የጎንጂ ቆለላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከፍተኛ የአማራ ክልል የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል። ባለፉት ስምንት ዓመታት በግንባታ ላይ የነበረው ሆስፒታሉ በቶሎ ተጠናቆ አገልግሎት ባለመስጠቱ የወረዳው ነዋሪዎች እንግልት ሲደርስባቸው ቆይቷል።
በ105 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር የግንባታ ወጪ የተጠናቀቀው ሆስፒታሉ፣ በወረዳው ላሉ ከ136 ሺህ በላይ ሕዝብ ግልጋሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡
ሆስፒታሉ 99 የሕክምና አልጋዎች ይኖሩታል፡፡ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ መረጃ እንደሚያመላክተው በክልሉ ካሉት 101 ሆስፒታሎች መካከል አንደኛው ነው።
ወይዘሮ ሕብስቴ ጌቴ በጎንጅ ቆለላ ወረዳ አዲስ ዓለም ከተማ ነዋሪ ናቸው። በአካባቢው ከቅርብ መታከሚያ ሆስፒታል ባለመኖሩ አዴት እና ባሕር ዳር ድረስ በሰው ሸክም እየሄዱ ጤናቸውን ይከታተለሉ እንደ ነበር አስታውሰዋል። “በመንገድ ላይ ወላድ እናቶች ይንገላቱ እና ይሞቱ ነበር፤ ለከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እና እንግልት ይዳረጉ ነበር፤ ይህ ሆስፒታል ተመርቆ ወደ ሥራ ሲገባ ከዚህ ቀደም የነበሩ እንግልት እና የገንዘብ ወጪዎች ይቀንሳሉ። የእናቶች ሞትም ይቀንሳል” የሚል ሐሳብን ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳው ነዋሪ “ሆስፒታሉ በመመረቁ አይተን የማናውቀው እድል ነው ያገኘነው” ሲሉ ከዚህ ቀደም የገጠማቸውን ችግር በማስታወስ ሐሳብ ሰጥተዋል።
“ወንዶች እና ሕሙማንን በጋሪ እና በሰው ሸክም ነበር የምናጓጉዝ” አሁን ያ ሁሉ ችግራቸው እንደሚቀረፍ ተስፋን ሰንቀዋል፡፡ “የመኪና አገልግሎት ባለመኖሩ ታምሜ አዴት ድረስ በሸክም ወስደውኛል” ያሉት ሐሳብ ሰጪዉ “ከደጃፋችን መሠራቱ ያን ሁሉ ድካም የሚቀንስ ትልቅ ደስታ ነው” ብለውታል፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን ነፍሰ ጡር እናቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ ሕክምና ሳይሄዱ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸው፤ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ በማስገባት ቀልጣፋ አገልግሎት እንሰጣለን ብለዋል። ይህ ሆስፒታል ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ለወረዳው እና አጎራባች ወረዳዎችም አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት።
የበኩር ዜጣ ዘጋቢ በቦታው ተገኝቶ እንደታዘበው የተመረቀው ሆስፒታል ግንባታው ከመጠናቀቁ በስተቀር ማሽኖች፣ አልጋዎች፣ እና ሌሎች ቁሳቁሶች አልተሟሉለትም።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱል ከሪም መንግሥቱ “ሁሉም የሕክምና መሳሪያዎች ተገዝተዋል። የማጓጓዝ ስራ ይቀራል። የጸጥታ ችግር ነው እንጂ በቅርቡ ሁሉንም አስፈላጊ ቁስሳቁስ እና ግብዓት እናሟላለን” ሱሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሆስፒታሉን ስራ ለማስጀመርም የቅጥር እና ሰው ኀይል ማሟላት ሥራ መጀመሩን ቢሮ ኀላፊው በምረቃው ላይ ተናግረዋል። ለዚህ ሆስፒታል አንድ አምቡላስ እንዲሁም ለወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት ደግሞ አንድ አምቡላንስ ተበርክቷል።
የሕክምና ግብዓት እና ቁሳቁሶችን ወደ ወረዳው በማጓጓዝ በቅርቡ ሆስፒታሉ ሥራ እንዲጀምር በትኩረት እንሰራለን ሲሉም ቢሮ ኀላፊው ቃል ገብተዋል።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም