ምክር ቤቶች የሕዝብ ውክልናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

0
134

የአማራ ክልል ምክር ቤት በተዋረድ ከሚገኙ የምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ ምክትል አፈ ጉባኤዎች፣ ቋሚ ኮሚቴዎች እና የዕቅድ ባለሙያዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሟል።

በግምገማው የተሳተፉት የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፍቅሬ በፈቃዱ በዘጠኝ ወሩ ምክር ቤቶች ውክልናቸውን ለመወጣት የአገልግሎት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በመቀበል እና ክትትል በማድረግ መሥራታቸውን አንስተዋል። የሕዝብን ጥያቄዎች አሥፈጻሚው እንዲመልስ በቋሚ ኮሚቴዎች ክትትል እና በጉባኤዎች ውይይት በማድረግ ውክልናውን ለመወጣት መሠራቱን ገልጸዋል። በብሔረሰብ ምክር ቤቱም በየሦስት ወሩ የሪፎረም ውይይት በማድረግ ሥራዎችን እንደሚገመግሙም ነው ያብራሩት።

ምክር ቤቶች የሕዝብን ጥያቄዎች በመያዝ በጉባኤዎቻቸው እየተወያዩ አሥፈጻሚው የሚሠራበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ እና እንደሚገመግሙ አፈ ጉባኤ ፍቅሬ ገልጸዋል። ከወቅታዊ ችግሮች አኳያ ውስንነቶች ቢኖሩም በየጊዜው የሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ አሥፈጻሚውን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል። የጸደቁ አዳዲስ አዋጆች እና መመሪያዎችን ወደ ታች የማድረስ ሥራ መሠራቱን እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ አየን ብርሃን በበኩላቸው በዘጠኝ ወር የምክር ቤቱ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ የተዋረድ ምክር ቤቶች አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ጠቅሰዋል። ቋሚ ኮሚቴዎች የአሥፈጻሚውን ሥራ በአካል ተገኝተው ምልከታ በማድረግ የሚስተካከሉት እንደተስተካከሉ እና ቀሪ ሥራዎችም እንዳሉ በውይይቱ መነሳቱን ገልጸዋል። የሕዝብ ፍላጎት ለማስፈጸም ተወያይቶ መፈጸም እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡንም አንስተዋል።

የሕዝብ ጥያቄዎችን ይዞ ለመፍታት ምክር ቤቶች በትኩረት እየሠሩ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አየን ችግሮችም የሚፈቱት በሰላማዊ መንገድ እና በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት ነው ብለዋል። የክልሉ መንግሥትም ለሰላም ትኩረት በመስጠት የሰላም አማራጮችን በማስቀደም ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ሕዝቡን የሚያማርሩ እና ከችግር ላይ ችግር የሚጨምሩ አሠራሮችን በመቀነስ እና በመታገል በኩልም ምክር ቤቶች በአገልግሎት አሰጣጥ እና በሙስና ያሉ ችግሮችን አጥብቆ በመያዝ መታገል እንደሚገባ ገልጸዋል። የተጀመረው የሪፎርም ሥራም የዚሁ አካል እንደሆነ አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማው ያደገ የሥራ አፈጻጸም መታየቱን አንስተዋል። የሕዝብን ተጠቃሚነት ከመፍጠር እና ከማሳደግ አኳያም ትኩረት እንደተሰጠ ተናገረዋል። የተቋማት ዕቅድ ተፈጻሚነት እና ብልሹ አሠራሮች ስለሚቀረፉበት ሁኔታም ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል። ሊታረሙ የሚገባቸው ችግሮች መኖራቸውም እንደተነሳ ገልጸዋል። ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በመሥራት እና ያለውን ጅምር በማጠናከር ምክር ቤቱም ድርሻውን መወጣት መጀመሩን ተናግረዋል።

በክልሉ ላለው የጸጥታ ችግር እና መፍትሄው ምክር ቤቱ የራሱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት መነሳቱንም አብራርተዋል። በምክር ቤቶች ጉባኤዎች ላይ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች በአሥፈጻሚው እንዲመለሱ መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።

የሕዝብ ጥያቄዎችን በመመለስ በክልሉ ሰላም እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ከማበርከት አኳያ ጥያቄዎችን በተገቢው ለይቶ ለባለቤቱ በመስጠት እንደሚሠራ ነው ያረጋገጡት። የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል እና የመልካም አሥተዳደር ችግርን ለመፍታት የተሠሩ ሥራዎችን በመገምገም እንደሚሠሩም አብራርተዋል። በሰላም ዙሪያ የሕዝቡን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡ እንዲመክር ማድረግ ይገባል፣ በምክክር ኮሚሽኑም የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲቀርቡ ተደርጓል ብለዋል።

(ቢኒያም መስፍን)

የሚያዝያ 20  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here