አልዛሂመር ይረታ ይሆን?

0
100

የኒውሜክሲኮ የጤና ሳይነስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የመርሳት በሽታ መንስኤ የሆነውን ከአንጐል ህዋሳት  ውጪ የሚከማች የኘሮቲን ግግርን ለመከላከል ተስፋ ሰጪ ነው የተባለለትን ክትባት በሰዎች ላይ ለመሞከር መዘጋጀታቸውን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል::

በቅርቡ  “ዘጆርናል ኦፍ አልዛሂመር አሶሴሽን” አልዛሂመር እና ዳመእንቲያ የተሰኙ ህመሞችን ለመከላከል አስቻይ  አዲስ ግኝትን ለህትመት አብቅቷል:: የኒውሜክሲኮ የጤና ሳይንስ ማእከል የተመራማሪዎች ቡድን በምርምር ያገኘውን የመከላከያ ክትባት በአይጥ እና ዝንጆሮዎች ላይ ሞክሮ ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱን አብስሯል::

የተመራማሪዎች ቡድን መሪው ኘሮፌሰር ኪራን ብሃስካር እንደተናገሩት ክትባቱ በአይጦች እና ዝንጆሮዎች ላይ ተሞክሮ ተስፋ የፈነጠቀ በመሆኑ በሰዎች  ላይ ለመሞከር ተዘጋጅተዋል:: ይህንኑ ውሳኔያቸውን ማለትም የክትባቱን የመጀመሪያ ሙከራ ተግባራዊ ለማድረግ ለጋሽ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው መጠየቃቸውን ጠቁመዋል::

በሰዎች  አንጐል ውስጥ የሚከማች የኘሮቲን ቅሪት (ታው) ተጋግሮ የነርቭ ሴሎች እንዲረጉ ወይም እንዲጠጥሩ እና በሚያገኙት ክፍተት ሾልከው በመውጣት “የኒውሮዲጄኔሬሽን” በሽታን እንደሚያስከትሉ ነው ተመራማሪዎቹ ያብራሩት::

የመርሳት ህመም (አልዛሂመርን) ለመቆጣጠር ወይም ለህመሙ ፈውስ ለመሻት እስከ አሁን በርካታ ተመራማሪዎች ጥረት አድርገው መፍትሄ ያሉትን ያቀረቡ ቢሆንም ውጤታማ አለመሆኑን እና የረጋ ኘሮቲን ላይ ያነጣጠረው ግኝት የተሻለ እና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ነው የተመራማሪዎች ቡድኑ ያሰመረበት::

የድህረ ዶክትሬት ተባባሪ ተመራማሪዋ ኒኮል ማፊስ የኒውሜክሲኮ ዩኒቨርሲቲ ከመሰል ተቋማት ተመራማሪዎች ጋር በትብብር መስራቱ ክትባቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ አበርክቶው የጐላ መሆኑን ነው አፅንኦት ሰጥተው ያደማደሙት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here