን ነው? የሚለውን መረዳትም ተገቢ ነው፡፡ ፈተናዎች በበይነ መረብ አማራጮች በኦንላይን መሰጠታቸው ትውልዱ ዓለምን ወደ አንድነት እየሳበ ወዳለው የቴክኖሎጂ ዓለም እንዲገባ ከማድረግ ጀምሮ የዘመነ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲዳብር፣ በባህላዊ መንገድ እየተሰጠ ባለው የፈተና ሂደት እየወጣ ያለውን ወጪ ለማስቀረት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
ፈተናዎች በወረቀት በሚሰጡበት ወቅት ለፈተና ጥያቄዎች እና ለመልስ መስጫ ወረቀት የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማሟላት የግድ ከፍተኛ ወጪ ማውጣትን ይጠይቃል፡፡ ዋናው ሕትመት ከተጠናቀቀም በኋላ ለመጠባበቂያ እና በሕትመት ወቅት ለሚያጋጥም ስህተት ተጨማሪ ወረቀቶችን ማዘጋጀት ስለሚያስፈልግ እንደ ሀገር የሚወጣውን ወጪ ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡
የፈተና ወረቀቶችን ከማዕከል አውጥቶ ፈተናዎች ወደሚሰጡባቸው አካባቢዎች ለማድረስ የሚጠይቀው ሐብት፣ ጉልበት እና ጊዜም ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪም ፈተናዎች በወረቀት ሲሰጡ ፈተና የሚሰጥባቸውን ተቋማት ምቹ ለማድረግ፣ ክትትል እና ቁጥጥር ለሚያደርጉ አካላት የሚፈጸመው ክፍያም በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡
ፕሮፌሰር ዋሴ ኀይሌ በፈረንጆቹ 2019 በሊንክዲን የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ኢትዮጵያ ብሄራዊ ፈተናዎችን በወረቀት ለመስጠት በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ታደርጋለች፡፡ ዛሬ ፈተናዎችን በአብዛኛው አካባቢዎች በኦንላይ አማራጭ ለመስጠት ውሳኔ ላይ መድረሷ ሀገሪቱ ታወጣው የነበረውን ወጭ እንድትቀንስ ያግዛታል፡፡
የኦንላይ የፈተና አሰጣጥ ለተማሪዎች እና ለመምህራን ትልቅ የጊዜ አጠቃቀም ማስተማሪያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ የሳይረስ አሰስመንት መረጃ ያሳያል፡፡ ፈተናዎች በወረቀት አማካኝነት ሲሰጡ የፈተና ወረቀቶችን ለማሰናዳት የሚጠፋው ጊዜ እጥፍ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ መረጃዎች ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መነሻ አድርገው እንዳመላከቱት ተማሪዎች ለፈተና በመጡበት ቅጽበት ሳይገቡ እንዲጉላሉ፣ እንዲረበሹ እና በዚህም የጠበቁትን ውጤት እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡ መምህራንም ፈተናዎችን ለማረም ወረቀቶችን ከማገላበጥ ያድናቸዋል፡፡ የብዙ ተማሪዎችን የፈተና ወረቀት ተሸክሞ ከመመላለስ ያድናል፡፡
የፈተና አሰጣጥ ሂደት ደኅንነትን አስተማማኝ ለማድረግ ፈተናዎች በኦንላይን አማራጭ መሰጠታቸው ሌላው ፋይዳው ነው፡፡ የፈተና አሰጣጡ በኦንላይ አማራጭ ሲሆን የቁጥጥር ሥርዓቱ በአንድ ማዕከል መሆኑ፣ ፈተናዎችም ቀድመው ወደ ፈተና ማዕከላት የማይገቡ እና ከመጓጓዝ ነጻ መሆናቸው ከስርቆት የጸዳ እንዲሆን በማድረግ ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት ያስችላል፡፡
ፈተናዎች በኦንላይን መሠጠታቸውን ተከትሎ ሊመጡ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ አበርክቶዎች እንዳሏቸው ሁሉ ውስንነቶችም አሏቸው፡፡ ከተለምዷዊ የፈተና አሰጣጥ ሂደት (ወረቀት) ወደ ኦንላይን በሚደረገው ሽግግር ወቅት ቀዳሚው ፈታኝ ነገር መሠረታዊ የኮምፒውተር ዕውቀት ለሌላቸው ተማሪዎች ነው፡፡ ተፈታኞችን ከፈተና በፊት በሚፈለገው ልክ ለማብቃት የሚጠይቀው ጊዜ ሰፊ መሆኑ እና የየትምህርት ቤቶቹ የኮምፒውተር፣ የላፕቶፕ፣ የኢንተርኔት አቅርቦት እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች በበቂ መጠን አለመኖር የፈተና አሰጣጡ ተቀባይነት እንዲያጣ ሊያደርገው እንደሚችል ይታመናል፡፡
መምህራን ከመደበኛው ትምህርት በተጓዳኝ ተማሪዎች መሠረታዊ የኮምፒውተር ዕውቀት እንዲኖራቸው በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ ያመላከተው ደግሞ ኮርስ ኢራ ዶት ኦርግ (coursera.org) ነው፡፡ መንግሥትን ጨምሮ የትምህርት ተቋማት፣ በተዋረድ የሚገኙት የትምህርት ባለድርሻ አካላት እና ባለሐብቶች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በሚደረገው ሂደት ንቁ ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ተማሪዎችም ኮምፒውተር እና ላፕቶፕ ላይ ለመጻፍ ከመለማመድ ጀምሮ የትኛው የኤሌክትሮኒክስ መተግበሪያ ለምን ዓላማ እንደተጫነ በመረዳት በተደጋጋሚ መጠቀም ይገባል፡፡
በፈተና ወቅት የፈተና አሰጣጡ መደናገር እንዳይፈጥር በቀደሙት ዓመታት በኦንላይን የተሰጡ ፈተናዎችን በመክፈት መልሶችን ማክበብ፣ የጽሑፍ ጥያቄዎችን እንዴት እና በምን አይነት ፍጥነት መሥራት እንደሚቻል ራስን መፈተሽ ዋናው የፈተና ወቅት የዘወትር ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ የኮርስ ኢራ ዶት ኦርግ መረጃ ይጠቁማል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም