የኦሞ የታችኛው ሸለቆ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ነው የሚገኘው:: ሸለቆው 165 ኪሎ ሜትር ርዝመት ተለክቷል:: ሸለቆው ከቱርካና ሐይቅ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች የሚርቅ ሲሆን በዓለም በቅድመ ታሪክ ቅሪት መገኛነቱም ከፍ ያለ እውቅና አግኝቷል::
በሸለቆው ቀጣና ከተገኙ በርካታ ጥንታዊ ቅሪት አካላት በተለይም ሆሞግራሲሊስ በሰው ልጅ ቅድመ ታሪክ ዝግመተ ለውጥ (ኢቮሉሽን) ጥናት በአራት እግር ከመጓዝ ወደ ሁለት እግር የተደረገው ሽግግር ማረጋገጫ ቦታ ሆኗል::
በታችኛው የኦሞ ሸለቆ ውስጥ ለዘመናት የተነባበረው የደለል ክምችት የሰው ልጅ ያለፈባቸው መሰረታዊ የዝግመተ ለውጥ “ምእራፎች” አሻራ መገኛም ሆኗል:: በዚህም ቀጣናው የኮንሶ ፌጀጅ (የፓሊዮንቶሎጂ) ሳይንሳዊ የምርምር መዳረሻን አጠቃሎ ይዟል::
በኦሞ ሸለቆ የተገኙ ጥነታዊ ቅሪቶች ከአንድ እስከ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዬን ዓመታት እንደሚዘልቁ የባዮስትራቲግራፊ፣ ራዲዮ ሜትሪክ እና ማግኔቶ ስትራቲግራፊካል መለኪያ ሚዛኖች አረጋግጠዋል::
በኦሞ ሸለቆ ቀጣና ውሰጥ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የተቋቋመው ሳይንሳዊ የምርምር ጣቢያ ከየ አህጉራት እና አገራት ለሚሰበሰቡ በመስኩ የላቀ እውቀት ላላቸው ተመራማሪዎችም መዳረሻ ሆኗል::
የጥንታዊ ቅሪት ተመራማሪዎቹም በሸለቆ ወደተለያዩ ቀጣናዎች በመዘዋወር ባደረጓቸው ፍለጋዎች ሉሲን መሰል የቀደምት የሰው ዘር አብነቶችን በሳይንሳዊ መንገድ አረጋግጠው ለማስተዋወቅ እየተጉ መሆናቸው ነው በድረገፆች ለንባብ የበቃው::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ደብሊው ኤች ሲ ዩኔስኮ፤ ቪዚት ኢትዮጵያ ትራቭል እና አፍሪካ ዲስከቨሪን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም