“እንኳንም ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ” እንዲሉ በኢዝላማባድ እና በኒው ዴልሂ መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነት ከሰሞኑ ተባብሷል፡፡ በሁለቱ ሀገራት የባለቤትነት ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባት አወዛጋቢዋ የካሽሚር ግዛት ዛሬም እንደ ትላንቱ ሕንድን እና ፓኪስታንን ጦር አማዝዛለች፡፡
ሕንድ እና ፓኪስታን መላውን የካሽሚር ክልል የይገባኛል ጥያቄን ባለማቆማቸው ቀጣይነት ወዳለው ውጥረት እና ግጭት አምርተዋል። ኒዮርክ ታይምስ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው እ.አ.አ ከ1947 እስከ 1948 ለአንድ ዓመት የቆየ ጦርነት በማድረግ ሁለቱ ሀገራት የካሽሚር ግዛትን ተከፋፍለውታል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል በካሽሚር ላይ የተደረገው የመጀመሪያው ጦርነት በቀጣዩ ዓመት እ.አ.አ በጥር 1949 በተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ ገብነት ከተጠናቀቀ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ሰላም ወርዷል። በተኩስ አቁም ውል መሰረትም ግዛቱን የሚከፋፍል መስመር ተዘርግቷል። በዚህም ሕንድ ከአካባቢው 55 በመቶ የሚሆን ክፍሉን ስትይዝ ፓኪስታን ደግሞ 30 በመቶ የሚሆነውን የግዛቲቱን ክፍል ተቆጣጥራለች፡፡ ሆኖም ሁልጊዜ አንዱ በአንደኛው ላይ ለሚደርስባቸው የሽብር ጥቃት ጣት ሲቀሳሰሩ ኖረዋል፡፡ ግፋ ሲልም ለሳምንታት የዘለቀ ጦርነት በማድረግ አቅማቸውን ሲፈታተሹ ኖረዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ግጭት ከሰሞኑ ያገረሸው በሚያዝያ 22 ቀን 2025 በሕንድ በሚተዳደረው ካሽሚር በፓሃልጋም ከተማ ውስጥ የፓኪስታን ታጣቂ ቡድን በቱሪስቶች ላይ ጥቃት በማድረሱ ነው። በሕንድ እንዲህ ዓይነት ክስተት ሲያጋጥም ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ነው ተብሏል። እ.አ.አ. ከ2008 የሙምባይ ግድያ በኋላ በሕንድ ውስጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የከፋው ጥቃት ተብሎ ተፈርጇል።
ሕንድም በአጸፋው ከሰሞኑ (ግንቦት 7 ቀን 2025) ከእኩለ ሌሊት በኋላ በፓኪስታን ቁጥጥር ስር የሚገኙ ግዛቶችን በመምታቷ የ31 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ጥቃት ፈጽማለች፡፡
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህ ባዝ ሻሪፍ ድርጊቱን “የጦርነት ድርጊት” ብለው ጠርተውታል፡፡ ለሕንድ ድርጊት ተስማሚ ምላሽ እንደሚሰጡም ነው ያስታወቁት። “የሕንድ ጊዜያዊ ደስታ በጽኑ ሐዘን ይተካል” ሲሉ ነው የዛቱት።
የፓኪስታን የመከላከያ ሚኒስትር ካዋጃ መሐመድ አሲፍ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ “አጸፋው ቀድሞውኑ ተጀምሯል። ውጤቱን ለማስተካከል ብዙ ጊዜ አንወስድም” ነው ያሉት።
ሕንድ 25 ዜጎቿንና እና አንድ የኔፓል ዜጋን ገድሎ በደርዘን የሚቆጠሩትን ባቆሰለው የፓሃልጋም ጥቃት ፓኪስታንን እጇ አለበት ስትል ከሳለች። ይሁንና የፓኪስታን መንግሥት ክሱን ውድቅ በማድረግ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።
በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አዋሳኝ ድንበር ላይ በሕንድ እና በፓኪስታን ወታደሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ፣ በሁለቱም በኩል ያሉ ዲፕሎማቶችን እና ዜጎችን ማባረር፣ የእርስ በርስ የአየር ክልል መዝጋትን እና የንግድ እንቅስቃሴ መቋረጥን ጨምሮ በሁለቱም ወገኖች ያለው እሰጣ ገባ አይሏል። ሕንድ ከሕንድ ወደ ፓኪስታን የሚፈሰውን የውኃ (የኢንደስ ወንዝ) ፍሰት እንደምታቆም ተናግራለች። ይህን እርምጃ የፓኪስታን ባለሥልጣናት እንደ ጦርነት ይቆጠራል ነው ያሉት።
የግንቦት 7ቱ የአየር ድብደባ በሕንድ ባለሥልጣናት “ኦፕሬሽን ሲንዶር” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤስ.ጃይ ሻንካር በኤክስ ገጻቸው ላይ “ዓለም ለሽብርተኝነት ምንም ትዕግስት እንደሌለው ማሳየት አለበት” ብለዋል። በዋሽንግተን የሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ሕንድ ቴክኒካል ግብዓቶች፣ የተረፉ ሰዎች ምስክርነት እና በፓኪስታን ላይ የተመሠረቱ አሸባሪዎች በሚያዚያው 22 ቀን 2025 እ.አ.አ ጥቃት ላይ ግልጽ ተሳትፎ እንዳላቸው የሚጠቁሙ ናቸው ብለዋል፡፡
የሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪክራም በበኩላቸው በኒው ዴልሂ በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ሕንድ ላይ ተጨማሪ ጥቃቶች ሊፈጸሙ እየተቃረቡ መሆናቸውን የሚጠቁሙ የስለላ መረጃዎች በመኖራቸው ህንድ አስቀድማ ጥቃቱን መሰንዘሯን ነው የጠቆሙት፡፡
የሕንድ መከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው እንዳስታወቀው የሚሳኤል ጥቃቶቹ የተፈጸሙት በሕንድ ላይ የሽብር ጥቃት በታቀዱባቸው ቢያንስ ዘጠኝ ቦታዎች ላይ ነው። መግለጫው አክሎም የፓኪስታን ወታደራዊ ተቋማት ምንም ኢላማ አልተደረጉም፡፡
የፓኪስታን ባለሥልጣናት በበኩላቸው እንደተናገሩት የሕንድ ጥቃት መስጊዶችን ጨምሮ በሲቪል መገልገያ ተቋማት እና መሰረተ ልማትን ኢላማ ያደረገ ነው። የፓኪስታን ባለሥልጣናት በጥቃቱ ከተገደሉት ሲቪሎች መካከል የሦስት ዓመት ህጻን ልጅ እንደምትገኝ ተናግረዋል። እንዲሁም በፓኪስታን በሚተዳደረው ካሽሚር ውስጥ በሚገኘው የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ላይ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በመመታቱ የፓኪስታን ጦር ኃይል የሕንድን ጥቃት የዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ የጣሰ ነው ብሎታል።
ፓኪስታን በጥቃቱ ምክንያት በካሽሚር እና በፑንጃብ ግዛት የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች። በርካታ በረራዎችም ተሰርዘዋል፤ የበረራ አቅጣጫም ቀይረዋል።
የፓኪስታን አየር ኃይል ለጥቃቱ አጸፋ አምስት የሕንድ ጄቶችን መትቶ እንደጣለ አስታውቋል፡፡ ሁለቱ የጦር ጄቶች ሕንድ በምትቆጣጠረው የካሽሚር መንደሮች ውስጥ የሚገኝ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ህንጻዎች ላይ መውደቃቸውን ነው ፓኪስታን ያስታወቀችው።
የሕንድ ባለሥልጣናት በበኩላቸው እንደተናገሩት ሕንድን እና ፓኪስታንን በሚለያዩ ድንበሮች ላይ የፓኪስታን ወታደሮች የዘፈቀደ ተኩስ በመክፈታቸው ቢያንስ ሰባት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከ46 በላይ ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ፓኪስታን በበኩሏ ሌሎች አምስት ንፁሀን ዜጎች በእነዚህ ድንበሮች ላይ በተተኮሰ ጥይት መሞታቸውን ተናግራለች።
የሕንድ የግድየለሽነት እርምጃ ሁለቱን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የታጠቁ መንግሥታትን ወደ ትልቅ ግጭት እየመራ እንደሆነ ነው የተነገረው። የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሌሎችም ፍጥጫው እና አጸፋዊ እርምጃው ፍጥነቱን እንዲቀንስ አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክሌር መሳሪያ የታጠቁ ጎረቤቶች ከፍተኛውን ወታደራዊ ገደብ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በመግለጫው ላይ “ቻይና የሕንድ ወታደራዊ ዘመቻ እንዳሳዘናት ገልጸዋል። አያይዘውም ሕንድ እና ፓኪስታን የሁልጊዜም ጎረቤታሞች እንደሆኑ እና ሁለቱም የቻይና ጎረቤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። አያይዘውም ቻይና ሁሉንም አይነት ሽብርተኝነትን እንደምትቃወም ጭምር ነው ያሳወቁት። ሁለቱ ወገኖች ለሰላምና መረጋጋት እንዲሠሩ፣ ተረጋግተው እንዲቆዩ እና ሁኔታውን የበለጠ ሊያወሳስቡ የሚችሉ እርምጃዎችን ከመውሰድ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ቻይና ቀደም ሲል ከፓኪስታን እና ሕንድ ጋር በሌሎች የካሽሚር ግዛቶች ላይ ቁርሾ ነበራት። እ.አ.አ በ1963 ከፓኪስታን ጋር የሁለቱን ሀገራት ድንበር ለመመስረት ስምምነት ላይ የደረሰች ሲሆን ሆኖም ሕንድ የዚያን ስምምነት ትክክለኛነት ውድቅ አድርጋ የቻይናን የምሥራቅ ካሽሚር ክፍልን የይገባኛል ጥያቄ ማቅረቧን ቀጥላለች።
ቻይና እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ በቻይና – ፓኪስታን ኢኮኖሚ ኮሪደር ላይ 62 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ ፓኪስታን ውስጥ ከፍተኛ ባለሃብት ሆናለች። ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል እንደ አስታራቂ ሆና ስትሠራ ቆይታለች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሕንድ በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካን ወታደራዊ መሳሪያዎችን በመግዛት ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራለች። ቀደም ሲል ኢዝላምባድ ከዋሽንግተን ጋር ጥብቅ ግንኙነት የነበራት ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን ፓኪስታን የጦር መሳሪያዋን ለማግኘት ወደ ቻይና ዞራለች።
ቤጂንግ ከቅርብ ወራት ወዲህ ከኒው ዴልሂ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እየሠራች ነው፡፡ ሆኖም አሜሪካ በበኩሏ በአካባቢው የቻይናን ተጽእኖ ለመቋቋም ከሕንድ ጋር ያለውን ግንኙነት ለዓመታት ስታዳብር በመቆየቷ ሕንድ ከቻይና ይልቅ ከአሜሪካ ጋር የበለጠ ተቆራኝታለች። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በትራምፕ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ብዙ ጊዜ ተገናኝተዋል። ሞዲ በየካቲት ወር(በ2025) ዋሽንግተንን በጎበኙበት ወቅት ስለ መከላከያ ግንኙነታቸው መወያየታቸው የሚታወስ ነው።
ሕንድ ከሰሞኑ በፓኪስታን ላይ ካደረሰችው ጥቃት በኋላ የአሜሪካው የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከሕንድ እና ከፓኪስታን የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪዎች ጋር በመነጋገር ሁለቱም ሀገራት “የግንኙነት መስመሮች ክፍት እንዲሆኑ እና መባባስ እንዳይፈጠር” አሳስበዋል።የኒውክሌር መሳሪያ ባለቤቶቹ ሕንድ እና ፓኪስታን ከአምስት ዓመት በፊትም በካሽሚር ግዛት ጉዳይ የቃላት ጦርነት ከማድረግ አልፈው ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ስጋት ፈጥረው እንደነበር የሚታወስ ነው። ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡም በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው። ዘንድሮም ታሪክ ራሱን ደግሞ በትራምፕ ጊዜ ሁለቱ ሀገራት ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
የሁለቱ ሀገራት ፍጥጫም የኃያላኑን ሀገራት ጎራ አሰልፎ ጦር እንዳያማዝዝ ስጋት ፈጥሯል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም