ለነገዎቹ ምሁራን

0
81

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 የትምህርት ዘመን  ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ቢያቅድም በክልሉ በተከሰተ የሰላም እጦት  በአሁኑ ወቅት በትምህርት ላይ የሚገኙት ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው::  ቢሮው የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በተያዘው ወር /ሚያዝያ/ በተለያዩ ቀጣናዎች ባካሄደበት ወቅት በዓመቱ በተማሪ ምዝገባ ማሳካት ያልቻለውን በውጤት ለማካካስ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተመላክቷል:: የግምገማው ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም ግጭቱ በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ከማሳወቅ ባለፈ ለመፍትሔዎችም ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል::

በሰሜን ወሎ ዞን 243 ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር እንዳልጀመሩ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሰጠ ታደሰ የክልሉ ትምህርት ቢሮ በደሴ ከተማ አዘጋጅቶት በነበረው የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ወቅት አስታውቀዋል:: በዚህም በአሁኑ ወቅት በትምህርት ላይ የሚገኙት ከ64 በመቶ እንዳይበልጡ ሆኗል:: በትምህርት ላይ ያሉት በዓመቱ ማጠናቀቂያ በሚሰጡ ፈተናዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ አስታውቀዋል::

የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዓለምነው አበራ በበኩላቸው በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ በርካታ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል:: በአሁኑ ወቅት በመማር ላይ የሚገኙት 452 ሺህ ተማሪዎች ሲሆኑ ይህም የዕቅዱ 58 በመቶ ነው::

በትምህርት ዘመኑ በምዝገባ የታጣው በውጤት እንዳይደገም ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎችን የሚወስዱ ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ኃላፊው አረጋግጠዋል:: በዞኑ ከሚገኙት 68 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 54ቱ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ያስፈትናሉ:: ቤተ መጻሕፍት ቤትን ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በሳምንቱ ሁሉም ቀናት ክፍት በማድረግ ተማሪዎች በሰፊው እንዲገለገሉ እየተደረገ ነው:: የአዳር ጥናት፣ የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርትም በተጠናከረ መንገድ በመስጠት ውጤትን ለማሻሻል በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ዓለምነው አስታውቀዋል::

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ክንዱ ዘውዱ በጉባኤው ላያ እንደተናገሩት በዞኑ ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎች ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎችን ይወስዳሉ:: ከዚህ ውስጥ ስምንት ሺህ 300 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ናቸው:: ቀሪዎቹ ከ29 ሺህ በላይ ተማሪዎች የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ተፈታኞች ናቸው::

ዞኑ ተፈታኝ ተማሪዎችን በማብቃት ላይ እያከናወነ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል:: ይህም በተማሪ ምዝገባ የታጣውን በውጤት ለማካካስ ለሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያምናሉ:: በዞኑ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የአዳር ጥናት እና የተማሪ ምገባ ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ መልካም ውጤት እንደሚያስገኝ ታምኖ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል:: የቤተ ሙከራ እና የቤተ መጻሕፍት አጠቃቀምን ማሻሻልም ለተማሪዎች የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት አንዱ ነው::

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሕዝቡ እና ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተገኘ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተለያዩ የትምህርት ግብዓት ለማሟላት እና የመምህራንን አቅም ለማሳደግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል::

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል  ኃላፊ መኳንንት አደመ  አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የአዳር ጥናት መጀመራቸው፣ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የቤተ መጻሕፍት የመጠቀሚያ ጊዜን በማሻሻል  ተማሪዎችን ለተሻለ ውጤት የማብቃት ሥራም በልዩነት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል:: በተመረጡ መምህራን አማካኝነት የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም አረጋግጠዋል:: በግጭቱ ምክንያት በተማሪዎች የተፈጠረው ሥነ ልቦናዊ ስብራት  ውጤታቸው ላይ አሉታዊ ጫና እንዳያሳድር በዘርፉ በሰለጠኑ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሥነ ልቦና እና የማነቃቂያ መርሀ ግብሮችን ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም አመላክተዋል::

እንደ አቶ አደመ ማብራሪያ በተያዘው የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልም ትኩረት ተደርጓል:: በዚህም ከኅብረተሰቡ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተመተባበር ከ900 በላይ ሕንጻዎች በግንባታ ላይ ናቸው:: ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ ተጠናቀዋል:: ይህም  ሕዝቡ የትምህርት ተቋማትን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ተሳትፎ ያመላክታል:: በዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ 50 በመቶ መሳካቱን ገልጸዋል።

በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ጉዳዮች አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ግጭቱ በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረውን ጫና አንስተው የቀጣይ አቅጣጫዎችን ጠቁመዋል:: መምህራን ትውልድ ለመገንባት ደፋ ቀና ባሉ ለእገታ፣ ድብደባ እና ግድያ መዳረጋቸውን ለግጭቱ ተጽእኖ ማሳያ አድርገው አንስተዋል:: ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችም በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ውጪ መሆናቸው  የሚያሳርፈው ዳፋ በአማራ ክልል ብቻ ሳይወሰን የዓለም ማኅበረሰብን በእጅጉ የሚጎዳ እንደሆነ አስታውቀውዋል::

የጸጥታ ችግሩ በክልሉ የትምህርት ዘርፍ ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ከፍተኛ የትውልድ ክፍተትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል:: በመሆኑም ችግር ላይ ያለውን የትምህርት ዘርፍ በመታደግ ተወዳዳሪ እና ተመራማሪ ትውልድ ለመፍጠር ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል:: በምዝገባ የታጣውን በውጤት ለማካካስ በትምህርት ላይ ሚገኙትን 40 ከመቶ ተማሪዎች ውጤት ማሻሻል ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here