የአርበኞች ቀን እንደ ዓድዋ

0
70

የአርበኞች መታሰቢያ የድል ቀን እንደ ዓድዋ ሁሉ በመንግሥት ደረጃ ታስቦ እንዲውል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ጠየቀ

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በያመቱ ሚያዚያ 27 ታስቦ የሚዉለዉ የአርበኞች ቀን ዓድዋ በሚከበርበት አውድ ልክ በታላቅ ድምቀት መከበር እንዳለበት አሳስበዋል:: ፋሽስት ሞሶሎኒ ከ40 ዓመት ዝግጅት በኋላ ሰብቆ የመጣው ጦር በኢትዮጵያውያን ላይ ያስከተለው ሁለንተናዊ ኪሳራ ከፍተኛ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ሕልም የማይጨበጥ ጉም ያደረጉበት ጦርነት በመሆኑ ድሉ ከፍ ያለ ቦታ ላይ እንዲቀመጥ ያደርገዋል ሲሉ ምክንያታቸውን አንስተዋል::

የአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገሩን አሳልፎ ላለመስጠት ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉበትም ጭምር ነው:: ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ አርበኛ መሆናቸው በተግባር የተገለጠውም በዚህ ጦርነት ነው::፡ ኢትዮጵያውያን በሚያውቁት ሁሉ በየፊናቸው ተሰልፈው ሀገራቸውን ከወረራ መታደጋቸውን ልጅ ዳንኤል አዉስተዋል :: ይህም አንድነት ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ባህል፣ ወግ እና አጠቃላይ ማንነታቸው ኮርተው እንዲኖሩ እንዳስቻላቸው ይታመናል::

ጀግኖች አርበኞቻችን ከአድዋ ድል በሃላ የአምስት አመቱን ጦርነት በዳግም አሸናፊነት በማጠናቀቅ ሚያዚያ 27  1933 ዓ/ም ኢትዮጵያ ሰንደቃላማዋን የሰቀለችበት ዕለት በመሆኑ መታሰቢያ ቀኑ ከፍ ባለ መንፈስ ሁሉም አስቦት ሊውል እንደሚገባ ልጅ ዳንኤል አሳስበዋል:: የዘንድሮው የድል መታሰቢያ በዓልም ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ አራት ኪሎ የድል አደባባይ ተከብሮ እንደሚውል ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል:: በመሆኑም በቦታው ተገኝቶ በዓሉን ማክበር የማይችል ዜጋ በአባቶቹ ታሪክ የሚመካ እና አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚተጋ ትውልድ መፍጠር በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ውሎውን እንዲያደርግ ተጠይቋል:: ዕለቱን አስመልክቶ ታሪኩን ለልጆቹ ማሳወቅ ደግሞ ዋናው የዕለቱ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን አሳስበዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here