ቻይናዊቷ ባለተሰጥኦ ቪክቶሪያ ሊ ገፅታዎችን በተለያዩ ቀለማት ጥቃቅን መስመርን በመስራት ጥራት ባለው ካሜራ የተነሳ ምስል አስመስላ መስራት የቻለች የንቅሳት ጠቢብ መሆኗን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት አስነብቧል፡፡
ድረ ገጹ እንዳስነበበው የንቅሳት ጠቢቧ ባለፉት 17 ዓመታት በኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ በስራቸው እውቅና አግኝተው ለንባብ ከበቁት መካከል መካተት የቻለች ወጣት ናት፡፡
ወጣቷ ከአራት ዓመት እድሜዋ ጀምሮ ንቅሳት መስራቷን ያስነበበው ድረ ገጹ አሁን ላይ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የንቅሳት ጠቢባን ዝርዝር ውስጥ ተካታለች፡፡
ወጣቷ የንቅሳት ጠቢብ በፎቶ ግራፍ የተነሳን ምስል በንቅሳት ከካሜራ በላይ ማጉላት መቻሏን በስራዎቿ ማረጋገጥ ችላለች፡፡
የንቅሳት ጥበብ አጀማመሯን አስመልክታ ቪክቶሪያ ሊ ከስነጥበብ ትምህርት ቤት እንደተመረቀች የአያቷን ምስል በንቅሳት ማሰራት ፈልጋ ባለሙያ ታማክራለች፤ የሰራላት ግን አላረካትም፤ እናም ራሷ ለመሞከር ወስና ቀጠለች እና ወደደችው ወደ ጥበቡ ሙሉ በሙሉ መግባትም ቻለች፡፡
ለንቅሳት ጥበብ መነሻ የሚሆናት የደንበኞቿ ፍላጐት መሆኑን የተናገረችው ጠቢቧ አንድ ስራን ሰርታ ለማጠናቀቅ በርካታ ሰዓታት እንደሚወስድባትም ነው ያብራራችው፡፡
ጠቢቧ አሁን ላይ በቻይና ቤጂንግ ቻዮንግ ግዛት ቋሚ የስራ ቦታ (ስቱዲዮ) ከፍታለች፡፡
ቪክቶሪያ ዩክሬናዊውን የንቅሳት ጠቢብ ዲሚትሪ ሳሞሂን አድናቂ እና አርዓያ ያደረገችው መሆኗን ነው በማጠቃለያነት ያሰመረችበት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም