የጓርዲዮላ ደቀመዛሙርት

0
71

ብዙዎቹ  በእግር ኳስ ቆርቧል ይሉታል፤  እግር ኳስን እንደነብሱ ይወዳል፤ በእግር ኳስ ምክንያት የ30 ዓመት  ትዳሩ ተናግቷል፤ ስለስፖርት ስነ ልቦና እና ፍልስፍና ያለእረፍት ያነባል፤ ይመራመራል፤ ለመማር ዝግጁ ነው፤ የማይነጥፍ የፈጠራ እና የታክቲክ እወቀት አለው፤የካታሎናውያን ኩራት ነው፤ የእግር ኳስ አርትስም ነው። የቅርጫት ኳስ እና የጎልፍ ስፖርት አፍቃሪ፤ በእግር ኳስ ደግሞ ሊቅ ነው።  የዓለም እግር ኳስ ማርሽ ቀያሪው አሰልጣኝ- ጆሴፕ ፔፕ ጓርዲዮላ።

ስፔናዊው ታክቲሺያን የ21ኛው ክፍለ ዘመን አቢዮተኛ አሰልጣኝ ነው። በሚከተለው ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት (ፖዚሽናል ፕሌይ) በባርሴሎና፣ ባየርሙኒክ እና ማንቸስተር ሲቲ አስደናቂ ስኬትን አስመዝግቧል። ጓርዲዮላ የ21ኛው ክፍለ ዘመን እግር ኳስን መቀየሩን ብዙዎች ይመሰክሩለታል። በእግር ኳስ ስፖርት የመነኮሰው ጓርዲዮላ ሁሌም ሀሳቡ እግር ኳስ እና እግር ኳስ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ 30 ዓመታትን ከደፈነው የትዳሩ ጋር አለያይቶታል።

ከአርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ማርሴሎ ቤልሳ  በተጫማሪ የአንጋፋው የቅርጫት ኳስ አሰልጣኝ ጆን ውድ ተጽእኖ እንዳለበት የጎል ዶት ኮም መረጃ ያመለክታል። ይህ ደግሞ በጨዋታ አቀራረብ እና ፈጠራ እንዲካን አግዙታል ይላል መረጃው። ጓርዲዮላ ከጨዋታ በኋላ የእግር ኳስ ትንተና ሲሠራ እና ሲያነብ ብዙ ጊዜውን እንደሚያሳልፍ መረጃው አመልክቷል። በጓርዲዮላ መነጽር የትኛውም ጥቃቅን የእግር ኳስ ክስተት እና ሀሳብ ዋጋ አልባ አይደለም። ነገሮቹን በጥልቀት መመርመሩ  አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ አግዞታል።

ጓርዲዮላ በተጫዋችነት ዘመኑ ድንቅ የመሀል ሜዳ ኦርኬስትረኛ እንደነበር የእግር ኳስ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህ ብቻ ግን ድንቅ አሰልጣኝ አላደረገውም። እ.አ.አ በ2006 በተጫዋችነት የእድሜ ማምሻው ወደ ሜክሲኮ በመብረር በዶራዶስ ዶ ሲናሎአን መጫወቱን የግል የታሪክ ማህደሩ ያስነብባል። ታዲያ በዚህ ክለብ ያሳለፈው ጊዜ አጭር ቢሆንም በእግር ኳስ ህይወቱ ማርሽ ቀያሪው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

በሜክሲኮ ቆይታው የታክቲክ እውቀቱን በማጎልበት ልዩ የስልጠና ዘይቤ እንዲከተል እና የተለያዩ የእግር ኳስ አስተሳሰቦችን እንዲገነዘብ አስችሎታል። በተጨማሪም ወደ አርጀንቲና ተጉዞ ከአሰልጣኝ ማርሴሎ ቤልሳ እግር ስር በመማር አዲስ የስልጠና አስተሳሰብ ፈጥሯል። በተለይ ጓርዲዮላ በካታሎኑ ክለብ ቤት በነበረበት ወቅት ይታወቅበት የነበረውን የቲኪ-ታካ የእግር ኳስ ፍልስፍና የወለደው ከአሰልጣኝ ማርሴሎ ቤልሳ ጋር ከተገናኘ በኋላ ነው።

ጓርዲዮላ የታክቲካል አባዜ የተጠናወተው አሰልጣኝ ነው ማለት ይቻላል። የጨዋታ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን(ቪዲዮችን) መመልከት፣ መተንተን እና አዳዲስ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የጨዋታ ዘይቤ እና ስልቶችን በመንደፍ ይታወቃል።

ብዙዎቹም በዚህ  አስደናቂ የእግር ኳስ ህይወቱ እና ክህሎቱ ፍቅር ወድቀው የፍልስፍናው እና የአስተሳሰቡ ምርኮኛ ሆነዋል። በ17 ዓመታት የአሰልጣኝነት  ህይወቱም ዋንጫ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የዓለምን እግር ኳስ የቀየረ አዲስ አስተሳሰብ እና ጽንሰ ሀሳብ ፈጥሯል።

የ55 ዓመቱ ስፔናዊ የልህቀት እና የፈጠራ ምልክትም ነው። የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ በላሊጋ በቡንደስ ሊጋ እና በፕሪሚየር ሊግ የተለያዩ ዋንጫዎችን በማሳካት ውጤታማ አሰልጣኝ ነው። ጆሴፕ ፔፕ ጓርዲዮላ በፈጠራ የተካነ፣ ታታሪ፣ የላቀ የታክቲክ ግንዛቤ ያለው እና ድንቅ ጨዋታን የማንበብ ክህሎት ያለው የዘመናችን ታላቅ አሰልጣኝ ነው።

 

በባርሴሎና እና በማንቸስተር ሲቲ ቤት የሦስትዮሽ ዋንጫ በማንሳት የመጀመሪያው አሰልጣኝ ነው። የአውሮፓ ክለቦች የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር በማሳካት የመጀመሪያው አሰልጣኝ ነው። በላሊጋ፣  በቡንደስ ሊጋ እና በፕሪሚየር ሊጉ በተከታታይ የሊግ ዋንጫዎችን በማሳካት ባለክብረወሰን ነው።

ጓርዲዮላ ዋርካ ነው፤ አሁን ላይ በእርሱ የስልጠና እና አስተሳሰብ የተማረኩ እና የተጠለሉ በርካታ አሰልጣኞች አሉ። የእርሱ የእግር ኳስ ጥልቅ ስሜት የተጋባባቸው እና የተጠናወታቸው የእግር ኳስ ሊሂቃን አሁን በአውሮፓ ምድር አንቱ ተብለዋል። ገሚሶች የእርሱ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እውቀቱን የተቋደሱ ናቸው። ገሚሶች ደግሞ በተጫዋችነት ዘመናቸው ወደ አሰልጣኝነት ህይወት የሚያመራቸውን እውቀት ከታላቁ አሰልጣኝ ሸምተዋል።

የወቅቱ የአርሴናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በኢትሀድ የጓርዲዮላ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ አገልግሏል። የመድፈኞች አለቃ ከ2016 እስከ 2019 እ.አ.አ ለሦስት ዓመታት በኢትሀድ የጓርዲዮላ ረዳት ሆኖ በሠራባቸው ዓመታት ሁሉንም ዓይነት የታክቲክ ስልቶች፣ በተጫዋቾች ዘንድ በምን መንገድ የአሸናፊነት ስነ ልቦና እንደሚገነባ እውቀትን ቀስሟል። ከጓርዲዮላ በቀሰመው ልምድ እና እውቀትም ከ2019 እ.አ.አ ጀምሮ በኤምሬትስ ተግባራዊ እያደረገው ይገኛል።

የ44 ዓመቱ ስፔናዊ ኤምሬትስ ከደረሰ በኋላ የፕሪሚየር ሊጉ ዋነኛ ተፎካካሪ አድርጎታል። በወጣቶች የተሞላ ቡድን በመገንባት በሁሉም የሜዳ ክፍል ክለቡን አስፈሪ ማድረግ ችሏል። በ2022/23 እና በ2023/24 የውድድር ዘመን በተከታታይ በፕሪሚየር ሊጉ እስከመጨረሻው በመፎካከር ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ክለቡ ዘንድሮም የሊቨርፑል ተፎካካሪ ሆኖ ዓመቱን ዘልቋል። በታላቁ መድረክ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም በሩብ ፍጻሜው የስፔኑን ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድን በሰፊ ውጤት በመርታት ግማሽ ፍጻሜ ድረስ መጓዙ አይዘነጋም።

የጓርዲዮላ ትልቅ ተጽእኖ ያረፈበት ሌላኛው ስፔናዊ አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ ነው። ዣቢ አሎንሶ በሁለት ታላላቅ ክለቦች ሊቨርፑል እና ሪያል ማድሪድ ቤት ከተጫወተ በኋላ በ2014 እ.አ.አ ወደ ጀርመን አቅንቶ የባቫሪያኑን ክለብ ተቀላቅሏል። የቀድሞው የመሀል ሜዳ ሰው በጓርዲዮላ ስር ለሁለት ዓመታት ሰልጥኗል። እ.አ.አ በ2017 ከተጫዋችነት ህይወቱ በመገለል በሪያል ሶሲዳድ ሁለተኛ ቡድን የአሰልጣኝነት ህይወቱን ጀምሯል። ከሦስት ዓመታት በኋላም እ.አ.አ በ2022 የጀርመኑን ክለብ ባየር ሊቨርኩሰን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል።

የ43 ዓመቱ አሰልጣኝ አሎንሶ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በቡንደስ ሊጋ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን አሳክቷል። በተጨማሪም ባየርሊቨርኩሰን የዲኤፍ ቢ ፖካል ዋንጫን ከ30 ዓመታት በኋላ  አንስቷል። በውድድር ዓመቱ በአጠቃላይ 51 ጨዋታዎችን ባለመሸነፍ በአውሮፓ ምድር አዲስ ክብረወሰንም ሰብሯል። ታዲያ አሎንሶ ከጀርመኑ ክለብ ጋር ያለው የውል ስምምነት በቅርቡ ይጠናቀቃል። የጣሊያናዊው አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ወደ ብራዚል ማቅናትን ተከትሎ የኃያሉን ክለብ ዙፍን ይቀመጥበታል ተብሎ ይገመታል።

ስፔናዊው የቀድሞ  የባርሴሎና አማካይ ዣቪ ሄርናንዴዝ በእግር ኳሱ ዓለም ከታዩ ምርጥ የመሀል ሜዳ ኦርኬስትረኞች መካከል አንዱ ነው። የ45 ዓመቱ አሰልጣኝ በተጫዋችነት ህይወቱ ከስፔን ብሄራዊ ቡድን እና ከካታለኑ ክለብ ጋር ያላሳካው ዋንጫ የለም። ፔፕ ጓርዲዮላ ከ2008 እስከ 2012 እ.አ.አ ባርሴሎናን ባሰለጠነበት ወቅት የቲኪ ታካ ዋነኛው አቀነባባሪ እና የልብ ምት ዥቪ እንደነበር አይዘነጋም።

ዣቪ በኳታሩ ክለብ አል ሳድ የአሰልጣኝነት ህይወቱን ከጀመረ በኋላ በ2021 እ.አ.አ የባርሴሎና አለቃ ሆኖ በዩሀን ላፖርታ ተሿሟል። በኑካምኘ በቆየባቸው ሦስት ዓመታትም የላሊጋን ዋንጫ አሳክቷል። ኳስን በመቆጣጠር እና ተጭኖ መጫወትን (ፓዚሽናል ፕሌይ) ፍልስፍና ከጓርዲዮላ ተምሮ እና ከራሱ ጋር በማዋሀድ የሚከተለው ፍልስፍና ነው።

የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትዱ እና የአያክስ አምስተርዳም አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ከላንክሻየሩ ክለብ ጋር ከተለያየ በኋላ አሁን እረፍት ላይ ይገኛል። የ55 ዓመቱ ኔዘርላንዳዊ አሰልጣኝ ምንም እንኳ የኦልትራፎርድ ሥራ ከብዶት ከክለቡ ጋር ቢለያይም በአያክስ አምስተርዳም ግን በወጣት ኮከቦች የተሞላ ቡድን በመገንባቱ እና አስደናቂ ገድል መሥራቱን የእግር ኳሱ ዓለም ይመሰርክራል።

በኤርዲቪዚው ከአያክስ ጋር ሦስት ተከታታይ ዋንጫዎችን አሳክቷል። በተጨማሪም ሁለት የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን ማሳካቱ የሚታወስ ነው። ኤሪክ ቴን ሀግ የጓርዲዮላ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ለሁለት ዓመታት በጀርመኑ ክለብ ባየርሙኒክ ቤት አገልግሏል። ታዲያ የጓርዲዮላን የእግር ኳስ ፍልስፍናን ተግባራዊ በማድረግ በአያክስ አምስተርዳም ድንቅ ጊዜ አሳልፏል። ቴን ሀግ በአንድ ወቅት “ከጓርዲዮላ ብዙ ተምሬአለሁ” በማለት የእርሱ ደቀመዝሙር እንደሆነ አረጋግጧል።

የባየርሙኒኩ አሰልጣኝ ቪኒሴንት ኮምፓኒ ሌላኛው የጓርዲዮላ ተማሪ ነው። ኮምፓኒ ከ2016 እስከ 2019 እ.አ.አ በኢትሀድ አምበል በመሆን ከስፔናዊው አለቃ ጋር አብሮ ሠርቷል። ታዲያ በተጫዋችነት ዘመኑ ከጓርዲዮላ በተማረው የአጨዋወት ስልት እና ፍልስፍና በ2022/23 የውድድር ዘመን በርንሌይን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማሳደጉ አይዘነጋም። ዘንድሮ ደግሞ በመጀመሪያው የቡንደስ ሊጋ የውድድር ዓመቱ ከባየርሙኒክ ጋር የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ አንስቷል።

ኤንዞ ማሬስካም ሌላኛው የፔፕ ጓርዲዮላ ተማሪ መሆኑን የጎል ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል። ጣሊያናዊው የ45 ዓመቱ አሰልጣኝ በ2021 የማንቸስተር ሲቲ አካዳሚ ሥራ አስኪያጅ በመሆን የተቀጠረ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ የጓርዲዮላ ረዳት አሰልጣኝ መሆን ችሏል። እ.አ.አ በ2023 የሻምፒዮን ሺፑን ክለብ ሌሲስተር ሲቲን በመረከብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አሳድጎታል። የስፔናዊው ታክቲሺያን ተጽእኖ ያረፈበት ማሬስካ ካሳለፍነው የውድድር ዓመት ጀምሮ የምዕራብ ለንደኑን ክለብ ቸልሲን እያሰለጠነ ይገኛል።

በተመሳሳይ የፈረንሳዩ ክለብ አሰልጣኝ ሊዊስ ኢኔሪኬ በጓርዲዮላ ጥላ ስራ እየኖረ ያለ ባለሙያ ነው። አሰልጣኝ ኢኔሪኬ ከ1996 እስከ 2004 እ.አ.አ በኑካምፕ አብረው ተጫውተዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ጓርዲዮላ የባርሴሎና ዋናው ቡድን አሰልጣኝ በሆነበት ወቅት ኢኔሪኬም ሁለተኛውን ቡድን እያሰለጠነ እንደነበር የታሪክ ማህደራቸው ያስነብባል። እናም የፓርሴን ዥርሜኑ አሰልጣኝ በቅርብ ሆነ የጓርዲዮላን እውቀት ከተቋደሱት አሰልጣኞች መካከል እንደሆነ ጎል ዶት ኮም አስነብቧል።

ምንም እንኳ በአሰልጣኝነት ህይወቱ ብዙም ባይገፋበትም የቀድሞው የአርሴናሉ እና የባርሴሎናው ኮከብ ቴሪ ዳንኤል ሄነሪም ሌላኛው የፔፕ ተማሪ ነው። ጓርዲዮላ በዘመናዊ እግር ኳስ ከሚያሳድረው ተጽእኖ እና ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ብዙ ደቀ መዝሙሮችን ያፈራ አስተማሪ ጭምር ነው ማለት ይቻላል። ሁሉም ተማሪዎቹ የሚከተለውን የእግር ኳስ አስተሳሰብ እና ፍልስፍና ተግባራዊ ማድረጋቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል።

የዣቪ ሄርናንዴዝ፣ የሚኬል አርቴታ እና የዣቢ አሎንሶ የኳስ ቁጥጥርን ስንመለከት በፍጥነት ጓርዲዮላን  አዕምሯችን ያስታውሰናል። ተጭኖ በመጫወት እና የተደራጀ የመከላከል ስልትን ተግባራዊ የሚያደርጉት ሚኬል አርቴታ እና ዣቪ ሄርናንዴዝን ማስታወሳችን ተገቢ ይሆናል። ተለዋዋጭ ታክቲክ እና ፈጠራ ኮምፓኒ እና ኤሪክ ቴን ሀግ ተግባራዊ የሚያደርግ ቡድን ገንብተው አሳይተዋል። በተጫዋቾች ዘንድ ጠንካራ የመሪነት እና የአሸናፊነት  ስነ ልቦናን በማስረጽ አርቴታ፣ ዣቪ  ሄርናንዴዝ እና አሎንሶ ውጤታማ ሆነውበታል። ታዲያ ለዚህ ያበቃቸው ከጓርዲዮላ ስር ተቀምጠው መማራቸውን የስፖርት ዱኒያ መረጃ አስነብቧል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here