ሥራ ላይ ባለው የፌዴራል የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ውስጥ ጋብቻ ለሚለው ቃል ትርጉም በቀጥታ አልተሰጠም፡፡ ነገር ግን ከሕጉ የተለያዩ ድንጋጌዎች የቃሉን ትርጉም ማግኘት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ሀገሮች ግን ለቃሉ በቤተሰብ ሕጎቻቸው ትርጉም ለመስጠት ይሞክራሉ፤ ለምሳሌ የኢንዶኒዥያ የቤተሰብ ሕግ “ጋብቻ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ጥምረት በመፍጠር በፈጣሪ ፈቃድ ዘላቂና ደስተኛ ቤተሰብ ለመመስረት የሚደረግ ጥምረት ነው” በማለት ትርጉም ይሰጣል፡፡
ነገር ግን ይህ ትርጉም ጋብቻ የሚለውን ቃል በምዕሉነት የተረጎመ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተጋቢዎቹ በስምምነት የጋራ ቁሳዊ ጥምረት ሳይፈጥሩ በየግላቸው የግል ንብረቶችን እያስተዳደሩ በጋብቻ ተሳስረው መኖር ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ጋብቻ ለሚለው ቃል ሁሉን በአንድ የሚያስማማ ትርጉም ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ውስጥ በዋነኝነት በሦስት አይነት የጋብቻ ማስፈፃሚያ ሥርዓቶች እውቅና ተሰጥቷል፡፡
እነዚህም በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ በሃይማኖታዊ እና በባህል ሥርዓት መሠረት የሚፈጸሙ ጋብቻዎች ናቸው፡፡
ሦስቱም ዓይነት የጋብቻ መፈጸሚያ ሥርዓቶች በቅድሚያ ሚያሟሏቸው መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የሚጸና ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነፃና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ እንደሆነ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ ስድስት ላይ ተገልፆል፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34(2) ላይ “ጋብቻ በተጋቢዎቹ ነፃና ሙሉ ፈቃድ ላይ ብቻ ይመሰረታል” ይላል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም አይነት ጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓት ጋብቻ ቢፈጸምም የተጋቢዎቹ ነፃ እና ሙሉ ፈቃደኝነት አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላው የተጋቢዎች የዕድሜ ጉዳይ ነው፡፡ ጋብቻ ራሱን የቻለ ኃላፊነት የሚያስከትል በመሆኑ ወደ ጋብቻው የሚቀላቀሉት ተጋቢዎች ይህን ኃላፊነት መቀበል የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጤና አንጻር ወደ ጋብቻ የሚገቡ ሰዎች በእድሜያቸው ብቁ መሆን አለባቸው፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 7(1) ላይ ወንዱም ሆነ ሴቷ አስራ ስምንት ዓመት ሳይሞላቸው ጋብቻ መፈጸም እንደማይችሉ ይገልፃል፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ ይህ እድሜ ሳይሞላ በፍትሕ ሚኒሥቴሩ ከመደበኛ እድሜ ሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ በመቀነስ እንዲጋቡ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነው ከባድ ምክንያት ሲያጋጥም ብቻ ነው፡፡
ትዳር ለመመስረት ዝምድና የሌላቸው መሆኑ ሌላው መስፈርት ነው፡፡ ከህብረተሰቡ ሞራልና በጤና ምክንያት የተነሳ ተጋቢዎች የቅርብ ዘመድ (የስጋም ሆነ የጋብቻ ዘመድ) መሆን እንደሌለባቸው እሙን ነው፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 8 እና 9 ላይ ክልከላው በግልጽ የተቀመጠ ነው፡፡
የፀና ጋብቻ ያለው አንድ ሰው በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈፀም የተከለከለ ነው፡፡ ይህ ጋብቻ ጸንቶ እያለ ሌላ ጋብቻ መፈጸም እንደማይችልም የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ (አንቀጽ 11) ክልከላ ተጥሎበታል፡፡
ጋብቻ የቤተሰብ መመስረቻ መሰረታዊው እና ዋናው መንገድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቤተሰብ ደግሞ የህብረተሰብና የሀገር መሠረት እንዲሁም መሰሶ ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ እና የሀገር መሰሶ የሆነው ጋብቻ የተጋቢዎቹ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡ እና የሀገርም ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም የህብረተሰብ እና የመንግሥት ጥበቃና እንክብካቤ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ በመሆኑም ነው ጋብቻው ከመፈጸሙ በፊት መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታዎች ወይም ክልከላዎች የተቀመጡት፡፡
በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት እነዚህ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ጋብቻ ተፈጽሞ ሊገኝ ይችላል፡፡ ለአብነት በሕግ ከተደነገገው እድሜ በታች ወይም በቤተዘመዶች መካከል ጋብቻ ተፈጽሞ ሊገኝ ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ቅድመ ሁኔታውን አሟልቶ ያልተፈጸመ ጋብቻ ወይም ሊደረግ የታቀደ ካለ እንዳይፈጽም ወይም ሕጋዊ እርምት የመውሰድ ኃላፊነት ለመንግሥት እና ለህብረተሰቡ የተሰጠ አደራ ነው፡፡ ይህ ማለት በዓቃቤ ሕግ በኩል እና በተጋቢዎቹ ዘመዶች፣ በሌሎች ጉዳዩ ያገባናል በሚሉ የሕጻናትና ሴቶች መብት አስከባሪ ድርጅቶች እና በመሳሰሉት በኩል የሚከናውኑ ይሆናል፡፡
ጋብቻው እንዳይፈጸም መቃወም ወይም እንዲፈርስ ጥያቄ ማቅረብን የሚችሉት ወገኖች ማንነት የሚወስነው ለተቃውሞው መሠረት የሆነው ጉዳይ ማለትም ያልተሟላው ቅድመ ሁኔታ ይወስነዋል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የመቃወሚያው መሠረት በጋብቻ ላይ ጋብቻ ከሆነ ይህን ቀድሞ የጸና ጋብቻ ያለው/ያላት ባለትዳር ወይም ዐ/ሕግ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ጋብቻው ተፈጽሞ ከሆነ ደግሞ እንዲፈርስ አቤቱታ የሚቀርበው ለፍ/ቤት እንደሆነ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75(ለ)) ላይ ሰፍሯል፡፡ ነገር ግን ሊፈጸም የታቀደው ጋብቻ እንዳይፈጸም የሚቀርብ አቤቱታ ከሆነ የሚቀርበው ጋብቻውን ለሚያስፈጽመው ባለሥልጣን ነው፡፡ ይህም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 19 ላይ ተገልፆ ይገኛል፡፡
መቃወሚያ በጽሑፍ መቅረብ ያለበት ደግሞ እጅግ ቢዘገይ ጋብቻው ሊፈጸምበት ከታቀደው ቀን ቀጠሮ 15 ቀን በፊት መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ተቃውሞ የቀረበለት ተቋምም በሕግ በተቀመጠው አምስት ቀን ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡ ውሳኔው ተቃውሞውን ውድቅ ያደረገ እንደሆነ ውሳኔው የመጨረሻ ነው፡፡ ነገር ግን ውሳኔው ተቃውሞውን በመቀበል ጋብቻው እንዳይፈጸም የተወሰነ እንደሆነ ጋብቻው እንዳይፈጸም ማድረግ እና ይህንኑ ውሳኔ ወዲያው ለተጋቢዎች ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ተገቢዎቹም ይግባኛቸውን ለፍ/ቤት ማቅረብ ይችላሉ፡፡
ጋብቻ ተጋቢዎቹ በማህበረሰቡ ውስጥ በፊት ከነበራቸው ማህበረሰባዊ ቦታ ማለትም ለአቅም አዳም እና ሄዋን ደርሰው ከነበሩበት ወንደላጤነት እና ሴተላጤነት ወደ ሌላኛው ማህበረሰባዊ እርከን አባወራ እና እማወራ የሚቀየሩበት እና የማህበረሰብ መሠረት የሆነውን ቤተሰብ የሚመሰርቱበት ነው፡፡ ይህ የሚመሰረተው ጋብቻ ተጋቢዎቹ በፊት ከነበራቸው ግላዊ ህይወት ወደ ጋራ የሆነ ህይወት የሚያዘዋውራቸው ነው፡፡ በዚህ የጋራ በሆነ ህይወት ውስጥ ግላዊ ግንኙነታቸው ዘላቂ እና የተረጋጋ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ይህም ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ አለባቸው፡፡ ይህ የመተጋገዝ፣ የመከባበር እና የመረዳዳት ግዴታ በምንም ሁኔታ ተጋቢዎቹ ሊያስቀሩት የማይችሉት ግዴታቸው (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 49) ላይ ሰፍሯል፡፡
ተጋቢዎቹ ቤታቸው በፍቅር የደረጀ፣ መከባበር፣ መተሳሰብ እና መተጋገዝ የሰፈነበት እንዲሆን ባል እና ሚስት ቤትን በማስተዳደር እኩል የሆነ ሚና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በኢፌዲሪ ሕግ መንግሥት አንቀጽ 34(1) ላይ “ተጋቢዎች በጋብቻ አፈፃፀም፣ በጋብቻው ዘመንና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት አላቸው” ይላል፡፡ ይህ የሀገራችን የሕግ ሁሉ የበላይ የሆነ ሕገ መንግስት ባል እና ሚስት በትዳራቸው እኩል መብት እንዳላቸው ይገልፃል፡፡
የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 50 ላይም ባል እና ሚስት በቤተሰብ አመራር፣ ልጆች አስተዳደር እና የቤተሰቡን ደህንነት ጥቅም በማስከበር ላይ እኩል መብት ያላቸው መሆኑን ይገልፃል፡፡ በመሆኑም ቀደም ባሉ ጊዜያት በሰፊው ይስተዋል የነበረው ሴቶችን በጋብቻ ውስጥ የበታች አድረጎ የሚወስድ አስተሳሰብ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በማያሻማ ሁኔታ እንዲወገድ ተደርጓል፡፡
በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ /አንቀጽ 1 – 4/ በውጭ ሀገር የተፈጸመ ጋብቻ በዛ ሀገር ጋብቻ አፈፃፀም ሕግ መሠረት የተፈጸመ ከሆነ እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሞራል እስካልተቃረነ ድረስ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት በሦስት አይነት ስርዓቶች ከተፈጸሙ እኩል እውቅናና ተቀባይነት አለው፡፡
( ሙሉ ዓብይ)
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም