ዲጂታል መታወቂያ የእርስ በርስ መተማመንን ይፈጥራል

0
60

በአማራ ክልል የዲጂታል መታወቂያ አተገባበር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተካሂዷል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሰተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ሚና እንዲኖራት አስተዋጽኦው የጎላ ነውም ብለዋል።

በአማራ ክልል አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማከናዎናቸውንም ተናግረዋል። ሥራው በተፈለገው ልክ እንዲሄድ ተቋማት ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው ነው ያስገነዘቡት።

ዲጂታል መታወቂያ እርስ በእርስ መተማመንን ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል። ያደጉ ሀገራት የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ እና እንደ ክልል በሀገራዊ የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የራስን አስተዋጽኦ ለማድረግ አስፈላጊ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በዲጂታል መታወቂያ ላይ የተዛቡ ግንዛቤዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊው ይህንንም ለመፍታት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ዲጂታል መታወቂያ ዘር ብዙ ጥቅም እንዳለው በመገንዘብ የክልሉ ነዋሪዎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ ለአንድ ሀገር ትልቁ ሃብት ሰው ነው፤ ሰውን በአግባቡ አገልግሎት ላይ ለማዋል ደግሞ በብሔራዊ ደረጃ ወጥ በሆነ መንገድ መለየት ይገባል ነው ያሉት።

በብሔራዊ ደረጃ ሰውን ወጥ በሆነ መልኩ መለየት ሰዎች መብታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲጠቀሙ ያስችላል ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን ቀላል ለማድረግ እና የዲጂታል ኢኮኖሚን ከፍ ለማድረግ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የዲጂታል መታወቂያ ዓላማው ዲጂታል ዱካ እንዲኖር ማድረግ ነው ያሉት አስተባባሪው የመረጃ ትስስር እንዲኖር እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

እርስ በእርስ መተማመን እንዲፈጠር እንደሚያደርግም በማንሳት ዜጎች ዲጂታል ኢትዮጵያን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል። የዲጂታል መታወቂያ እንደ ሀገር አንድ  የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

(ታርቆ ክንዴ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here