የ35 ዓመቷ አስካል አድማሱ ትውልድ እና እድገቷ በባሕር ዳር ከተማ በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በፈለገ ዓባይ አንደኛ ደረጃ እና በዕውቀት ፋና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትላለች:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በጣና ኃይቅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር የተማረችው:: 10ኛ ክፍል እንደጨረሰች ለአንድ ዓመት በባሕር ዳር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በኬክና በዳቦ ጋገራ ሰልጥናለች::
ለቤተሰቦቿ አራተኛ ልጅ የሆነችው አስካል ከሕጻንነቷ ጀምሮ እኩዮቿ ልባቸው ወደ ጨዋታ ሲያደላ እሷ ደግሞ እናቷን ሥራ ለማገዝ እና ሙያ ወደ መቅሰም ታጋድል ነበር:: ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ከእናቷ የባልትና ሙያ እየቀሰመች ነው ያደገችው::
የባልትና ሙያን ከእናቷ እና ከማሰልጠኛ ተቋም የቀሰመችው አስካል ከቤተሰብ ወጥታ ራሷን ለመቻል የገቢ ምንጭ ማግኛ መንገዶችን ማማተር ጀመረች:: በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች የእናትነትን ፀጋ ተጎናፀፈች:: ይህም ሁኔታ ራሷን ለመቻል ያሰበችውን አስካል ከመንገድ አላስወጧትም፤ የሚያበረታቷት ምክንያቶች ተበራከቱ እንጂ::
የአስካልን ሀሳብ ቤተሰቦቿም ደግፈው ለሥራ መነሻ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉላት:: የጸጉር ቤት በመክፈት ሥራን “አሃዱ“ አለች:: 17 ዓመታትም በጀመረችው ሥራ ፀንታ ቤተሰቦቿን ማስተዳደር ቻለች::
በአሁኑ ጊዜ የጸጉር ቤቷን ብትዘጋውም በየቤቱ እየተንቀሳቀሰች ሹርባን ትሠራለች:: “ሕይዎት አልጋ በአልጋ አይደለችም፤ ጥረው ግረው የሚኖሩባት የልፋትን ዋጋ የምትጠይቅ ናት” የምትለው አስካል፤ የልጇ አባት ሌላ ቦታ በመሆኑ ብቻዋን ለማሳደግ ተገዳለች::
አስካል በአንድ ወቅት የምታውቃቸው ሰዎች ፕሮግራም ኖሯቸው ጠላ ለማድረግ እንደተቸገሩ ሲጨነቁ ሰማች:: ከእናቷ ጎን ሳትለይ ሙያ ትቀስም ለነበረችው አስካል የሰዎች ጭንቀት እርሷን እንድታስብ አደረጋት፤ “ለምን እኔ አልሠራላችሁም፤ ጠላ መጥመቅ እችላለሁ!” በማለት ወደ ሙያው እንድትገባ አነሳሳት::
በወቅቱም ባለድግሶቹን ጠላውን በመጥመቅ ከጭንቀት ገላገለቻቸው፤ የእርሷን መክሊትም አገኘች:: አስካል በጊዜ ሂደት ጠላ መጥመቅ ላልቻሉ ሰዎች ምጥኑን በማዘጋጀት እና በመደፍደፍ መሸጥ ጀመረች::
በዚህ ሳትገደብ በየቤቱ እየተዘዋወረች ጠላ ጠማቂ ለሚፈልጉ ሰዎች በቤታቸው በመሄድ መጥና እስከመጨረሻው ታዘጋጃለች:: በተጨማሪም ከሌላ ቦታም ይሁን በራሳቸው የተዘጋጀ የጠላ ምጥን ደፍድፋ መስጠት ጀመረች::
አስካል እንደምትለው ብዙ ጊዜ በእርግጠኛነት ጠላዋ በሰዎች ዘንድ ተመራጭ ነው:: ይህን ሙያዋን ይዛ ለመቀጠል ግን ከምጥን ማዘጋጀት፣ እቃ ከማጠብ ጀምሮ ያሉት ሂደቶች ሙሉ በሙሉ በእርሷ ቢያልቁ ትመርጣለች:: ምክንያቱም እንደየ ሰው ሙያውም ሊለያይ ስለሚችል ሌላ ሰዉ ያዘጋጀውን ምጥን ማዘጋጀት “እጀ ሰባራ ሊያደርግ ይችላል“ ትላለች::
አስካል ጠላ መጥመቅ በራሱ ትዕግስትን የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን ትገልጻለች። ታዲያ ለሌላ ሰው ማዘጋጀት ደግሞ ተጨማሪ መታገስንና ማሳመንን እንደሚጠይቅ ነው የተናገረችው። አንዳንዴ ከደንበኞቿ ጋር አለመግባባት እንደሚፈጠር የጠቀሰችው አስካል ሆኖም በመነጋገር መስተካከል ያለባቸው ነገሮችን እንደምታስተካክል ነው ያስረዳችን::
እስካሁን የጠላ እህሉን በመመጠን እስከ መበጥበጥ (ማሰር) ድረስ ያለውን ሂደት ከሠራችላቸው ሰዎች ጋር ቅሬታ ቀርቦባት እንደማያውቅ ነው የተናገረችው:: “ጠላ የሚጠነሰስበት እቃ በደንብ በግራዋ ታጥቦ በወይራ ከታጠነ ጠላ አይበላሽም እንዲሁም ምጠኑን በሥርዓት መመጠን ይገባል” ትላለች::
ከሴቶች የውበት ሳሎን ወደ ጠላ ምጥን ማዘጋጀት፣ አለፍ ሲልም እስከመጨረሻው ጠላ ወደ መጥመቅ የተሸጋገረችው አስካል በአሁኑ ጊዜ ደምበኞቿ ተበራክተዋል:: በተለይም ለበዓላት፣ ለክርስትና፣ ለልደት፣ ለተዝካር እና ለሰርግ ፕሮግራም የጠላ ምጥን ለሚፈልጉ ሰዎች ከምጥኑ ዱቄት ጀምሮ ድፍድፍ በማዘጋጀት በክልሉ ከተለያዩ አካባቢዎች አልፋ አዲስ አበባ ድረስ አገልግሎት መስጠት ጀምራለች:: አሁን ላይ ብዛት ያለው ጠላ ስትጠየቅ ከራሷ አልፋ ሌሎች ሥራ አጥ ወገኖችን በአጋዥነት በመቅጠር ተጠቃሚ ማድረግ ችላለች::
“ ‘የመንግሥት ሥራ ካልተቀጠርሁ’ በሚል ከቤታቸው ለተቀመጡ ሰዎች የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ፤ የወር ደመወዝተኛ ለመሆን ከሚታገሉ የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ከጠባቂነት ቢወጡ መልካም ነው:: እኔ አሁን ላይ ሦስት ልጆቼን ያለማንም አጋዥ ነው የማሳድገው:: የሰው እጅ አላይም፤ ወር ጠብቄ አልኖርም፤ በቀጣይ ሥራዬን በማስፋት ከኔ አልፌ ለሌሎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ በሥራም ሆነ በሌላ ምክንያት ባሕላዊ የሆነውን ጠላ ማዘጋጀት እየፈለጉ ለሚቸገሩ እንዲሁም ከልምድ ማነስ ጠላ ሲያዘጋጁ ከመጠን በላይ አትረፍርፈው በማዘጋጀት ሐብታቸውን እና ጉልበታቸውን በከንቱ የሚያባክኑ ደንበኞቼን ለማርካት ካሁን በበለጠ መዳረሻየን በማስፋት የበለጠ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ“ በማለት የወደፊት ዕቅዷን ነግራናለች::
ከደምበኞቿ መካከል የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ በሰጡን አስተያየት “ለድግስ ጠላ እንድታዘጋጅልን የምንጠራውን ሰው መጠን ነገርናት:: ይህን መሰረት አድርጋም እኛ ያዘጋጀነውን የጠላ እህል መጥና ከጥንስሱ እስከ መጨረሻው ጠላ ድረስ አዘጋጀችልን:: በዚህም ያዘጋጀችው ጠላ ያልተትረፈረፈ ነበር:: ይህም የመንግሥት ሠራተኛ በመሆኔ ጊዜዬን፣ንብረቴን ከብክነት፣ ጉልበቴን… ታድጋልኛለች!“ በማለት አስካል ከራሷ ባላነሰ እንደ እርሳቸው ያሉትን ጊዜ…እንደታደገችላቸው መስክረዋል::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም