አጣብቂኝ

0
124

የዓለም ለውጥ አምጪ ሰዎችን ታሪክ ለሚያነብ ሰው የተለወጡት በአጣብቂኝ ውስጥ በማለፋቸው ነበር።

ምርጫ መኖሩ ለመለወጥ ጥሩ ቢሆንም እንኳን ምርጫዎች የሰው ልጆችን ባሉበት ወይም ወደ ኋላ እንዲመለሱ ያደርጋቸዋል። ብዙ ምርጫዎች መኖራቸውን ደስታን አይሰጥም። የሰው ልጆች ደስታን ብዙ በማግኘት፣ በማከማቸት ሊያገኙት ሞክረዋል። እውነቱ ግን ብዙ ባለን ቁጥር ብዙ ጭንቀት እና ስቃይ ይበዛብናል።

ሳን ትዙ “ዘ አርት ኦፍ ዋር” በሚለው መጽሐፉ ውጊያ ላይ ያሉ ወታደሮች  ጀልባዎቻቸውን እና ያለፉበትን ድልድይ እንዲያቃጥሉ እና እንዲሰብሩ ይመክራል። ወደ ኋላ ለመመለስ ያላቸውን አማራጭ እያጠፉ ወደ ጠላት ስፍራ መጓዛቸው ምርጫ የሌለው ምርጫ ነው ይላል። ምናልባት የጠላት ጉልበት በርትቶባቸው ወደ ኋላ መመለስ እችላለሁ የሚል አማራጭ ቢኖራቸው በቀላሉ ቀድመው ይሸነፋሉ። ድልድዮችን መስበር በሰሜኑ የሀገራችን ጦርነቶች የተሞከረ እና ብዙ እልቂትን ያስቀረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የተከዜ እና ጽጽቃ ወንዞች  መሸጋገሪያ ድልድዮች በጦርነት ወድመው ነበር። በዚህ ጊዜ ምን ያህል ጉዳት ማስቀረት ተቻለ የሚለውን ድልድዮችን ያፈረሰው ተዋጊ ቡድን ብቻ ነው የሚያውቀው።

ሳን ትዙ የሚለውም ይህን ነው። ለማፈግፈግ ያለህን አማራጭ ዝጋ፣ ስበር  ነው የሚለው። ማምለጫ፣ መሿለኪያ፣ መመለሻ አማራጭ የሌለው ወታደር ከጠላት ጋር የሞት ሽረት ትግል ያደርጋል። የመጨረሻ የሚለውን አቅሙን ይጠቀማል።

እ.አ.አ በ1519 የስፔኑ ካፒቴን ሄርናን ኮርቴስ በሚክሲኮ የሐይቅ ዳርቻዎች ወረራ አድርጎ ወታደሮችን ጀልባውን አቃጥሉት የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ። ወታደሮች ሐይቁን ተሻግረው አዲስ ግዛት ውስጥ እንደገቡ ጠላት የተኩስ ጋጋታ ቢከፍትባቸውም እንኳን መመለሻቸውን አቃጥለዋልና፤ ምርጫቸው መፋለም ነው። በዚያም ጊዜ ጦርነቱን በአሸናፊነት ወደ ፊት መግፋት ችለዋል።

“ጀልባዎች ሐይቅ ዳርቻዎች ላይ ከተቃጠሉ ጠላት ተኩሱን ቢያበረታብኝም እንኳን የምመለስበት አማራጭ፣ የማፈገፍግበት እድል የለኝም በሚል አዕምሮ ለማሸነፍ ይዘጋጃል። “ማምለጫ የለህም፣ እስከ ምት  ተዋጋ” የሚል የጥንቃቄ መልእክትን ይናገራል። ለማሸነፍ እና በሕይወት መቆየት ቆራጥ ይሆናል።

አዕምሮ አማራጭ ካለው አቅምን ይቆጥባል። የጀመርነውን እንድናቋርጥ ይነግረናል። ማምለጥ ወይም ማቋረጥ አዕምሮ የሰው ልጆችን በሕይወት ለማቆየት የሚፈጥረው ዘዴ ነው። ፉክክር በበዛበት፣ በንግድ፣ ስራ  ዓለም ውስጥ ደግሞ በሕይወት መቆየት የመሪዎች እና የስራ ፈጣሪዎች ድርሻ አይደለም። ለአማካይ እና ተራ ሰዎች በሕይወት መቆየት ትልቅ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ሕልም እና ራዕይ ላላቸው ግን ቀልድ ነው። ለተራ ሰዎችማ ስራ መያዝ በቂ ነው። ያችን ስራ ሳይለቁ መቆየት ትልቅ ስኬት ነው።

ፈሪ ሰዎችን አጣብቂኝ ውስጥ አታስገቧቸው፤ ከገቡ የመጨረሻ የአልሞት ባይ ተጋዳይ ርምጃቸውን ወስደው ያጠፋሉና። ከጅብ በጣም ትንሽ ጉልበት ያለው አህያ ነው። ማምለጫ ሲኖረው ከጅብ ሮጦ ያመልጣል። በጉልበቱ ደካማ ነው። ከሩጫ በኋላ በጅቡ መበላት የተፈጥሮ ገሀድ ነው።

ይህ ገሀድ ግን የሚለወጥበት ጊዜ ይመጣል። ጅብ አህያን ማምለጫ፣ መሮጫ፣ መሳደጃ ያሳጣው  ጊዜ ግን ተሸናፊው አሸናፊ ይሆናል። አህያ የመሮጥ እድል ተሰጥቶት አመልጣለሁ ማለቱ ነው የጅብ ራት የሚያደርገው። “ጅብ ቢመጣብኝ እሮጣለሁ” የሚል ምርጫው ነው የሚያስጠቃው። አልሮጥም እገጥማለሁ ቢል ጅብን የማሸነፍ አቅም እንዳለው አይተናል። እንዳይራመድ፣ እንዳያመልጥ አማራጭ ያጣ ጊዜ የመጨረሻ አቅሙን አሟጥጦ ይጠቀማል። ተነካሹ ነካሽ፣ ተሳዳጁ አሳዳጅ፣ ሯጩ አሯሯጭ፣ ተበዩ በይ ይሆናል። አህያ ጅብን ነክሶ ይዞ ሲገድል በእንስሳት ዓለም ቪዲዮ አምራቹ  ናሽናል ጂኦግራፊ አይቻለሁ።

አህያው ጅቡ ሲመጣበት የማምለጥ እድል እና የማፈግፈጊያ አማራጮችን ያማትራል። በፍጥነት ሳይደርስበት ለማምለጥ ሲሮጥ ተይዞ ይበላል። አህያው ምንም ምርጫ ባልኖረው ጊዜ አጥፊውን ያሸንፋል። ከመግጠም በቀር ምርጫ የለኝም ብሎ በሚገጥምበት ጊዜ አህያ ጉልበቱ ከጅብ በልጦ አንገቱን አንቆ  ይገድለዋል።

አማራጭ ሲኖር መወላወል፣ ዛሬ ወይም ነገ ማለት፣ በአንድ ነገር ላይ ለማተኮር መቸገር አለ። ጥግ ይዞ የተቀመጠ ድመት እና ውሻን እስከመጨረሻው ማሳደድ በአሳዳጁ ላይ የተሳዳጅነት እጣን ያመጣል። እንደሚሞት ያወቀ እንስሳ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ከፍተኛ አቅም ይጠቀማል።

ከኋላው ጅብ ሊበላው የሚያሯሩጠውን  ገደል ጫፍ ያለን በሬ አስቡት።  ይህ በሬ  በሕይወት ለመቆየት ያለው ያለው ምርጫ አንድ ብቻ ነው። ለመኖር ጉጉት አለውና ቆሞ በጅብ መበላትን ማንም አይመርጥም። ይህ በሬም ለጅብ ሰውነቱን ቆሞ አይሰጥም። ቀዳሚው ምርጫው ከዚህ ቀደም በመልካም ጊዜ ሊሻገረው የማይችለውን ገደል መዝለል እና በሕይወት መቀጠል ነው። የተደበቀውን አቅሙን ይጠቀማል። ማንም ያልገመተውን ችሎታውን አውጥቶ ተጨማሪ እድሜን ለመኖር ይችላል። አድሬናሊን የተባለው ሆርሞን በጭንቀት ጊዜ ይመነጫል። “ግጠም ወይ ሩጥ” የሚል ዝግጁነትን በሰውነት ውስጥ ያሰራጫል። አካል ያን ጊዜ ለሁለቱ ነገሮች ይዘጋጃል። የመጨረሻ አቅምን አሟጦ መግጠም ወይም መሮጥ ምርጫ ይሆናል።

አጣብቂኝ ውስጥ መገኘት በሁለት ምክንያቶች ወደ ፊት እንድንገፋ ያደርገናል። አንደኛው ያልተነካ አቅማችንን እንድንጠቀም ያደርገናል። ሁለትም የማናውቀውን በውስጣችን ያለ ጉልበት እንድናውቅ ከራሳችን ጋር ያስተዋውቀናል። ብዙ ሰዎች ከችግሮቻቸው በኋላ “እንዴት እንዳደረግሁት አላውቅም፣ ከየት አመጣሁት ያንን ድፍረት እና ጉልበት” ሲሉ እንሰማቸዋለን።

በአሸናፊ እና ተሸናፊ መሐል ያለው ልዩነት ድብቅ አቅምን አሟጦ የመጠቀም ጉዳይ ነው። ወደ ኋላ መመለስ እንደማይችል፣ ሞት የሚባል ነገር እንደሚጠብቀው የሚያውቅ በሬ ወደ ፊት ገደሉን ዘልሎ ከመሻገር ውጪ ምርጫ የለውም።

በሰዎች አኗኗርም የሚደግፏቸው፣ የሚረዷቸው፣ አይዟችሁ የሚሉ አጋዦች ያሏቸው ሰዎች ብዙ በስኬት መንገድ አይራመዱም። ከብዙኀኑ የተለየ ውጤት አያስመዘግቡም። ቢሳካላቸው እንኳን በደጋፊዎች ብርታት እንጂ በራሳቸው ጥረት  የተለወጡ አይደሉም።

የሚደግፋቸው ዘመድ ያላቸው ሰዎች ለምን ብለው ዋጋ ይከፍላሉ? ለምን ብለው ቅዝቃዜ ይጋፈጣሉ? ለምን ብለው እንቅልፍ ያጣሉ? ለምን ብለው ይጨነቃሉ? ለምን ብለው አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ያልፋሉ?

አማራጭ የሌላቸው ሰዎች ያድርጉት እንጂ!

“ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ አትሞትም” እንደሚሉት አበው ሁለተኛ እና ሦስተኛ አማራጭ ያላቸው ሰዎች ወደ ፊት ገፍተው ለመራመድ አይደፍሩም። ዋጋ ለመክፈል ምክንያት ያጣሉ።

ለማፈግፈግ ምንም ምርጫ ከሌላችሁ ወደ ፊት ትገፋላችሁ። ተራራ እየወጣችሁ ከሆነ ምርጫችሁ ወደ ኋላ መመለስ አይሆንም። ወደ ፊት መግፋት ብቻ ነው። “ብዙ ምርጫዎች ሲኖሯችሁ ሁለት ያሳደደ አንድ አያገኝም” እንደሚባለው የምርጫ ጋጋታ ለተሻለ ውጤት አያበቃም።

“ምርጫ የለኝም” ብለው የሚሰሩ ሰዎች ትኩረታቸው አንድ ነገር ላይ ብቻ ነው። ከመስራት በቀር ምንም ምርጫ እንደሌላቸው ሲያውቁ ወደ ፊት ገፍተው ይለወጣሉ። ከክንዳቸው በቀር ማንም ዋስትና እና መተማመኛ እንደሌላቸው ሲገባቸው ጥግ ድረስ አንድ ነገር ላይ አተኩረው ይሰራሉ።

ከመጠንከር በቀር፣ በተስፋ ከመራመድ በቀር፣ ከቆራጥነት በቀር፣ ከጀግንነት በቀር በሕይወት ሌላ ምርጫ የሌለው ሰው በያዘው ነገር ጸንቶበት ይለወጣል።

በድህነት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች፣ በፈተናዎች እና አጣብቂኞች ውስጥ ያለፉ ሰዎች አለምን ቀይረዋል። ለትውልድ የሚሻገር ፍሬያማ አሻራዎችን አስቀምጠዋል።

ትልቅ ጉዳይ ማሳካት የምትፈልጉ ከሆነ፣ ስኬታማ ስራ እንዲኖራችሁ ምትሹ ከሆነ አማራጭ ባይኖራችሁ ጥሩ ነው የሚለው የሳን ትዙ ምክር ነው። ሳን ትዙ እንደሚለው በዚህ ዘመን የሚቃጠል ጀልባ ላይኖረን ይችላል። የጀልባዎች መቃጠል ዋና መልእክቱ በድርጊታችን መግፋት፣ ለስኬት መትጋት እና አማራጮችን ማጥፋትን ነው። የተበታተነ ትኩረታችንን ሰብስበን አንድ ጉዳይ ላይ ለውጤታማነት እንድናውለው ነው።

ዊል ስሚዝ “እቅድ ቢ አያስፈልግም፤ ከእቅድ ኤ ያናጥባልና” ብሏል። በሕይወት ውስጥ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ሲያልፍም ሦስተኛ እቅዶችን ማስቀመጥ የተለመደ ጉዳይ ነው። ሦስት እና አራት ምርጫዎች መኖራቸው አንዱ ባይሳካ ሁለተኛውን እይዛለሁ። ሁለተኛውም ባይሰምር ሦስተኛውን አደርጋለሁ ብሎ እንደማሰብ ነው። ሁለት እና ሦስት እቅድ አይኑራችሁ የሚለውን  ሐሳብ ብዙዎች ይቃወሙት ይሆናል።

በዊል ስሚዝ እና በሳን ትዙ ሐሳብ መሰረት አንደኛውን እቅድ ግግም ብላችሁ አሳኩት። ሁለተኛ እንደሌላችሁ አስባችሁ በቆራጥነት ብትሰሩ አንደኛው ማይሳካበት ምክንያት የለም ማለት ነው። ሁለተኛው እቅድ ድረስ መሄድ ለምን? አንደኛውን በመወላወል ከጀመራችሁት አይሳካም፤ ስለዚህም የመጀመሪያውን የመጀመሪያም የመጨረሻም አድርጋችሁ ስሩ ነው የሚሉን።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here