ክትባት በሽታን የመከላከል አቅምን በማጎልበት ህፃናትን ከህመም እና ከአካል ጉዳት ይከላከላል፡፡ የሞት ምጣኔንም ይቀንሳል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከግንቦት 6 እስከ 15 2017 ዓ.ም የኩፍኝ መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና አጠባበቅ ትምህርት እና የስነ – ተዋልዶ ጤና ባለሙያ ወ/ሮ የሺወርቅ አሞኘ ገልጸዋል፡፡ ባለሙያዋ እንደገለጹት በዚህ ዘመቻ ዕድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ አምስት ዓመት ለሆናቸው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለሦስት ሚሊዮን 749 ሺህ 171 ህፃናት ለመስጠት ዕቅድ ተይዟል፡፡
ኩፍኝ ተላላፊና በቫይረስ የሚከሰት በሽታ ሲሆን ሞት እና ከባድ ህመም ያስከትላል። በብዛት የሚተላለፈውም የኩፍኝ ሽፍታ ከመታየቱ ከአራት እስከ አምስት ቀናት ቀደም ብሎ ነው።
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ አብዛኛውን ጊዜ በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ያልተከተቡ ህፃናት ቁጥር ሲጨምርና የኩፍኝ ወረርሽኝ በሀገራችን በብዙ ቦታዎች ሲከሰት ሀገር አቀፍ ዘመቻ በመፍጠር ክትባት በዘመቻ መልክ ይካሄዳል፡፡ ክትባት ከመደበኛው ባሻገር በዘመቻ መልክ ሲሰጥም በመደበኛ ለተከተቡት ሁለተኛ ዕድል ሲፈጥርላቸው ላልተከተቡት ደግሞ ዕድል በመፍጠር በሺታውን መከላከል ያስችላል፡፡
መደበኛው ክትባት ዕድሜያቸው ከ45 ቀን ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት የሚሰጥ ሲሆን የኩፍኝ ክትባት ደግሞ ዘጠኝ ወር ለሞላቸው እና አንድ ዓመት ከሦስት ወር ጀምሮ ላሉ ልጆች ይሰጣል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በክትባት ልንከላከላቸው የሚችሉ በሽታዎችን ባለማስከተባችን ብቻ ሰዎች ለከፋ ሕመም እና ለአካል ጉዳት እና ሞት ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ የኩፍኝ ክትባት አንድ ጊዜ የወሰዱ ሰዎች 85 በመቶ በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸው ሲሆን 2ኛ ክትባት ሲወስዱ ደግሞ 95 በመቶ እና በላይ የመከላከል አቅማቸው ይጎለብታል፡፡
ግንቦት 6 2017 ዓ.ም የሚጀምረው የዘመቻ ክትባት መደበኛ ክትባትን እንደማይተካ የተናገሩት ባለሙያዋ ለ10 ቀናትም እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት፡፡
ከኩፍኝ ክትባት ጋር ተቅናጅተው እንዲሰሩ የጤና ሚንስቴር በሰጠው አቅጣጫ መሰረትም ተጨማሪ የጤና አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ነው ወ/ሮ የሺወርቅ የተናገሩት፡፡ በዚህ መሠረትም እድሜያቸው ከአንድ እስከ አምስት ዓመት ለሆናቸው ክትባት ያልጀመሩና ጀምረው ያቋረጡ ህፃናት የማካካሻ ክትባት ይሰጣቸዋል፡፡ እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች ለሆኑ በመደበኛ ክትባት መረሃ ግብር ያልተከተቡ እና ክትባት ጀምረዉ ያቋረጡ ህፃናት የመደበኛ ክትባት ይከተባሉ፡፡
ከአምስት ዓመት በታች የታመሙ ህፃናትን የመለየት እና ወደ ጤና ተቋማት ለህክምና መላክም ይከናወናል፡፡ በተፈጥሮ የከንፈር እና የላንቃ መሠንጠቅ አጋጥሟቸው ለተወለዱ እና በተፈጥሮ የተጣመመ እግር ኖሯቸዉ የተወለዱ ህፃናትንም በመለየት ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
እድሚያቸዉ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት፤ለነፍሰ ጡር እና ለአጥቢ እናቶች የአጣዳፊ ምግብ እጥረት ልየታ ይከናወናል፡፡ የቫይታሚን ኤ እንክብል ጠብታ፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትል መድኃኒት መስጠት፣ ከወሊድ ጋር የተያያዘ ፊስቱላ (ሽንት፣ ሰገራ፣ ወይም ሁለቱንም የመቆጣጠር ችግር ) እና የማህፀን መዉጣት ያጋጠማቸዉ እናቶች ልየታ እና ምርመራ እንደሚደረግላቸው ነው የጠቆሙት፡፡
አንዳንዴ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት የወሰዱ ልጆች ሲታመሙ ይስተዋላሉ እና ይህ ሚሆነው ለምንድን ነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ወ/ሮ የሺወርቅ አልፎ አልፎ የተከተቡ ህፃናት ሊታመሙ እንደሚችሉ እና ነገር ግን ህመሙ እንደማይጸናባቸው ነው የጠቆሙት፡፡
ወ/ሮ የሺወርቅ በጥናት የተረጋገጠ ብለው በሰጡን መረጃ መሠረት በተወለዱ በዘጠኝ ወራቸዉ የመጀመሪያዉን የኩፍኝ ክትባት የተከተቡ ህጻናት 85 በመቶ ብቻ የኩፍኝ በሽታን የሚከላከል አቅም ይኖራቸዋል፡፡ በተወለዱ አንድ ዓመት ከሦስት ወራቸዉ ሁለተኛዉን የኩፍኝ ክትባት የተከተቡ ደግሞ 95 በመቶ እና በላይ መከላከል እንደሚቻላቸው ነው የነገሩን፡፡ ነገር ግን 100 በመቶ (ሙሉ በሙሉ) በሽታን መከላከል የሚያስችል ክትባት እንደሌለ ነው የገለጹልን፡፡
በሽታው ከተከሰተ በኋላ ምን መደረግ አለበት? ለሚለው ጥያቄያችንም የታመሙ ህፃናትን በአካባቢው በሚገኝ የጤና ተቋም በመወሰድ ህክምና እና ምክር ማግኘት እንዳለባቸው ነው የመለሱልን፡፡ ለባለሙያዋ የኩፍኝ በሽታን በባሕላዊ መንገድ ማከም ይቻላል ወይ? ብለን ጥያቄ አንስተንላቸዋል።
የኩፍኝ በሽታ መንሳኤ ቫይረስ በመሆኑ በባህላዊ መንገድ ማከም እንደማይቻል ጠቁመው በተለምዶ ብዙ ጊዜ ሰዎች “ጥላ” ይሆናል በማለት ፊታቸውን ባለማጠባቸው ለከፋ የዓይን ህመም እንደሚጋለጡ ጠቁመው ከዚህ ድርጊታቸው መቆጠብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም