የዓለማችን ከባዱ ጦርነት

0
96

ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በዓለማችን እየተደረገ የሚገኝ ከባድ ጦርነት እንደሆነ  ይነገርለታል፡፡  ጦርነቱ ታዲያ ብዙ ግምቶች እየተሰጡበት  ቀጥሏል፡፡ አሜሪካ በአዲሱ ኘሬዝዳንቷ በዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት “አስቆመዋለሁ፤ ሁለቱንም ወደ ሰላም  አመጣቸዋለሁ” የሚል ተስፋ ሰንቃ ነበር፡፡ አሜሪካ ይህንን ትበል እንጂ እስካሁን ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡

በአውሮፓዊያን እና በአሜሪካ የጦር መሳሪያ ድጋፍ አለሁልሽ እየተባለች ዩክሬን ጦርነቱን ቀጥላለች፡፡ሩሲያም በኢራን እና በሰሜን ኮሪያ ድጋፍ የራሷን ኃያልነት በመጠቀም መቋጫ የሌለው በሚመስለው ጦርነት ተዘፍቃለች፡፡

ከግሎባል ኮንፍሊክት ትራከር ድረገጽ //www.global-conflicttracker// ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ከሆነ እ.አ.አ. ከጥር 2022 ጀምሮ ዩክሬን ከ118 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከአሜሪካ እና  407 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ ደግሞ   ከሌሎች ሀገራት ተቀብላለች። በጦርነቱ ከ40 ሺህ በላይ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ አራት  ሚሊዮን ሰዎች  የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሆነዋል፡፡ ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮኑ  ከዩክሬን ተሰደዋል። 14   ሚሊዮን 6 መቶ ሰዎች ደግሞ ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ለሁለቱ ሀገራት ጦርነት መባባስ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች መኖራቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዩክሬን በኩል የምዕራባዊያን ጣልቃገብነት ሲጐላ በሩሲያ በኩል ደግሞ እንደ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ያሉ ሀገራት  በጣልቃ ገብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከሰሞኑም ሰሜን ኮሪያ ወታደሮቿ በኩርሱክ ግዛት ለሩሲያ እየተዋጉ እንደሚገኙ ማመኗ የሚታወስ ነው፡፡ ይህም በጐረቤቷ ደቡብ ኮሪያ በኩል ከፍተኛ ውግዘት አስከትሎባታል፡፡

የአሜሪካ እና የዩክሬን የደኀንነት ምንጮች ግን ቀደም ሲል የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያ እንደሚገኙ ጠቁመው ነበር፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው ሩሲያ ሰሜን ኮሪያ የሠራችላትን ውለታ ለመመለስ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማንኛውንም ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች፡፡

ኩርሱክ በሁለቱ ኃይሎች ጠንካራ ፍልሚያ የተደረገባት ግዛት ነች፡፡ በተለይም ዩክሬን ሩሲያን ለማስገደድ የምትችልበት አንዱ መንገድ የኩርሱክ ግዛት ናት ብላ ታምን ነበር፡፡ ከባድ ተጋድሎም ያደረገችባት ከተማ ናት፡፡  ከስምንት ወራት የዩክሬን ሰራዊት ቆይታ በኋላ ነው ኩርሱክ በሩሲያ ወታደሮች እጅ የገባችው፡፡ ይሁንና ዩክሬን አሁንም ወታደሮቿ በኩርሱክ ግዛት እየተፋለሙ እንደሚገኙ ነው ያስታወቀችው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ድብደባ  እንድታቆም ጠይቃለች፡፡ የአሜሪካ ኘሬዝዳንት ዶናልድ ትራምኝ ሩሲያ ድብደባዋን ካላቆመች አሜሪካ የማደራደር ሥራዋን እንደምትተው ነው የገለጹት፡፡ትራምፕ ከሰሞኑ እንደገለጹት ሩሲያ ያለማቋረጥ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመው የቦንብ ናዳ በእጅጉ አበሳጭቷቸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የሮማዉ ጳጳስ የቀብር ስነ- ስርዓትን ምክንያት በማድረግ ወደ ቫቲካን ያቀኑት ቬሎድሚር ዘሌንስኪ ከትራምፕ ጋር እንደተነጋገሩ ተገልጿል፡፡ በሁለቱ መሪዎች ውይይትም ክርሚያን ለሞስኮ አሳልፈው ሊሰጡ እንደሚችሉ ፍንጭ ታይቷል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ስለ ውይይታቸው በጋዜጠኞች በተጠየቁበት ጊዜ ዩክሬን ክርሚያን ለሩሲያ እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

በተያያዘም ሩሲያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በሰርጌይ ላቭሮብ በኩል በዩክሬን ላይ ከሰሞኑ እያካሄደችው ያለው ድብደባ ንፁሃን በሌሉበት እንደሆነ አረጋግጣለች፡፡ ኢላማ ያደረገችውም ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ብቻ እነደሆነ ጠቁማለች፡፡ ሚኒስትሩ ሩሲያ የዩክሬንን የጦር አቅም ለማዳከም ያለመ ጥቃት በቀጣይም እንደምትፈጽም ነው አስረግጠው የተናገሩት፡፡

አውሮፖዊያን ዩክሬንን በወታደራዊ ኃይል በማጠናከር ማንበርከክ እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ አዲሱ የአሜሪካው ኘሬዝዳንት ዶናልድ ትራምኘ ግን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ጦርነት አያስፈልግም የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ እንዲሁም አሜሪካ ዩክሬን በሩሲያ የተያዘባትን ቦታዎች በኃይል ልታስመልስ አትችልም የሚል እምነት እንዳላት ምክትል ኘሬዝዳንቷ ጄዲ ቫንስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ ሩሲያም ሆነች ዩክሬን ከፍተኛ የሰብዓዊ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደሚገቡ ነው የተናገሩት፡፡ በተለይም በርካታ ዜጐቻቸው ለህልፈት እንደሚዳረጉ ነው እየተነገር የሚገኘው፡፡ የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ካልታቋጨ በቀጣይ የኑክሌር ጦርነት ሊያስከትል እንደሚችል ነው ስጋታቸውን ያስቀመጡት፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ሩሲያ 80ኛ ዓመት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የድል በዓልን ለማክበር ሽርጉድ እያለች ትገኛለች፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግም የተናጠል የተኩስ አቁም ለማድረግ መወሰኗን አሳውቃለች፡፡ እ.አ.አ. ከግንቦት 8 እስከ 10 የሚቆይ የሦስት ቀናት የተኩስ አቁም ነው ያወጀችው፡፡ ሩሲያ በናዚ ጀርመን ላይ ድል የተቀዳጀችበት በአሏን ነው የምታከብረው፡፡ “ለሰብዓዊነት በሚልም የተኩስ አቁም አደርጋለሁ” ነው ያለችው፡፡ ለ72 ሰዓታት ባወጀችው የተኩስ አቁም ዩክሬን ጥሪውን እንድትቀበል ጠይቃለች፡፡ ዩክሬን ተኩስ የማታቆም ከሆነ ግን ከሩሲያ በኩል የከፋ ምላሽ እንደሚጠብቃት ነው ያስጠነቀቀችው፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በአንድሪስ ኢቫኖቪች በኩል ምላሽ የሰጠችው ዩክሬን ከሦስት ቀኑ በፊት ለ30 ቀናት የተኩስ አቁም ታውጆ አልነበረም ወይ የሚል ጥያቄ  አንስታለች፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው የአውሮፓ ሀገራትም የሩሲያ  የሦስት ቀናት የተናጠል ተኩስ አቁም አልተዋጠላቸውም፡፡ሩሲያ ይህንን የወሰነችው ሌላ ማግኘት የምትፈልገው ነገር ስላለ ነው ይላሉ አውሮፓዊያኑ፡፡

ዩክሬን የሁሉቱ ሀገራት ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እነዲቋጭ መጀመሪያ ሩሲያ በጦርነት የያዘችውን አራቱን ግዛቶች ጨምሮ ያለጦርነት ከ10 ዓመት በፊት የያዘቻትን የክርሚያ ግዛት  እንድትመልስ ጠይቃለች፡፡ ሩሲያ በበኩሏ የያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶችን እንደማትመልስ፣ ዩክሬን የኔቶ አባል እሆናለሁ የሚለውን ጥያቄዋን እንድትተው እና ጦሯ ጠንካራ እንዳይሆን ትፈልጋች፡፡ ታዲያ የሁለቱ ሀገራት ፍላጐት አራምባ እና ቆቦ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም ይፈጥራሉ ብሎ ማሰብ የማይቻል አደርጎታል፡፡

ዩክሬን የኔቶ አባል ሀገር እሆናለሁ የሚለው ጥያቄዋ እና ፍላጐቷ ለሁለቱ ሀገራት የጦርነት መነሻ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ዩክሬን በሩሲያ በሚደርስባት ጠንካራ ቡጢ እና በአሜሪካ በሚደርስባት ጫና ግዛቶቿን ለሩሲያ አሳልፋ ትሰጣለች በሚል የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ስጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 20 በመቶ የሚሆነው የዩክሬን መሬት በሩሲያ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡ ሉሀኑስክ፣ ዶንተስክ፣ ዛፖራዚያ፣ ኬህርሶን እና ክርሚያ በሩሲያ  ቁጥጥር ስር ናቸው፡፡ በተለይ ጀርመን ዩክሬን ግዛቶቿን አሳልፋ በመስጠት ሰላም አመጣለሁ የሚል አስተሳሰብ እንዳይኖራት አስጠንቅቃለች፡፡

የፓለቲካ ተንታኞች ዶናልድ ትራምፕ በዘሌንስኪ ላይ ጫና እያሳደሩ ነው የሚል ምልከታ አላቸው፡፡ይህ በእንዲህ እያለ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ያለው መረጃ እንደሚያመላክተው አሜሪካ በምትፈልገው ፍጥነት ሰላም አይመጣም ይላል የክሬምሊን መግለጫ፡፡

ቭላድሚር ፑቲን ለሰላም ክፍት ናቸው፡፡  ይህን ለማሳካትም ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የጠቆመው የክሬምሊን መግለጫ ነገር ግን የሚፈለገው ሰላም አሜሪካ በምትፈልገው ፍጥነት አይመጣም ሲል ማስታወቁን  ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የአውሮፓ ኅብረት ክርሚያን እንደ ሩሲያ አካል እንደማይቀበል ሲያሳውቅ በሌላ በኩል 600 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ለሩሲያ በዩክሬን ላይ ሲዋጉ መገደላቸውን ደቡብ ኮሪያ ገልጻለች፡፡ ዘሌንስኪ በበኩላቸው ሩሲያ በወታደራዊ ልምምዶች ሽፋን በቤላሩስ ‘አንድ ነገር እያዘጋጀች’ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል፡፡ኪቭ ኢንዲፔንደት ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው የዩኤስ-ዩክሬን ማዕድን ፈንድ በወራት ውስጥ ሥራ ሊጀምር እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ምንም እንኳን እርግጠኛ ባይሆኑም የዩክሬን ባለስልጣናት ስምምነቱን በዶናልድ ትራምፕ ስር የአሜሪካን ድጋፍ ለማነቃቃት የሚረዳ የፖለቲካ ምዕራፍ ነው ብለውታል።

ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ያደረገችውን ታሪካዊ የማዕድን ስምምነት “በዩክሬን ውስጥ ጉልህ የሆነ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችል መሠረታዊ የዕኩል ስምምነት” ሲሉ ገልፀውታል።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here