ያዩ የጫካ ቡና መጠበቂያ

0
72

ከዋና ከተማዋ አዲስ አባ በስተደቡብ ምእራብ 640 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ኢሊባቦር ዞን ነው የሚገኘው፡፡ በዓለማችን አንደኛ ደረጃ ተመራጩ የቡና ዝርያ “ኮፊ አረቢካ” መገኛ ማእከልም ነው ያዩ የሜካ ቡና መጠበቂያ፡፡

ያዩ የጫካ ቡና መጠበቂያ ተራራማ ቀጣና  ይበዛዋል፡፡ አጠቃላይ ስፋቱ በስድስት ወረዳዎች 167 021 ሄክታር ተለክቷል፡፡ የ “ኮፊ አረቢካ” የቡና ዝርያ መገኛው የያዩ ጫካ በ2002 ዓ.ም ማለትም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት “UNESCO’’ እውቅና አግኝቷል፡፡

የያዩ የጫካ ቡና መጠበቂያ በሦስት ቀጣና የተከፈለ ነው፤ ዋና  የመጀመሪያው  ቀጣና 27 733 ሄክታር  ሁለተኛው  ቀጣና 21552 ሄክታር የመጨረሻው የሽግግር ቀጣና 117,736 ሄክታር ነው፡፡

በተለይም የሦስተኛው የሽግግር ቀጣና ቡና እና ሌሎች ሰብሎችን በአጐራባች የሚገኙ አርሶ አደሮች እንዲያመርቱ የተፈቀደበት ክልል ነው፡፡

በቀጣናው የተቋቋመው (manand Biospher) የተሰኘው አጋር አካላትን ያቀፈ ኘሮግራም የአካባቢው አርሶ አደሮች የቡና ተክሎቻቸውን እያደሱ (የቡና ተክሉን እየገረዙ) ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ትምህርት ይሰጣል፡፡

በያዩ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች የቡና ተክሎችን ያረጁ ቅርንጫፎችን በመመልመል አዲስ አውጥተው ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ከአጋር አካላት ተውጣጥቶ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ጠንክሮ እየሰራ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡

በቀጣናው ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች አዳዲስ ጉድጓዶችን ቆፍረው የቡና ችግኝ እንዲተክሉም ተደርጓል፡፡ ተከላው በየመስመር መካከል  ሁለት ሜትር በእያንዳንዱ የቡና ተክል መካከል ደግሞ አንድ ነጥብ አምስት ሜትር ክፍተት መተውን ግድ እንደሚል ሳይንሳዊ ምክር ለግሰዋል፡፡

የያዩ የጫካ ቡና መጠበቂያ ጫካ  በዋናነት “የኮፊ አረቢካ” አንደኛ ደረጃ ተመራጭ ቡና ዝርያ መገኛ ከመሆኑ ባሻገር የ450 እፅዋት፣ 50 አጥቢ እንስሳት እና 20 በየብስ እና በውኃ ውስጥ የሚኖሩ ዝርያዎች መገኛ መሆኑ ነው የተሰመረበት፡፡

በአጠቃላይ 100 እፀዋት፣ አእዋፍ እና አጥቢ እንስሳትን ያቀፈ ቀጣና ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ  ከአጠቃላይ 44 ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ያንዣበበባቸው ሆነው መመዝገባቸውን ነው ድረ ገፆች ያስነበቡት፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ያዩ ባዬስ ፌር፣ ኢንተርናሽናል ክላይሜት ኢንሼቲቭ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here