በጋዛ ያንዣበበዉ ረሀብ

0
75
Israeli tanks stand near the border between Israel and the Gaza strip, as seen from the Israeli side of the border May 13, 2025 REUTERS/Amir Cohen

በጋዛ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገልጿል። ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም ሰሚ አላገኙም:: በተለይም ለህጻናት እና ነፍሰጡር ሴቶች ያጋጠመው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሁኔታውን በጣም አስደንጋጭ አድርጎታል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከ70 ሺህ የሚበልጡ የፍልስጤም ህጻናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ  ነው:: የእስራኤል ጦር አሁንም እርዳታ ወደ  ጋዛ ሰርጥ እንዳይደርስ እየከለከለ ነው። በየቀኑ ንጹሃን (ሲቪሎች) ዕድለኛ ከሆኑ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ምግብ  ይመገባሉ::ብዙ የረድኤት ድርጅቶች  የእህል ክምችት በመሟጠጡ ምክንያት ማከፋፈል ማቆማቸውን ነው አልጀዚራ የዘገበው፡፡

ዓለም አቀፉ የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (IPC) ከሰሞኑ እንዳስታወቀው የጋዛ ሰርጥ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ አስከፊ ጦርነት ካሳለፈ በኋላ አሁንም ከከፍተኛ የረሃብ አደጋ ጋር እየተጋፈጠ ነው:: ለሰዎች ህልውና በጣም አስፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶች ተሟጠዋል፤ ወይም በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ያልቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለረሃብ ይጋለጣሉ ሲልም አስታውቋል። በግምት 93 በመቶው የጋዛ ሕዝብ ከፍተኛ የምግብ እጥረት እያጋጠመው መሆኑንም አክሏል። በጥቅምት ወር ከወጣው የቀደመው የአይ ፒ ሲ  ሪፖርት ወዲህ ሁኔታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሰዋል።

በጋዛ የእስራኤል ከበባ ከቀጠለ መላው ሕዝብ የከፋ የምግብ ዋስትና እጦት ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል። ከአምስት ሰዎች መካከል አንዱ ከግንቦት እስከ መስከረም ባለው በተለይ ከፍተኛ የእስራኤል ድብደባ ባስተናገዱት ሰሜናዊ ጋዛ እና በደቡባዊው የጋዛ ሰርጥ ክፍሎች (ራፋ)  ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መከሰቱ ተሰምቷል:: የእርዳታ እገዳው ከቀጠለ በመላው ጋዛ ተጨማሪ የጅምላ መፈናቀልን ሊያስከትል እንደሚችልም ነው የተነገረው።

በጋዛ ሰርጥ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ምግብ፣ ውኃ፣ መጠለያ እና መድኃኒት እያገኙ አይደለም። በጋዛ የምግብ ዋጋ ከመጠን በላይ እየጨመረ ነው። የአይ ፒ ሲ (IPC) ዘገባ እንደሚያመለክተው ከየካቲት ወር ጀምሮ  በማዕከላዊ ጋዛ እና በደቡብ ካን ዮኒስ አካባቢዎች የስንዴ ዱቄት ዋጋ ሦስት ሺህ በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

አ.አ.አ  በጥቅምት 7 ቀን 2023 ሃማስ  በደቡብ እስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት የእስራኤል ጦር ቢያንስ 52 ሺህ 862 ፍልስጤማዊያንን ገድሏል።  119 ሺህ 648 ደግሞ ቆስለዋል። በእስራኤል በኩል ደግሞ ከአንድ ሺህ 139 በላይ ሰዎች ሞተዋል፤ ከ200 በላይ ሰዎች ወደ ጋዛ ታግተው ተወስደዋል።

የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያመላክተው ከ200 በላይ ጋዜጠኞች በእስራኤል – ሃማስ ጦርነት ምክንያት ሞተዋል። የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማሕበር ምክትል ዳይሬክተር ፓስካል ሁንዳት እንደሚሉት በጋዛ ያሉ ንጹሃን ሰዎች በተደጋጋሚ ከመፈናቀላቸው እና ዘወትር ለጥቃት ከመጋለጣቸውም ባሻገር ሰብዓዊ እርዳታ በመስተጓጎሉ ችግር ውስጥ ገብተዋል።

ዳይሬክተሩ “በፍጹም ከዚህ በላይ ሁኔታው እንዲባባስ መፍቀድ የለብንም” ይላሉ:: ወደ ጋዛ የሚወስዱ መንገዶች በእስራኤል በመዘጋታቸው ምግብ እና መድኃኒትን ጨምሮ የሰብዓዊ እርዳታ መቋረጡን ነው  የተናገሩት፡፡

እስራኤል የሃማስ ታጣቂ ቡድን ወደ ጋዛ የሚገባውን ምግብ እንደሚቆጣጠር እና እንደሚዘርፍ ብትናገርም ይህንን  የእስራኤል አቤቱታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አልተቀበለውም። እስራኤል የግል ድርጅቶች ምግብ እንዲያከፋፍሉ ባቀረበችው ሃሳብ ላይም  የመንግሥታቱ ድርጅት እንደማይሳተፍ አስታውቋል።

የተመድ የፍልስጤማዊያን ስደተኞች ተቋም ዋና ኮሚሽነር ፊሊፔ ላዛሪኒ የጋዛ ነዋሪዎች እያዩት ያለውን ስቃይ እና እንግልት ለመግለጽ ቃላት እንደሚያጥራቸው እና ከሁለት ወራት በላይ እርዳታ መቋረጡን ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል። በረሃብ የተነሳ ዜጎች መዳከማቸውንና በቀጣይ ሳምንታት እርዳታ ካልገባ ሰዎች በጥቃት ብቻ ሳይሆን በረሃብም እንደሚሞቱ  ነው የጠቆሙት። “ሰብዓዊ እርዳታን የጦር መሣሪያ አድርጎ መጠቀም የሚባለው ይህ ነው” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

አይ ፒ ሲ እንደሚለው 22 በመቶ የሚሆኑት የጋዛ ነዋሪዎች (470 ሺህ ሰዎች) ደረጃ አምስት በሚባለው አስከፊ የረሃብ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። ደረጃ አምስት የከፋ ረሃብ የመጨረሻው መለኪያ ነው። 71 ሺህ ሕጻናት እና 17 ሺህ እናቶች የምግብ እጥረት ሕክምና ያስፈልጋቸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እና የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለጹት እገዳው ከመጋቢት 02 ቀን ጀምሮ 57 ህጻናትን በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ሕይወታቸውን እንዲያጡ አድርጓል።

“ይህን የሚፈርጀው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቢሆንም” ይላሉ ኮሚሽነር ፊሊፔ ላዛሪኒ  “ማየት ከምንችለው ተነስተን ምግብና ሰብዓዊ እርዳታ መከልከልን እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም እስራኤል በጋዛ ያላትን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ግብ ለማሳካት እየሞከረች ነው” ብለዋል።

አንድ ሺህ 200 የእስራኤል ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪዎች በጻፉት ደብዳቤ የጦርነቱ መራዘም “ከደኅንነት ጉዳይ ይልቅ ከፖለቲካና ከግል ፍላጎት ጋር የተገናኘ ነው” ማለታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውቋል።

ሁለተኛው ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት የሚተገበርበት ዕድል በጦርነቱ ዳግመኛ መጀመር ምክንያት መክሸፉ ይታወቃል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ከወጣች ሃማስ የተቀሩትን ታጋቾች በአጠቃላይ እንደሚለቅ አስታውቋል። ይሁንና የእስራኤል ባለሥልጣናት በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማዊያን በአይሁዳዊያን ሰፋሪዎች እንዲተኩ ስለሚፈልጉ ጦርነቱን ማቆም እንደማይሹ ነው የተገለጸው።

አክራሪ ብሔርተኞችና የእስራኤል ፖለቲከኞች ኔታንያሁ ጦርነቱን እንዲያቆሙ አይፈልጉም::ጦርነቱን ካቆሙ የፖለቲካ ሕይወታቸው ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ነው የተገለጸው።

እስራኤል የቻለችውን ያህል ፍልስጤማዊያንን ከጋዛ   አስወጥታ ወደ ደቡባዊ ራፋህ አቅራቢያ እንዲሰደዱ  ትፈልጋለች። ይሁንና ራፋህን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መውደሟ ነው የሚነገረው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው 90 በመቶ ያህል ጋዛ ለፍልስጤማዊያን መኖሪያ መሆን በማይችልበት  ደረጃ ላይ ይገኛል።

ኔታንያሁ ከሰሞኑ በውጊያ ላይ እያሉ የቆሰሉ የእስራኤል ወታደሮችን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት ፍልስጤማዊያን ከጋዛ እንዲወጡ የሚያስችል አስተዳደር ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፤ ይሁን እንጂ ተቀባይ ሀገሮች እንደሚያስፈልጉ አስታውቀዋል። እስራኤል እና አሜሪካ ከግዛቱ ሊወጡ የሚችሉ ፍልስጤማዊያንን ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆኑ ሀገሮችን እየፈለጉ ነው። ታዲያ ይህ ጉዳይ የአረብ ሀገራትን አስቆጥቷል፡፡

