“ስፖርትን ሕዝባዊ እናድርገዉ ”

0
68

26ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከሰሞኑ ያካሄደው የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ስፖርት ምክር ቤት በ2017ዓ/ም የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር በማሳወቅ በቀጣይ ወራት ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ከስፖርት ቤተሰቦቹ ጋር መክሯል፡፡

በጉባኤው የባሕርዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ እና የባሕርዳር ከተማ ስፖርት ምክርቤት ሰብሳቢ አቶ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ከከፍተኛ እስከ ቀበሌ ድረስ  ያሉ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው የስፖርት ቤተሰቦች እና ም/ቤት አባላት ተሳትፈዋል፡፡

እንደሚታወቀው የስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ ስፖርት ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ለማድረግ በየደረጃው ያሉ የስፖርት ማሕበራት ኮሚቴዎች በየጊዜው እየተገናኙ ተግባራትን እየገመገሙ የሚመሩበት ነው፡፡ በመሆኑም በመድረኩ የስፖርት ም/ቤት ጉባኤዎች ለከተማው ስፖርት ዕድገት መሰረት መሆናቸው ነው የተጠቀሰው፡፡

የባሕርዳር ከተማ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቶማስ ታምሩ እንደተናገሩት ስፖርት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማሳያ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት  ነው፡፡ እንዲሁም ስፖርት ትውልድን በአካልም ሆነ በአዕምሮ በጥሩ ስነ- ምግባር መገንቢያ  በመሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በከተማ፣ በክፍለ ከተማና በቀበሌ በስፋት እንዲሠሩ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በ26ኛው ጠቅላላ ጉባኤ  በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን  ጥያቄዎች ተነስተውም ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም በየክፍለ ከተማው የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ አያያዛቸው ግን ተገቢ እንዳልሆኑ እንዲያውም ለጤና ጠንቅ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው የተነገረው፡፡ በመሆኑም ጥገና ለምን አይደረግላቸውም? ፣ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች መካከል የሚደረጉ ውድድሮች ተተኪን ለማፍራት ጠቃሚ ሆነው ሳለ ለምን ተቋረጡ ?፣ የብስክሌት ውድድር ለምን አይጀመርም?፣  ለሁሉም የስፖርት አይነቶች ለምን ተመሳሳይ ትኩረት አይሰጣቸውም?  የሚሉ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም አሁን ካለው የዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ አሰልጣኞች ለውድድር ወደ ሌላ ቦታ ሲሄዱ የውሎ አበል ስለሚያንሳቸው ቢስተካከል የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ የአትሌቲክስ ክለብም ራሱን ችሎ ለምን አይቋቋምም የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡

ለቀረቡት ጥያቄዎች ከከተማ አስተዳደሩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከምላሾቹም መካከል ለበሽታ ሊዳርጉ የሚችሉ  የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በጊዜያዊነት ጥገና እንደሚደረግላቸው ተገልጿል፡፡

የስፖርት ምክርቤቱ ሰብሳቢ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ የተከበሩ አቶ ጎሹ እንዳላማው እንደገለጹት  ከተማ አስተዳደሩ በዓመት 120 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የከተማዋን ስፖርት ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም  ማህበረሰባዊ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ነው የገለጹት፡፡

ለጤና ጠንቅ የሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በጊዜያዊነት ማስተካከል እንደሚገባ ነው ከንቲባ ጎሹ የተናገሩት፡፡ ለሁሉም የስፖርት ክለቦች እኩል ትኩረት የለም የሚለውን በተመለከተም ለሁሉም ስፖርቶች ዕኩል በቂ ሙያዊ እና የአመራር ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

ስፖርቱን ህዝባዊ ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት ከንቲባው ትምህርት ቤቶች ላይ የስፖርት ውድድሮች እንዲካሄዱ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የስፖርት ማዕከል ግንባታ በልዩ ትኩረት ሊሠራ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ከስፖርቱ ዘርፍ ሀብት እንዴት ማግኘት እንደሚቻል የስፖርት መምህራን ትኩረት እንዲያደርጉበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በተጨማሪም የባሕርዳር ከተማ የብስክሌት ውድድር ወደነበረበት መመለስ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ ሀገር አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የስልጠና ማዕከላት፣ ጥርጊያ ሜዳዎች፣ በት/ቤቶችና በተቋማት ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በማስፋፋት እና በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ እንደሚደረግ ነው የተገለጸው፡፡

በክ/ከተማ እና በገጠር ያሉት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ህጋዊ ማረጋገጫ ሰነድ/ደብተር ካርታና ፕላን ተሰርቶላቸው ደረጃቸው ተጠብቆ እንዲገነቡና አገልግሎት እንዲሰጡም ይደረጋልም ነው የተባለው፡፡ የባሕርዳር ከተማ የአትሌቲክስ ክለብ ለምን አይቋቋምም ለሚለው ጥያቄም የባሕርዳር ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቶማስ  ታምሩ እንደገለጹት “ክለብ እንሁን” የሚሉ ጥያቄዎች ከአትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የስፖርት ዘርፎችም እንደሚመጡ ጠቅሰው ይህንን ጥያቄ ለማስተናገድ የፋይናንስ አቅም ስለሚጠይቅ የባሕር ዳር እግርኳስ ቡድንን (የጣናው ሞገድን) በማጠናከር በስሩ የተለያዩ ስፖርቶችን እንዲያካትት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ለፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች/ ተወካዮች 200 ብር የአልጋ አበል እንዲጨመራቸው ተወስኗል፡፡ እንዲሁም ከከተማ መምሪያዎች ወይም ጽ/ቤቶች አንድ መቶ ሺህ ብር በዓመት ለስፖርት ም/ቤት  የገቢ ድጋፍ ተወስኗል፡፡

ተቀዳሚ ከንቲባ የተከበሩ አቶ ጎሹ እንዳላማው ስፖርቱን ህዝባዊ ማድረግ  ላይም የሚቀር ሥራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ስፖርቱን ለመንግሥት ብቻ መተው እንደማይገባ የተናገሩት ከንቲባው  ህዝባዊ በማድረግ ባለሀብቱ ጭምር እንዲሳተፍ መደረግ እንዳለበት ነው የጠቆሙት፡፡

“ስፖርት ለባሕር ዳር ከተማ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም ከተማ ናት፡፡ በተፈጥሮ የታደለች ከተማ ናት፡፡ ስለዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ እና ማሰልጠኛ ቦታዎች ያስፈልጉናል” ነው ያሉት ክቡር ከንቲባው፡፡ ይህንን ለማድረግም በጀቱን  ከመንግሥት ብቻ መጠበቅ እንደማይቻል እና ስፖርቱን ህዛባዊ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ነው በጥብቅ ያሳሰቡት፡፡ በዚህ ዓመት በስድስቱ ክፍለ ከተሞች አንዳንድ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ደረጃቸውንና ጥራታቸውን የጠበቁ ተደርገው እንደሚሠሩ ነው የገለጹት፡፡ ይህ ሥራ ሲሠራ ግን የህብረተሰቡ እና የባለሀበቱ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያም  ለዳኞች    ከፍተኛ ውጤት ለተገኘበት ስፖርት ዘርፍ አሰልጣኞች፣ ለፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት/ ተወካዮች፣  ለቡድን መሪና ኃላፊዎች   ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሚያዝያ 27  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here