ዘመናዊ የምርመራ ስልትን ለመጠቀም

0
77

ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ማህበረሰቡን የሚያውኩ እና እጅግ ዘግናኝ የሚባሉት ወ ናቸው፡፡  ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ከሚባሉት መካከልም የዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም፣ የጦር እና የወረራ ወንጀሎች ናቸው፡፡ ሕጉ ዓለም አቀፍ መንግሥታት ወንጀለኞችን እንዲከሱ እና እንዲቀጡ ግዴታ ለመጣል የወጣ ዓለም አቀፍ ሕግ  ነው፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው   እንዳሉት የፖሊስ ተቋም በተለያዩ ግጭቶች የሚፈጠሩ ውስብስብ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን  ምርመራ በማጣራት አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ተቋም ነው። በተለይም ደግሞ ውስብስብ እና ዓለም አቀፍ ባሕሪ ያላቸው እንደ ዘር ማጥፋት፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣  የጦር ወንጀል የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ  ወንጀሎችን  ለመከላከል፤ ተፈጽመው ሲገኙ ደግሞ በአግባቡ ምርመራ በማካሄድ ወንጀለኞችን ለፍትሕ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ ሥልጠናዎች   ለባለሙያዎች መስጠት አሥፈላጊ ነው።

ለዚህም የሚረዳ የሕግ ባለሙያዎች ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ምርመራ እና ክስ አመሠራረት ላይ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ አባላት ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ሥልጠና ሰጥቷል። የተሠጠው ሥልጠና የምርመራ ክፍተቶችን በመሙላት ለሕግ የበላይነት መከበር እና ለፍትሕ መረጋገጥ አቅም የሚፈጥር ስለሆነ ከሥልጠናው በኋላ  ዘመናዊ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም እና ዓለም አቀፍ የሕግ መርሆችን በመከተል ማኅበረሰቡን ማገልገል እንደሚገባ ረዳት ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።

በተለይም በአማራ ክልል ከተደረገው የሰሜኑ ጦርነት  አሁን ካለው የእርስ በርስ ግጭት ጋር ተያይዞ ወንጀል ሲከሰት  ፓሊስ በአግባቡ መመርመር እና ተጠያቂነትን መፍጠር የሚችልበት አቅም እንደሚፈጥር ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ኢንስፔክተር ትዕግሥት መንገሻ አንዷ ናት፡፡ ሥልጠናው በዓለም አቀፍ ወንጀሎች የምርመራ እና የክስ አመሠራረት እንዴት መተግበር  እንዳለበት   የምርመራ ሂደትን ለማዘመን እና አገልግሎት አሠጣጡን ለማቀላጠፍ በሚወጡ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሕጎች ምን ይመስላሉ? የሚለውን ተመልክተዋል፡፡ በቀጣይም በፓሊስ ምርመራ ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች ባለሙያዎች ሥልጠናዎችን ተደራሽ በማድረግ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ  ነው የገለፁት።

ሌላው የስልጠና ተሳታፊ ኢንስፔክተር መለሰ አምባቸው ሥልጠናው በየአካባቢው ከሚከሰቱ ወንጀሎች ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የወጡ ሕግችን አውቆ እና ቀድሞ ለመከላከል፣ ወንጀሉ ከተከሰተ ደግሞ ለመከታተል የሚያግዝ እንደሆነ ነው የገለፀው፡፡

በሥልጠናው ላይ ኢትዮጵያም የጄኔቫ ኮንቬንሽንን ጨምሮ እሱን ተከትለው የወጡትን ተጨማሪ ፕሮቶኮሎችን ያፀደቀች ሀገር መሆኗ ተመላክቷል፡፡ እነዚህን ሕጎች መሰረት በማድረግ በ1996 የወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ላይ የጦር ወንጀሎችን እና የሚያስከትሉትን ቅጣቶች በመዘርዘር አስቀምጣለች፡፡

የወንጀል ሕጉ ከአንቀጽ 270 እስከ 280 ባለው አንቀፆች ስር በዓለመወአቀፍ ስምምነቶች እና በጦር ሕጎች መሰረት ጥበቃ የሚደረግላቸውን መብቶች፣ የተደረጉ ክልከላዎችን እና ክልከላዎችን መጣስ የሚያስከትሉትን ተጠያቂነት እና ቅጣት በመዘርዘር አስቀምጦ ይገኛል፡፡

በጥቅሉ ዓለም አቀፍ ሕጉ የሉዓላዊ ሀገራት ግንኙነት የሚመራበትን የሕግ ማእቀፍ የሚደነግግ ሕግ ሲሆን ተፈጻሚነቱም እንደ ሕጉ ባህሪ በፈራሚ  እና በአባል ሀገራት ላይ ነው፡፡ ሀገራችንም ከዚህ አንጻር ያላት ዓለምአቀፍ ግንኙነት በዚሁ ሕግ አግባብ የሚመራ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በዘር ማጥፋት፣ በሰብአዊነት፣ በጦር  እና በመሳሳሉ ዓለም አቀፍ በሚባሉ ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ኢትዮጵያም ፈርማለች፡፡ በዚህ መሠረት በዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በጅምላ ጭፍጨፋ፣ በሰብዓዊ ወንጀሎች፣ በጦር ወንጀሎች፣ በማሰቃየት፣ ሰዎችን በመሰወር እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ሀገራት እርስ በርስ ይተባበራሉ።

ሀገራቱ ማስረጃ በመቀባበል፣ በምርመራ ሂደት በመተባበር፣ ተጠርጣሪዎች ወንጀል ከፈፀሙበት ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ተጉዘው ከሆነ ለፍርድ ወደ ሚያቀርባቸው ሀገራት አሳልፎ በመስጠት አሊያም ባሉበት ለፍርድ እንዲቀርቡ እና እንዲጠየቁ ለማድረግ ያስችላል።

ስምምነቱ ዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሥራ የሚደግፍ እንዲሁም ተጨማሪ የፍትሕ ሥርዓትን የሚፈጥር እንደሆነም በስልጠናው ላይ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ወንጀሎች የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ሸሽተው በተገኙበት ሀገር ፍርድ መስጠት የሚቻልበትን ሁኔታ ያመቻቻል።

በአጠቃላይ ሕጉ በሰለጠነው ዓለም ጦርነት የራሱ የሆነ ሕግና ሥነ ምግባር አለው፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገራት የተስማሙባቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያሉ ሲሆን የጦር ሕግጋት በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገራችን የወንጀል ሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸው እና ጥሰቶችም ሲከሰቱ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በስልጠናው ላይ የተገኙት የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የሥልታዊ ሙግት አሥተባባሪ ሜሮን ተስፋዬ እንዳሉት በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጸድቋል። ፖሊሲውን ለማስፈጸም በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ሕጎችም በመረቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ነው ለሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ድርጅትም ለሽግግር ፍትሕ ረቂቅ የሚሆኑ ግብዓቶችን እና ሥልጠናዎችን መስጠት አስፈላጊ የሆነው፡፡ በቀጣይም የሽግግር ፍትሕ ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት ብቁ የሆኑ የፍትሕ ባለሙያዎችን ለመፍጠር ሥልጠናው ትልቅ ትርጉም አለው፡፡

ሥልጠናው  በአማራ ክልል ለሚገኙ የፖሊስ አባላትን እና አቃቢ ሕጎችን  በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ዙሪያ የምርመራ እና የክስ አመሠራር ሂደት ላይ ያላቸውን ግንዛቤ የሚያሳድግ  እንደሆነም አረጋግጠዋል፡፡፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here