የተማሪ ምገባዉ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

0
76

በአማራ ክልል ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ በ2017 ዓ.ም ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ውጪ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ገበታ ላይ ሆነው በዓመቱ መጨረሻ ለሚሰጠው ፈተና ዝግጁ እንደሆኑ የተነገረው ደግሞ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ያህል ተማሪዎች ናቸው፡፡ በምዝገባ ማሳካት ያልተቻለውን በውጤት በማካካስ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ማፍራት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ዋና አጀንዳ ሆኖ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

ተመዘግበው በትምህርት ላይ የሚገኙትም በተለያዩ ምክንያቶች የጀመሩትን ትምህርት እንዳያቋርጡ ለማድረግ የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ በልዩ ትኩረት እየተሠራበት ነው፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በዓመቱ አንድ ሚሊዮን ተማሪዎችን በምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የተለያዩ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች ምገባን  በስፋት እያከናወኑ መሆኑ ቢነገርም አብዛኛዎቹ ትርፍ አምራች አካባቢዎች ግን አልጀመሩም ተብሏል፡፡ የጀመሩት ውጤቱን አይተው በቀጣይ እንዲያስፋፉ፣ ያልጀመሩትም ከጀመሩት ምን ውጤት እንደተገኘ ልምድ ቀስመው በቀጣይ እንዲጀምሩት የክልሉ ትምህርት ቢሮ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት ተጠይቋል፡፡

የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባን ከጀመሩ እና የዕቅዳቸውን ከ90 በመቶ በላይ ካሳኩ አካባቢዎች መካከል የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ይገኝበታል፡፡ በኩር በከዚህ ቀደም ዕትሟ በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ እና የተማሪ ምገባ ከጀመሩ ት/ቤቶች መካከል አንዱ በሆነው በቁልቋል ሜዳ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝታ የምገባ ፕሮግራም እንቅስቃሴውን መቃኘቷ ይታወሳል፡፡ ተማሪዎች በምገባው ተጠቃሚ በመሆናቸው ምክንያት የቀሪ እና አርፋጅ ተማሪ ቁጥር ዜሮ መድረሱን፣ የትምህርት አቀባበላቸው መሻሻሉን፣ ከትምህርት ውጪ ያለውን ጊዜያቸውን ከትምህርት ቤት ውጪ ሳይወጡ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ማስቻሉን፣ የውጤት መሻሻል መታየቱን ት/ቤቱ መግለጹ ይታወሳል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በባሕር ዳር ከተማ በገመገመበት ወቅት የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ  ኃላፊ  ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባን የተማረ እና ብቁ ዜጋ የማፍሪያ መንገድ አድርገን እየሠራንበት ነው ብለዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ዐሥር ሺህ ሕጻናት ቁርሥ ሳይበሉ ወደ ትምህርት ቤት እንደሚሄዱ ተናግረዋል፡፡ ቁርሳቸውን አዘግይተው ለመብላት ይዘው የሚመጡት ተማሪዎችም ቢሆን ከበቂ በታች የሆነ እና ያልተመጣጠነ ምግብ መሆኑን መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎች በቂ እና የተመጣጠነ ምግብ ካላገኙ በትምህርት አቀባበላቸው ዝቅተኛ ከመሆን ጀምሮ ማኅበራዊ ሕይወታቸው ችግር ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል፡፡ ይህም ተማሪዎች አዘውትረው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ፣ ቢሄዱም የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት እንዳይከታተሉ በማድረግ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩም አመጋገብ ከተማሪዎች አልፎ በሀገር ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ በመረዳት በሥሩ በሚገኙ 17 ትምህርት ቤቶች የተማሪ ምገባ እያከናወነ መሆኑን ኃላፊዉ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ዘጠኝ ሺህ 267 ተማሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ ምገባዉ መሠረት በሚያዝበት የቅድመ መደበኛ የት/ቤት ደረጃ ላይ ትኩረት ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ሦስት ሺህ 985 ተማሪዎች የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ማሳያ አድርገዋል፡፡ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ላይም ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡

የምገባ መርሀ ግብሩ ተሳታፊ የሆኑ አካላት እነማን ናቸው? የሚለውንም ገልጸዋል፡፡ ለምገባው ዕውን መሆን መንግሥት 20 ሚሊዮን ብር፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች 13 ሚሊዮን ብር እና ሕዝቡ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ለምገባው የዋለው ገንዘብ 34 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በ2017 ዓ.ም የምገባ ተጠቃሚ አደርጋቸዋለሁ ብሎ በዕቅድ ከያዘው 10 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ ከ733 ተማሪዎች በስተቀር ማሳካት መቻሉን ኃላፊዉ አስታውቀዋል፡፡ ዶክተር ሙሉዓለም አክለውም ምገባ በተጀመረባቸው ት/ቤቶች አርፋጅ ተማሪዎች አለመኖራቸውን፣ ቀሪ መቀነሱን እንዲሁም የትምህርት አቀባበል ላይ ከፍተኛ መሻሻል መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

የተማሪ ምገባን የትምህርት ጥራት እና አግባብነት ማረጋገጫ አድርጎ በትኩረት እየሠራበት መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በባሕር ዳር ከተማ በገመገመበት ወቅት አስታውቋል፡፡ የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ ያደጉ ሀገራት ጭምር የትምህርት ጥራት ዋና ማረጋገጫ አድርገው እየሠሩበት ያለ ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባለፈ የሕጻናትን የአስተዳደግ ሁኔታ በሚቀይር አግባብ ተደራጅቶ እየተሰጠባቸው ያሉ ሀገራት መኖራቸውም በግምገማዊ መድረኩ ወቅት ተመላክቷል፡፡ ነገር ግን በአማራ ክልል ትርፍ አምራች የሚባሉ አካባቢዎች ሳይቀሩ ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠታቸው በክፍተት ተነስቷል፡፡

የትምህርት ቤት ምገባ ተማሪን ከመመገብ እና ካለመመገብ ባለፈ መቀንጨርን በዘላቂነት ከማስወገድ፣ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ፣ የትምህርት ሽፋንን ከማሳደግ ጋር መያያዝ እንደሚኖርበት በአጽንኦት ተነግሯል፡፡ በዚህም ወረዳዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ አንደኛ ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ማድረግን ታሳቢ አድርገው እንዲሠሩ እንደሚጠበቅ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ የምገባ ፕሮግራም በሁሉም አካባቢዎች ወጥነት ባለው አግባብ አለመጀመሩ እና ተግባራዊ አለመደረጉ በራሱ የፍትሐዊነት ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል አስቦ ሁሉም ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥቶ እንዲሠራም ተጠይቋል፡፡

በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን ተማሪዎችን በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የክልሉ ትምህርት ቢሮ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን እስከገመገመበት ጊዜ ድረስ ማሳካት የቻለው በ619 ትምህርት ቤቶች በሚገኙ 281 ሺህ ተማሪዎችን ነው፡፡ አሁንም 719 ሺህ ተማሪዎች ከምገባ ውጪ መሆናቸው ለአፈጻጸሙ ክፍተት ማሳያ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡

የት/ቤት የተማሪ ምገባ ከፍተኛ ገንዘብ እና ጠንካራ አስተዳደርን የሚጠይቅ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም አካባቢያዊ የሆነ የምገባ ሥርዓት የቀጣይ መውጫ መንገድ ሆኖ እንዲሠራበት ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

ኮምቦልቻ፣ ባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደሴና ወልዲያ ከተማዎች፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ጎንደርና ሰሜን ወሎ ዞኖች እንዲሁም ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የትምህርት ቤት ምገባን በተጠናከረ መንገድ እየሰጡ ያሉ አካባቢዎች ሆነው ለሌሎች በተሞክሮነት ተጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ኮምቦልቻ፣ ወልዲያ፣ ደሴ እና ጎንደር ከተማ አስተዳደሮች እስከ መቶ ሚሊዮን ብር ሐብት በማሰባሰብ የምገባ ፕሮግራምን በስፋት እያስኬዱ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ ምዕራብ፣ ሰሜን እና ምሥራቅ ጎጃም  ዞኖች እና አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ትርፍ አምራች ሆነው ተነሳሽነቱን ባለመውሰድ ሲጠቀሱ ለቀጣይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here