ብርቱ ሴቶች

0
95

ኢትዮጵያ በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከጣሊያን ጋር ሦስት ጦርነቶችን በዶጋሊ /በ1889 በአጼ ዮሓንስ አራተኛ ዘመን/፣ በዓድዋ/1888ዓ.ም በአጼ ዮሐንስ አራተኛ/ ዘመን እና በአምስቱ የፋሽስት ወረራዎች /1928 እስከ 1933/ዓ.ም በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን  አካሂዳ በድል ተወጥታለች:: በዚህ ተጋድሎ የሴቶች ሚና ገናና እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስታውሳሉ::

ታዋቂው ተጓዥ እና ፀሐፊ ጀምስ ብሩስ/James Bruce/ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት  ሴቶች ያደረጉትን አስተዋፅኦ በብዕሩ ከትቦ አስቀምጧል፤ “በዚህ ዓለም ማንም ሴት እንደ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ቀን ከለሊት ሳይለዩ፣ ሳይደክሙ፣ ሳይሰለቹ… ጦሩ ወደ ጉዞ ይዞት የሚሄደውን ስንቅ በማዘጋጀት፣ ውኃ በእንስራ ተሸክመው በማቅረብ የሚሠሩ ጠንካራ እና ብርቱወች  ናቸው:: ከዚህ ባለፈም በዕለት ከዕለት መንገድ በማፅዳት፣ የተጎዱትን አርበኞች የህክምና እርዳት በመስጠት… ሲሳተፉ ታይተዋል።”

በአብዛኛው የኢትዮጵያን  ሴት አርበኞች ልዩ ያደርጋቸው የነበረው ሁኔታ ደግሞ የጠላት ጦር መቃረቡን ለአርበኞች ጥሩንባ በመንፋት ያሳውቁ እንደነበር  ታሪክ ይዘክራል። የሴት አርበኞች ተጋድሎ ይህ ብቻ አልነበረም፤  ከአውሮፕላን የሚወረወረውን ፈንጂ ከምንም ሳይቆጥሩ በከፍተኛ ቦታ በመደበቅ የጠላት ጦር በሚያልፍበት ትላልቅ የድንጋይ ናዳ ለቆ መንገድ በመዝጋት ጠላትን የመከላከል፣ መሳሪያዎችን አጽድተው የማቅረብ… አስተዋፅኦ ያደርጉ እንደነበር ታሪክ ፀሐፊው ይገልፃሉ።

እንደ ወ/ሮ ፅጌ መንገሻ ያሉ አርበኞች የቆሰሉ ወገኖችን በህክምና ይረዱ እንደ ነበርም ይታወቃል። የታሪክ ፀሐፊዎቹ እንዳስቀመጡት  በጣም ብዙ ሴቶች የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለውበታል:: የታሪክ ፀሐፊው አንድሪው ሂለተን “The Ethiopian Patriots Forgotten Voices of the Italo-Abyssinian war 1935-41” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ  አርበኞቹ ዓለሚቱ መኮንን እና ወ/ሮ ዘነበች ወልደየስ የተባሉ የ80 ዓመት እድሜ ያላቸው አዛውንቶችን  በቃለ መጠይቅ  ለምስክርነት አቅርቧል።

አርበኛ ዓለሚቱ መኮንን በወረራው ጊዜ ምንም እንኳን የ15 ዓመት ታዳጊ ቢሆኑም ብዙ ነገር የሚያውቁ እና የተገነዘቡ ሴት እንደ ነበሩ የታሪክ ፀሐፊው በመጽሐፋቸው አስፍረዋል። በዚያ ወቅት ባደረጉለት ቃለ ምልልስ “የ15 ዓመት ዕድሜ ያለው ማንኛውም ወንድም ሆነ ሴት ሀገሩን ከጠላት ይጠብቃል ተብሎ ስለሚገመት እኔም ቤተሰቦቼ ገና የአስር ዓመት ልጅ እያለሁ ስለሀገር ፍቅር ግንዛቤ ፈጥረውልኛል:: አያቴ በአድዋ ጦርነት፣ አባቴ እና ወንድሞቼ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በቀደምትነት በሠለጠነ መሣሪያ ሳይሆን ባላቸው የቆዬ ጠብመንጃ ፉቺሌ (Fucill) ፣በዚያን ጊዜ ይታወቅ የነበረው ናስ ማስር( Nas Masr)፣ ስናድር እና ውጅግራ በመያዝ ነበር ከጠላት ጋር ግብ ግብ የሚገጥሙት:: ሕይወታቸውን እና ንብረታቸውንም ለሀገራቸው መሰዋትነት ከፍለዋል” በማለት ነበር እርሳቸውም የነሱን መርህ በመከተል  የውጭ ጠላት ሀገራቸውን ሲወራት በግንባር እና በደጀንነት መሳተፋቸውን የተናገሩት::

አርበኛ ዓለሚቱ መኮንን  ወንድማቸው በጠላት እጅ ወድቆ በጥይት ተደብድቦ ከመገደሉ ባለፈ  ጥርሶቹን አውልቀው አስከሬኑን ከሦስት ቀን በኋላ ገደል ውስጥ ጥለውት ማግኘታቸው ደግሞ እንደ ጦር ሕግ ቢሆን ኖሮ ይህን የፈጸመ አካል ተይዞ ለፍርድ ይቅርብ ነበር እንጂ እንደ እንስሳ የትም አይጣልም ነበር!” በማለት  ቁጭት እንዳደረባቸው ተናግረዋል::

ከወንድማቸው አሰቃቂ ግድያ ጋር  የ17 ቤተሰቦቻቸው እልቂት ተዳምሮ ሁሉን ነገር ትተው ወደ በረሀ በመግባት ትግላቸውን ጀመሩ:: አርበኛዋ በቃለ ምልልሱ ወቅት እንደተናገሩት ከቤጌምድር ውስጥ ወንዶ ገጠም (ሰሚ ማርያም) ተብላ ከምትጠራው ቦታ ጣሊያኖች በግራ እና በቀኝ ጦራቸውን አስፍረውባታል:: በዚች ስፍራ የአርበኞችን ጦር የሚመሩት ግራዝማች ተድላ እና ግራዝማች ገብሬም በጠላት ተገደሉ::  በወቅቱ አርበኛ ዓለሚቱ የሚሳተፉበት ጦር በጠላት የኀይል ብልጫ ለመበታተን ተገደደ፤  እሳቸው ግን ከሌሎች አርበኞች ጋር በመቀላቀል ትግሉን ቀጠሉ።

“በርግጥ ይህን ስል እንደ ጠላት በሰለጠኑ መሣሪያዎች መዋጋት ባንችልም ባለን የሀገር ፍቅር እና ቆራጥ ውሳኔ በመነሳሳት ባለን መሳሪያ በውጊያው ተሳታፊ ሆነናል። ከማስታውሰው አንድ ጊዜ የጠላትን የሬሽን (ምግብ ማጓጓዣ)  አውሮፕላን ተኩሰን በመጣል ዘመናው የጦር መሳሪያ፣ ዳቦ፣ ማርማራታ… የማረክንበት ወቅት እና ባገኘነው በሰለጠነ መሳሪያ እየታገዝን ለድል የበቃንበትን ሁኔታ አልረሳውም።

“በዚያን ጊዜ ሌላው ሳልጠቅሰው ማለፍ የማልፈልገው የሬዲዮ መገናኛ ባለመኖሩ ከሌሎች ራቅ ካሉ አርበኞች ጋር የደብዳቤ ልውውጥ እናደርግ የነበረው በእንጨት ዱላ (መቃ) ውስጥ መልክቱን በመክተት ማንም በማይጠረጥረው መንገድ ነበር። እንዲሁም የአንድ አካባቢ አርበኛ ከሌላው  ጋር በጠላት ላይ ሊደረግ የሚገባውን እንነጋገር ነበር።  በዚህም የጦር መሳሪያ እና ሌሎችንም ርዳታዎች እንለዋወጥ ነበር። ከጎንደር  ወደ ጎጃም ጥጥ ተልኮ ለአርበኞች  ልብስ ይሠራ ነበር። ሕዝቡም ውኃ ብንጠይቅ ወተት ሰጥቶ በሚያስፈልገው ሁሉ እንክብካቤ እድርጎልናል።”  በማለት  አርበኛ  ዓለሚቱ በወቅቱ ብሔር፣ ሃይማኖት…ሳይገድባቸው ለሀገራቸው ሰላም ካለልዩነት ይታገሉ እንደ ነበር መሰክረዋል::

ከንጉሡ በማንኛውም ጊዜ የማበረታቻ መልዕክት በሰውም ይሁን በደብዳቤ  ለአርበኛው ይደርሰው ነበር። በመጨረሻውም  ወደ ድል በሚቃረቡበት ወቅት ከእንግሊዝ ጦር ጋር ሲመለሱ የጣሊያን ፋሽሽት ጦር ከውጭ የጦር ኀይል መምጣቱን ሲረዳ በጣና ሀይቅ ውስጥ ብዛት ያለው ወርቅና ብር እንዲሁም የሰዎችን አስከሬን በደብረ ታቦር፣ በጢስ አባይ እንዲሁም በለሎች ስፍራዎች ጥሎ መሸሹን ገልፀዋል::

“እስካሁን ያላወቅነው የተገኘው አፅም ሁኔታ ነው…የተገኘው አፅም በጨካኙ ፋሽሽት የተጨፈጨፉ ሴቶችን ጭምር እንደሆኑ ነው። በመጨረሻም ሁላችንም ታሪክ ሠራን! ምንም እንኳን የሕይወትን አስከፊ ገፅታ እንድናይ ብንገደድም በምንም አይነት ምክንያት ሀገራችንን በባእድ (በጠላት) እጅ አሳልፎ ሰጥቶ በነጭ መመራትና መገዛትን አለመፈለግ ነበር። ይህን በማድረጋችን ደግሞ ኩራት ይሰማናል::

“በአሁኑ ጊዜ ሁሉም በሕይወት ባይኖሩም ያለነውም በዕድሜ ገፋ በማለታችን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ባንችልም ተስፋችንና ምኞታችን ለአዲሱ ትውልድ በአደራ እንገልጻለን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያን ሁልጊዜም ከጠላት ነፃ አድርጋችሁ እንድትጠብቋት! እኛ ለእናንተ ውድ ሀገራችንን ያስረክብናት ተርበን፣ ተዋርደን፣ ተገድለን፣ በቆዳ በሽታ ተለክፈን… ለጠላት አንሸነፍም! በማለት ስለሆነ እናንተም ይህንን መጠበቅ እንዳለባችሁ አደራም እላለሁ!? ሌላ እንዳትረሱ የምለው እኛ ኢትዮጵያን የራሳችን የሆነውን ለሌላው አንሰጥም፤ የሌሎችንም አንፈልግም!”በማለት በቃለ ምልልሱ ወቅት  ለተተኪው ትውልድ ያስተላለፉትን መልእክት ፀሐፊው በመጽሐፋቸው አስፍረውታል::

ሌላዋ ሴት አርበኛ  ዘነበች ወልደየስ ይባላሉ፤ የ80 ዓመት አዛውንት ናቸው። “የሀገር ፍቅር ያደረብኝ ባለቤቴ ከማይጨው ጦርነት ድል አድርገው ከተመለሱ በኋላ ነው። ከዚያም በአምስት ዓመት የጣሊያን ወረራ መሳተፍ የጀመርሁት ታዳጊ እያለሁ ነው:: የውጭ ጠላት በአጭር ጊዜ በአካባቢዬ ቡልጋ ድረስ በመምጣት ቤቶችን፣ ከብቶችን፣ ንብረቱን… በእሳት አወደመ። ይህን የፈፀመን ጠላት ለመዋጋት ወደ ጫካ በመሄድ ከጦሩ ጋር ተቀላቀልሁ።

መጀመሪያ በአርበኝነት ያገለገለገልሁት ቀኛዝማች ልክየለህ በሚመሩት ጦር ሰር በኋላም ከራስ አበበ አረጋይ ጋር ነበር። የመዋጋት ልምድ ባይኖረኝም  የወገን ጦር በሠጠን ስልጠና በመታገዝ ጠላት ሀገሬን እንዳይወር በብርቱ ታግያለሁ::

“አብዛኞቹ  ሴት አርበኞች እንደኔው ነበሩ።  በወቅቱ ብዙም የጦር መሳሪያ አልነበረንም፤ መሳሪያ ያገኘነው ካለው ላይ በመግዛት ነበር:: ይህ ትግል ይካሄድ የነበረው ደግሞ በውስጥ አርበኞች አማካኝነት ነበር” በማለት ሀገርን በውጭ ጠላት ላለማስደፈር ያደረጉትን ትግል ከጅማሮው አንስተው ተናግረዋል::

መንግሥት የነበረው መሣሪያ የተከፋፈለው በከተማው ላሉት ተፋላሚዎች ነበር። በየጊዜው በሚማርኩት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እየታገዙ ለመዋጋት መቻላቸውን ተናግረዋል። ትግሉ የሚደረገው ደግሞ  አንድ ቦታ  ሳይሆን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ መሆኑ  ጥንካሬ ፈጥሮላቸዋል::

በአንድ ወቅት ካሉበት 50 ኪ.ሜ በምሥራቅ አዲስ አበባ፣ በደብረዘይት አጠገብ እና በዝቋላ ተራራ ላይ በመቆየት የጣሊያንን ጦር እንዳይጠጋ ሲጠብቁ እንደ ነበር የታሪክ ፀሐፊው በመጽሐፋቸው አስፍረዋል። ውጊያ በተካሄደባቸው ቦታዎች ጠላት በአየር እና በምድር በከባድ የጦር መሳሪያ ወገንን ያጠቃበትን እንዲሁም እርሳቸውን ጨምሮ አርበኞች ይህን ሁሉ በመቋቋም የጠላትን ኀይል በማድከም ወደ ከተማ የገባበት ጊዜም እንደነበር ያስታውሳሉ።

አርበኛ  ዘነበች ወልደየስ በተሳተፉባቸው ቦታዎች ሁሉ የአርበኝነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል:: በቆይታቸውም  በተለይ የማይረሱትን ገጠመኝ አስታውሰዋል፤ “ዋሲል በተባለ ቦታ ላይ ሰላሳ  አርበኞች ከጠላት ከሰማይ በተወረወረ ቦምብ ይገደላሉ፤ ከአርበኞቹ አንዱ  እግሩን  ተመቶ ሲወድቅ  አየሁት:: ይህ ጎበዝ አርበኛ የንጉሣችን የዘብ ጠባቂ ሆኖ ያገለግል  ነበር፤  በፍጥነት ሄጄም አንስቼ ከሱ እገዛ ጋር ባንዱ ትከሻዬ እሱን በሌላው ደግሞ ጠብመንጃዬን ይዤ ወደ ተራራው አጠገብ ወስጄ  በመደበቅ ከጠላት እጅ እንዳይወድቅ አድርጊያለሁ።

“ሌላው የማስታውሰው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ስንጓጓዝ ለካ እኔ ቀድሜ ከጦሩ በመገንጠል ርቄ ተጉዤ ከጠላት ጦር መሀል በድንገት ገብቻለሁ:: እዚህ ላይ ምን እንደሚሰማኝ ልትገምቱ ትችላላችሁ። እኔ ግን በፍጥነት በሩጫ ጥቅጥቅ ወዳለው ከሰም ወንዝ ( Kessem River ) አጠገብ ለአምስት ቀን በመደበቅ ከጠላት እጅ በማምለጥ ከወገን ጋር መቀላቀል ችያለሁ፤” በማለት በጥበብ ትግሉን እንደተወጡት አስታውሰዋል።

“በወረራው ወቅት ጠላት ሀገራችንን አልመራትም” የሚሉት አርበኛ  ዘነበች፤  አርበኞች በአንዳንድ የታወቁ ቦታዎች ላይ ቀድመው በመስፈር የመከላከያ ግንቦችን ማጠር እና ዙሪያውን መቆጣጠር በመቻላቸው ነው። በዚህም የጣሊያን ጦር ያደረገው የተወሰኑ ከተሞችን ከመቆጣጠር ኬላ ዘልቆ በመግባት ኢትዮጵያን በሙሉ ማስተዳደር አልተቻለውም። ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ስለሆነች ነው::

አርበኛ ዘነበች እንዳሉት “አንድ  የታዘብኩት ነገር ቢኖር ጣሊያኖች በራሳቸው ሕዝብ ላይ ፋሺስት ናዚ የፈፀመውን ጭፍጨፋ በየጊዜው ሲያወሱ፣ ፈፃሚውን ተጠያቂ ሲያደርጉ እንሰማለን::  አንድ ጣሊያናዊ አርበኛ ‘በነጻነታችሁ ቀን ምን ተሰማዎት?‘ ተብለው ሲጠየቁ ‘ በስሜ መጠራቴ  ነው ትልቁ ደስታዬ!‘ በማለት የሰጡትን ምላሽ  ሁሌም አልረሳውም:: እኛ ግን   እነሱ በሀገራችን ላይ የፈፀሙትን ሰቅጣጭ ጭፍጨፋ ዞር ብለው ለአንድ አፍታም እንዲያዩት አለማድረጋችን የእኛ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቸልተኝነት ነው እላለሁ” በማለት ነበር ቁጭታቸውን የገለጹት::

በአጠቃላይ የሀገራችን ክብር ለማዋረድ ለመጣ የውጭ ጠላት በርካታ ሴቶች በግንባር ከመፋለም ጀምሮ በጀግንነት ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ዘክረዋቸዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሚያዝያ 27  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here