በሩሲያ ከተሪንበርግ ከተማ ኗሪዋ የ80 ዓመት አዛውንት ከጋራ መኖሪያ ህንፃቸው ስድስተኛ ፎቅ መስኮት ወድቀው ቢወረወሩም ከስር በቆመ ተሽከርካሪ አናት ላይ በማረፋቸው በህይወት መትረፋቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::
አደጋው የደረሰው አዛውንቷ የመኖሪያ ክፍላቸውን መስታውት ውጪያዊ ገጽ እያፀዱ በነበረበት ወቅት ነው:: አስደንጋጩ አደጋ በህንፃው ላይ በተገጠመ የደህንነት መከታተያ ካሜራ የተቀረፀ ሲሆን ሁነቱ በማህበራዊ ድረ ገፆች በመለቀቁም እጅግ በርካታ ተከታታዮች ተመልክተውታል::
ድረ ገጹ እንዳስነበበው አዛውንቷ ከስድስተኛ ፎቅ ቁልቁል ተወርውረው በታችኛው ወለል ላይ በቆመች የጐረቤት ተሽከርካሪ ጣሪያ ላይ ካረፉ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በእግራቸው መራመድ ችለዋል::
አዛውንቷ ጐረቤታቸውን ጠርተው አብረው በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሄደው በመመርመር ደህንነታቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውም ነው የተገለፀው::
በሩሲያ “ኢ1 አርዩ” የተሰኘ መገናኛ ብዙሃን አዛውንቷ በራሳቸው ቸልተኝነት ወይም የጥንቃቄ ጉድለት መውደቃቸውን ነው የዘገበው:: የቀጣናው የፓሊስ ጽ/ቤት ባልደረቦችም በቦታው ተገኝተው የተለያዩ መረጃዎችን ሰብስበዋል፤ ምርመራ ባካሄዱበት የጤና ተቋምም ባለሙያዎችን ጠይቀው ምንም ዓይነት ጉዳት ሌላው ቀርቶ በአካላቸው ላይ ጭረትም እንዳልደረሰባቸው ነው ያረጋገጡት::
ከአዛውንቷ ይልቅ ያረፉበት የተሽከርካሪዋ ጣሪይ ጐድጐድ ማለቱን ብቻ ነው በፎቶግራፍ አንስተው ለእይታ ያበቁት::
በመጨረሻም ፓሊስ በሰጠው የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ሪፖርት አዛውንቷ በግዴለሽነት መውደቃቸውን ጠቅሶ ተጨማሪ ማስረጃ እና የተለየ መንስኤ መኖር አለመኖሩን ለመገንዘብ የማጣራት ስራው መቀጠሉን ነው በማደማደሚያነት ያሰፈረው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም