ግጭቱ እንዲያበቃ…

0
69

ያለፉት ሁለት ዓመታት ለአማራ ክልል ሕዝብ  ፈታኝ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳ አሁን ላይ በአንጻራዊ የሰላም ሁኔታ ውስጥ ቢገኝም ካለፈው ዓመት ጀምሮ አሁንም ድረስ የቀጠለው የሰላም እጦት  የክልሉን ሕዝብ ከማኅበራዊ ግንኙነት እና እንቅስቃሴ አግልሎት ቆይቷል፤ ተጀምረው የነበሩ የልማት ሥራዎች በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ ሆነዋል። በምርት አቅርቦት ላይ ጫና በማሳደር የዋጋ ውድነት እንዲከሰት፣ የዜጎችም ፈተና እንዲሆን አድርጓል፡፡ ግጭቱ በተከሰተበት ቀጣና የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ዳፋውን አስረድተዋል፡፡

የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ነዋሪዋ ወይዘሮ አሚናት የሱፍ ክልሉ የገጠመው የሰላም መደፍረስ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ውስጣዊ ግጭቱ ነዋሪዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉም አድርጓል ባይ ናቸው፡፡ ይህም አምራች እጆች ለጠባቂነት እንዲዘረጉ ያደርጋል፡፡

እንደፈለጉ መንቀሳቀስ የማይችሉ አካል ጉዳተኞች፣ አቅሞ ደካሞች፣ ሴቶች እና ሕጻናት በግጭቶች ክፉኛ ተጎጂ እንደሚሆኑ ባለፉት ዓመታት በተስተዋሉ ጦርነቶች መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡ በወንድማማቾች መካከል እየተደረገ ባለው አሁናዊ ግጭትም ዜጎችን ለሞት እና ለአካል ጉዳት፤ ለንብረት  ውድመትም እየዳረገ መሆኑን አክለዋል፡፡

ውስጣዊ ግጭት የማታ ማታ መቋጫው ድርድር ቢሆንም ጠባሳውን ለመሻር የሚወስደው ጊዜ በቀላሉ የሚገለጽ አይሆንም፡፡ የአካል ጉዳት የደረሰበት በራሱ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ባለመቻሉ ምክንያት የመጨረሻ መተዳደሪያው  ልመና ይሆናል፡፡ ይህም ከሚፈጥረው ስነ ልቦናዊ ጫና ባለፈ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል፤ የማኅበረሰብ ዕድገትን ይገታል፤ በማኅበረሰብ መካከል የሚኖር ዕድገት ሰፍቶ የፍትሐዊነት ጥያቄ እንዲነሳ በማድረግ ለዳግም ግጭት የመዳረግ ዕድሉም ሰፊ ነው፡፡

ታዲያ ወይዘሮ አሚናት ግጭቶች ሥር ሳይሰዱ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ፡፡ ለዚህም የግጭትን ወይም የጦርነትን የነገ ተጽዕኖ በአግባቡ መረዳት፣ በጦርነት ያለፉ ሐገራትን የዛሬ ቁመና መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ወይዘሮ አሚናት ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ሰላማዊ አማራጭን መከተል፣ የችግር ምንጭ የሆኑ ችግሮችን በሀገራዊ ምክክር ለይቶ መፍትሄ እንዲሰጥባቸው ማድረግ፣ ሕዝቡም ልጆቹን መክሮ መመለስ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ እና ጠራ ወረዳ ነዋሪው አቶ ደረጀ ቦጋለ በበኩላቸው የአማራ ሕዝብ የሚገባው ከማኅበራዊ ግንኙነት የሚያስወጣው ተደጋጋሚ ግጭት ሳይሆን ልማት እና መልካም አስተዳደር ነበር ሲሉ የግጭቱን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል፣ ሕዝቧም በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ ወደፈለገው አካባቢ በፈለገው ጊዜ ግንኙነቱን እንዲያደርግ፣ በነጻነት ሠርቶ ሕይወቱን እንዲመራ የሚያደርጉ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ መትጋት የዚህ ትውልድ ቀዳሚ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ  አሳስበዋል፡፡

የጸጥታ ችግሩ ማብቂያ አግኝቶ ክልሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ “የጥፋት እጆች እና መዘዞቹ” በሚል መሪ መልዕክት  ውይይቶች እየተደረጉ ነው፡፡ የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሠራተኞችም በክልሉ የሰላም ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡ በዚህ ወቅት የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ክልሉ በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰበት ጉዳት ሳያገግም በገጠመው የውስጥ የጸጥታ ችግር ምክንያት ለዘርፈ ብዙ ቀውስ መዳረጉን አንስተዋል፡፡ በትምህርት አሰጣጡ እና በተቋማቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት አብነት አድርገዋል፡፡

ግጭቱ ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳያስከትል ምሁራን የተሸረሸሩ የአማራ ሕዝብ እሴቶች እንዲመለሱ፣ የቀደመው መደማመጥ እና ተነጋግሮ መግባባት እንዲኖር እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ለሰላም እጁን እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡

ሕዝቡ የተሻለ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኝ፣ ከድህነት እንዲላቀቅ፣ አስተማማኝ ሰላም በዘላቂነት ሰፍኖ ደኅንነቱ እንዲጠበቅ፣ አንድነቱ የተጠናከረ እንዲሆን ማንቃት እና ማስተማር እንደሚገባ አሳስበዋል። ለዚህም መሪዎች አርዓያ እንዲሆኑ ተጠይቋል። “ኢትዮጵያን ወደተሻለ ልማት እና እድገት እናሻግራለን ብላችሁ እየደከማችሁ ያላችሁ ወገኖቻችን እባካችሁ መለስ ብላችሁ እናታችሁ የተንገላታችበትን እዩና በቃ በሉ!፤ ሁሉን የሚያግባባ ነገር ፈልጉና ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ፍቱ፤ በዚህ አማራጭ እናት ሀገር እፎይታ እንድታገኝ አድርጉ፤ ይህንም ለውድ እናት የሚደረግ ካሣ አድርጋችሁ ውሰዱ” ሲሉ ቅዱስነታቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ከአሚኮ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ የክልሉ የጸጥታ ችግር መፈጠር እና መባባስ ሥረ ምክንያቱ “የተለየ አጀንዳን አንግበው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የተንቀሳቀሱ ኃይሎች መኖራቸው እና በወቅቱ ሁሉም የመንግሥት አካላት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተገቢው መንገድ አለመወጣታቸው ነው” ብለዋል፡፡ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ በወቅቱ መመለስ ባለመቻሉ አሁን ላለው ችግር ገዢ ምክንያት አድርገው አንስተዋል፡፡ ይህም የተለየ ዓላማ ይዞ ሲንቀሳቀስ ለነበረው ኃይል ጉልበት እንደሆነው አንስተዋል፡፡ በወቅቱ የምክር ቤት አባላት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ ጉድለት ነበረባቸው፣ ይህም ለችግሩ መባባስ የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡

ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ተመልሰው የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥል፣ ትውልድ በሚቀርጹ መምህራን ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲቆም እንዲሁም ሰላም እና ደኅንነት ተረጋግጦ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ሰላም ላይ መሥራት ለነገ የማይባል ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ወደ አንድ አካባቢ የሚንቀሳቀስ መምህር ዋስትናው የሚሄድበት አካባቢ ሕዝብ ነው ያሉት ወይዘሮ ፋንቱ፣ በመሆኑም ሕዝቡ የሰላም ደጀንነቱን በተግባር እንዲያሳይ ጠይቀዋል፡፡

ጦርነት ትርፉ ሕዝብን ማጎሳቆል በመሆኑ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ወይዘሮ ፋንቱ ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም ሕዝቡ ከመንግሥት፣ መንግሥትም ከሕዝብ ምን እንደሚጠብቅ ማሳወቅ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህ ረገድ በተዋረድ የሚገኙ የምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር በመገናኘት ማወያየት እና ማነጋገር እንደሚጠበቅባቸው  ተናግረዋል፡፡ የክልሉን ሕዝብ ከተራዘመ ግጭት በማውጣት የሰላም እና ልማት ፍላጎቱ ዕውን እንዲሆን የምክር ቤት አባላት ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆነው እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ የክልሉ ሕዝብ ከገጠመው የሰላም እጦት እንዲወጣ ተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ የሕዝቡ ፍላጎትም አሁን እየደረሰበት ካለው ግድያ፣ ዝርፊያ እና እንግልት መውጣት፤ ሰላም፣ ልማት እና ደኅንነቱ እንዲጠበቅለት ብቻ ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ክልልን ሰላም በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማጽናት ሕዝቡን በማወያየት የሰላም ዘብ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የሰላም አማራጭን መርጠው ከጥፋት መንገድ የሚመለሱ ኃይሎችን የተሐድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲመለሱ እየተደረገ ነው፡፡

የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን በአማራ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር  አካሂዷል፡፡ በዚህ ወቅት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በክልሉ ከጥር ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሰላማዊ መንገድን መርጠው ከጥፋት መንገድ የተመለሱ ታጣቂዎችን ወደ ሥልጠና ማዕከላት በማስገባት ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ አሁንም የሰላም አማራጭን ለሚቀበሉ ታጣቂዎች የሚሰጠው የተሐድሶ ሥልጠና እና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ጥረት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ ሕዝቡም ታጣቂዎች ከጥፋት መንገድ እንዲመለሱ፣ የተመለሱትም የልማት አካል እንዲሆኑ እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ  በክልሉ እና በመላ  ሀገሪቱ  ሰላም እና ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት። በግጭት ወቅት  በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች   ብቻ ሳይሆን በንብረት እና በሰው ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን በመረዳት የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ሲሠራ መቆየቱንም ጠቁመዋል። ወደ ሰላም የገቡ ታጣቂ ኃይሎችን ደግሞ ከብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ጋር በመተባበር  የተሐድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ተሟላ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አሁንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች  ጋር  የሰላም ስምምነት ላይ  መደረሱን ርእሰ መስተዳደሩ ጠቁመዋል፡፡ የታጠቁ ኃይሎችን  በቀጣይ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ተመልሰው የልማት አቅም እንዲሆኑ ኮሚሽኑ ለሚያደርገው ጥረት የክልሉ መንግሥት ድጋፉ እንደማይለይ አረጋግጠዋል፡፡ የታጠቁ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ ኑሮ ተመልሰው የልማት አቅም እንዲሆኑ ሕዝቡ እና አጋር አካላት ትብብር  እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ባለፉት ዘመናት በዓለም ላይ ለዓመታት በማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የነበሩ ሀገራት የጦርነት ውጤቱ የሰው ሕይወት ጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ የማኅበራዊ ግንኙነት መሻከር፣ የደኅንነት ስጋት፣ የንብረት ውድመት፣ … መሆኑን በመገንዘባቸው ለሰላም ሳይታክቱ ሠርተዋል፡፡

የሰላም መንገዳቸውንም እርስ በርስ ቀርቦ ችግሮችን ለይቶ ሁሉን የሚያስማማ መፍትሄ አስቀምጠዋል። አፍሪካዊቷ ደቡብ አፍሪካ ለዚህ በአብነት ትነሳለች፡፡ የአፓርታይድ ሥርዓትን በሰላማዊ መንገድ በማስወገድ ከዘር መድልዎ ነፃ የሆነች ሀገርን ለመፍጠር ንግግርን ብቸኛ አማራጭ አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ የሐሳብ ፍጭት የነበረ በመሆኑ አለመግባባቶች ቢስተዋሉም ውጤቱ ግን ችግሮች ሥር ነቀል በሆነ መንገድ እንዲፈቱ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያም ያሉ ችግሮቿን ለይታ ሥር ነቀል በሆነ መንገድ መፍትሄ ለመስጠት በየጊዜው ከምታስተጋባው የሰላም ጥሪ ባሻገር ሀገራዊ ምክክርን ዋና መውጫዋ አድርጋ እየተጋች ትገኛለች፡፡ ዜጎቿም እንደ ደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ኮሎምቢያ ዜጎች ሁሉ ለችግሮች እልባት ማግኘት  ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ለሰላም የሚደረግ ጥረትን በአዎንታ መመልከት ይገባዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here