በተመሳሳይ እስራኤል ጋዛን በመቆጣጠር ጥቃቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ከሰሞኑ አስታውቃለች::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ አሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና   የትራምፕ አስተዳደር የታገቱ ጉዳዮች መልዕክተኛ አዳም ቦህለር በቴል አቪቭ ከታጋች ቤተሰቦች ጋር ለሁለት ሰዓታት የሚጠጋ ውይይት ማድረጋቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል:: በውይይታቸውም  ቀሪዎቹን ታጋቾች ወደ ሀገር ቤት ለማምጣት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት፡፡

ከሰሞኑም የ21 ዓመቱ አሌክሳንደር ከእገታ  የተለቀቀው በሃማስ እና በትራምፕ አስተዳደር መካከል በተደረገ ድርድር ነው። እስራኤል  በዚህ  ድርድር  የተገለለች ሁናለች። የ19 ዓመቱ አሌክሳንደር በ2023 ጥቃት ከእስራኤል ጦር ሰፈር ነበር  የተወሰደው። በመጋቢት ወር እስራኤል – ከሃማስ ያደረጉት ለስምንት ሳምንታት የፈጀው  የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈረሰ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን ሕይዎታቸው አልፏል፤ አሌክሳንደር እስራኤል በጋዛ ላይ ከባድ ጥቃት ካደረሰች በኋላ ከእስር የተለቀቀው የመጀመሪያው ታጋችም ነው። የታጋቹን መለቀቅን አስመልክቶ ትራምፕ “ኳታር እና ግብፅ  ይህን እጅግ አረመኔያዊ ጦርነት ለማስቆም እና ሁሉንም በሕይወት ያሉ ታጋቾችን በማስለቀቅ ለዘመዶቻቸው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ነው” ብለዋል:: “ይህም በአሜሪካ በቅን ልቦና የተወሰደ እርምጃ”  ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

የአሜሪካ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ   ሁሉም ሰው ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄን  እንደሚመርጥ  ጠቁመው  አብዛኞቹ ታጋቾች የተለቀቁትም ከጦርነት ይልቅ በዲፕሎማሲ መሆኑን ነው የተናገሩት። ባለሥልጣናቱ ከስብሰባ በኋላ  ከፕሬዚዳንት ዶናልድ  ትራምፕ ጋር በመሆን  ወደ ዶሃ ኳታር በማቅናት  ቀጣናውን እየጎበኙ ነው። ኳታር በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ቁልፍ አስታራቂ ሆና ቆይታለች። ዊትኮፍ በድርድር ላይ እውነተኛ የዕድገት ዕድል አለ ብለው ካላሰቡ ወደ ኳታር እንደማይጓዙ ተናግረው ነበር።

በሌላ በኩል በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላዊያን በማዕከላዊ ቴል አቪቭ ሰልፍ አድርገዋል:: በሰልፉም መንግሥታቸው በጋዛ ላይ የሚደረገውን ጦርነት እንዲያቆም እና በፍልስጤም ግዛት ውስጥ የሚገኙ እስራኤላዊያን  ምርኮኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ነው የጠየቁት።

አልጀዚራ   እንደዘገበው በቴል አቪቭ የታገቱት እና የጠፉ ቤተሰቦች ፎረም የእስራኤል የዘመቻ ቡድን ሳምንታዊ የተቃዉሞ ሰልፉን  በ”ሆስታጅስ አደባባይ” አካሂዷል፡፡

የእስራኤሉ ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው ደግሞ በቴል አቪቭ ሀቢማ አደባባይ የተለየ የመንግሥት ተቃውሞ ተካሄዷል። ወላጆቹ በምርኮ የተያዙ እና በተለያየ የልውውጥ ስምምነት የተፈቱላቸው ሻይ ሞዝዝ የሚባል ግለሰብ በሀቢማ አደባባይ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ለተሰበሰበው ሕዝብ  “የእስራኤል እውነተኛ ጠላት ሃማስ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ነው፤  ኔታንያሁ የእስራኤልን  ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እያፈረሰ ነው” ብለዋል። አልጀዚራ እንደዘገበው በጋዛ የሚገኙ የእስራኤል ታጋች ቤተሰብ አባላት ኔታንያሁ ጦርነቱን የሚያራዝሙት ለግል እና ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲሉ እንደሆነ እና የትኛውንም አይነት የተኩስ አቁም ስምምነትን በተመለከተ ለመደራደር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነው የተናገሩት::

 

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here