በ50ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የሚገኝ የእናቴ ጎረቤት የነበረ ሰው ከብዙ ዓመታት በኋላ ወደ ሥራ ስሄድ ድንገት ተገናኘን። ሳገኘው የቀኝ እግሩ አውራ ጣት እብጠት ፈጥሮበት እያስነከሰ ነበር፡፡ ምነው? ምን አግኝቶህ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ከሰላምታ ልውውጥ በኋላ አስከተልኩልት። ባለፉት ሁለት ዓመታት የሪህ በሽታ ተገኝቶበት ሕክምና እየተከታተለ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ እንዴት ሊከሰትብህ ቻለ? በማለት ተጨማሪ ጥያቄ አነሳሁ። አብዝቶ ስጋ ይወድ እንደነበር በማንሳት ምክንያቱ ከዚህ ጋር እንደሚገናኝ ነገረኝ፡፡ እኔም ምህረቱን ፈጣሪ እንዲልክለት ተመኝቼ ወደ መሥሪያ ቤቴ አቀናሁ፡፡
በውስጤ እውነት ስጋ አብዝቶ መመገብ የሪህ ምክንያት ነው? እያልኩ እየተብሰለሰልኩ ነበር፡፡ ከስጋ ውጪ ሌላ ምግብ ያለ የማይመስላቸው በርካታ ወዳጆቼ አሉና ሁኔታው አሳሰበኝ፡፡ ይህን ጉዳይ ለመቋጨትም እንደኔ ግራ የተጋባ ሰው ሊኖር ይችላል በማለት በአሁኑ ሳምንት የጤና አምዳችን የሪህ በሽታን በተመለከተ በኩር ከባለሙያ ጋር ቆይታ እንድታደርግ ከባልደረቦቼ ጋር ተስማማን፡፡
ዶ/ር ይልቃል1. አቤ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እና መምሕር ናቸው። የሪህ በሽታን በተመለከተ ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
ሪህ ምንድነው? ብለን የመነሻ ጥያቄ አቅርበንላቸዋል። ዶ/ር ይልቃል እንዳብራሩት ሪህ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው ዩሪክ አሲድ የሚባል ኬሚካል በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር በደማችን ውስጥ እና በመገጣጠሚያዎቻችን በመሄድ ይጠራቀማል። ይህም መገጣጠሚያችን እንዲቆጣ፣ እንዲቀላ እና እንዲያብጥ ያደርገዋል፡፡ በተለምዶ የዚህ ሕመም መጠሪያም ሪህ ወይም በእንግሊዘኛው (gout arthritis) ተብሎ ይጠራል፡፡ በአጭሩም ሪህ በሰውነታችን ውስጥ ዩሪክ አሲድ በመጨመሩ ምክንያት የሚፈጠር በሽታ መሆኑን ነው ዶክተር ይልቃል ያስገነዘቡት፡፡
እንደ ዶ/ር ይልቃል ሙያዊ ማብራሪያ ዩሪክ አሲድ የሚፈጠረው ህዋሶቻችን ሲያረጁ ነው፡፡ ህዋሶቻችን የተሠሩበት ኬሚካል ዕድሜያቸው ሲገፋ ወይም ሲያረጁ ይሞታሉ፡፡ ህዋሶቻችን ሲሞቱ የሚፈጠረው የመጨረሻ ውጤት ነው ዩሪክ አሲድ የሚባለው፡፡ አብዛኛው በደማችን ውስጥ የሚገኘው ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ዩሪክ አሲድ ምንጩ ያረጁ ህዋሳት ናቸው፡፡
ሁለተኛው ዩሪክ አሲድ የሚፈጠረው (የምናገኘው) በተለያዩ ምግቦች ምክንያት ነው። በተለይም የፕሮቲን ይዘት ያላቸውን ምግቦች ማለትም ሥጋ፣ አቮካዶ፣ እንቁላል፣ ባቄላ… በብዛት ስንወስድ (በምንመገብበት ጊዜ) በሰውነታችን ውስጥ ዩሪክ አሲድ ይፈጠራል፡፡
ከአምስት እስከ 10 በመቶ የሚሆነው ዩሪክ አሲድ የሚገኘውም ከምግብ ነው፡፡
በተለምዶ በወንዶች ደም ውስጥ የሚገኝ የዩሪክ አሲድ መጠን ጤነኛ የሚባለው እስከ ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊ ግራም ሲሆን ለሴቶች ደግሞ እስከ አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊ ግራም ይደርሳል፡፡ መጠኑ በሁለቱም ጾታዎች ከዚህ በላይ ከሆነ ግን የሪህ ሕመም ይከሰታል ሲሉ ነው ዶክተር ይልቃል ያብራሩት፡፡
ዩሪክ አሲድ ለሰውነታችን ጠቃሚ ሲሆን ነገር ግን ሲበዛ ለበሽታ እንደሚዳርግ ነው የጤና ባለሙያው የገለጹት፡፡ ሪህ በአብዛኛው የሚያጠቃው በዕድሜ ገፋ ያሉ ወንዶችን ሲሆን የወር አባባ ማየት ያቆሙ (ያረጡ) ሴቶች ላይም እንደሚከሰት ነው የጠቆሙት፡፡
የሪህ በሽታ በዋናነት ስለሚያጠቃው የሰውነት ክፍልም ለዶክተር ይልቃል ጥያቄ አንስተንላቸው የሚከተለውን ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል። በሽታው ከሰውነት ክፍል ውስጥ ከ70 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው የሚያጠቃው የእግርን አውራ ጣትን ነው። በቁርጭምጭሚት፣ በጉልበት እና ክርን ላይም ሊከሰት ይችላል፡፡
በሪህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ መገጣጠሚያ ላይ ድንገተኛ እና ሊቋቋሙት የማይችሉት ሕመም እንደሚከሰትባቸው ነው ያብራሩት። የሪህ ሕመም ድንገት ሊከሰት ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ እኩለ ሌሊት ላይ የእግር አውራ ጣት በእሳት የተቃጠለ አይነት ሕመም ሊሰማና ከእንቅልፍ ሊያነቃ ይችላልም ነው ያሉት፡፡
ዶ/ር ይልቃል እንዳሉት ሪህ ያለበት ሰው የሚያሳየው ምልክት የመገጣጠሚያ ሕመም ነው፡፡ በመገጣጠሚያ አካባቢ መቅላት፣ ማሳከክ እና እብጠት ይኖራል፡፡ ከዚያም ከባድ የሕመም ስሜት ይከሰታል፡፡ በተጨማሪም ዩሪክ አሲድ በመጨመሩ ምክንያት በሚፈጠር የኩላሊት ጠጠር ማቅለሽለሽ፣ ማዞር እና ከፍተኛ ሙቀት ሊከሰት እንደሚችል ነው የጠቆሙት፡፡
አልኮል አዘውትሮ መጠቀም፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የኩላሊት ሕመም ያለበት ሰው፣ በብዛት ፕሮቲን ያላቸውን ምግቦች መመገብ (የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ)፣ ጣፋጪነት ያላቸውን ምግቦች እና መጠጦችን አዘውትሮ መመገብ እና መጠጣት፣ ከቤተሰብ አባል ሪህ የነበረበት ሰው ካለ እና አንዳንድ መድኃኒቶች ለሪህ አጋላጪ ምክንቶች መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ዶክተር ይልቃል ከሪህ ለመጠበቅ ወይም ሪህን ለመከላከል የሚያስችሉ መንገዶችንም ነግረውናል። አመጋገብን ማስተካከል እና አልኮል አዘውትሮ ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት ሙሉ በሙሉ ስጋ መብላት አቁሙ ማለት ሳይሆን አመጋገብን ማስተካከል ይገባል። “ዋናው የዩሪክ አሲድ መገኛ ያረጁ ህዋሳት በመሆናቸው ይህን ምግብ ብሉ ያኛውን አትመገቡ አይባልም ነው” ያሉት፡፡ “አንድ ሰው የተመጣጠነ ምግብ መመግብ አለበት። ነገር ግን የበሬ ስጋ መመገብ የሪህ በሽታን ያባብሳል የሚለው አባባል ነው” የሚሉት ዶ/ር ይልቃል “አዘውትረን ሥጋ ብቻ አንመግብ ነው እንጂ ከማዕዳችን ይጥፋ አላልንም” ነው የሚሉት፡፡
ሰዎች በተከታታይ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት እያሉ ስጋ ብቻ መብላት የለባቸውም፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ማለትም አትክልትና ፍራፍሬዎችን እና የእህል ዘሮችን በማዕድ ውስጥ በማካተት መመገብ አለባቸው፡፡ ይሁንና አዘውትረን ሥጋ የምንመገብ ከሆነ የዩሪክ አሲድ መጠኑ ሊጨምር ይችላል ነው ያሉት፡፡
ሪህ ሙሉ በሙሉ የሚጠፋ በሽታ አይደለም፡፡ የተከሰተበት ምክንያት ከታወቀ ምክንያቱን ማከም ነው የተሻለ የሚሆነው የሚሉት ባለሙያው በመሆኑም እንደ የልብ፣ ግፊት እና ስኳር ሕመሞች ሪህም ሁልጊዜ ክትትል እና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው በሽታ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ይልቃል ማብራሪያ ሕክምና ከተከታተልን ሕመሙን ማስታገስ ይቻላል፡፡ ጨርሶ ግን ሊጠፋ አይችልም፡፡
ሪህ በፍጥነት ካልታከመ የመገጣጠሚያ ቅርጽን እንደሚያበላሽ የተናገሩት ዶ/ር ይልቃል ሪህ በባሕላዊ መንገድ ይድናል ወይ ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ በጥናት የተረጋገጠ ነገር እንደሌለ ነው ያስረዱት:: ዩሪክ አሲድ በደም ውስጥ በአረጁ ህዋሳት አማካኝነት የሚፈጠር ስለሆነ እሱን ማስወገድ የሚችል የባሕል መድኃኒት የለም ነው ያሉት፡፡ ይሁንና ሕመሙንና እብጠቱን ሊያስታግሱ እንደሚችሉ በማንሳት ነገር ግን በባሕላዊ መንገድ የሚደረገው ሕክምና በጥናት መደገፍ አለበት ነው የሚሉት፡፡
ዶ/ር ይልቃል ለሕብረተሰቡ ባስተላለፉት መልዕክት የመገጣጣጠሚያ ሕመም ሁሉ ሪህ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “ይህ አመለካከት ወይም ድምዳሜ መታረም አለበት፡፡ በትልቁ የእግር አውራ ጣት ላይ ሕመም፣ መቅላት እና እብጠት ሲኖር እንዲሁም በሽታው የሚያስከትለው ሕመም ድንገተኛ እና ብዙውን ጊዜ በሌሊት ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ ከሆነ እነዚህ የሪህ ምልክቶች ናቸው። በመሆኑም ወደ ሕክምና ተቋም መምጣት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡ ሕክምና ቦታም ምልክቶቹን በማየት እና እብጠቱ ላይ በሚኖረው ፈሳሽ ናሙና በመውሰድ በቤተ ሙከራ ምርመራ መለየት እንደሚቻል ነው የገለጹት፡፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም