መስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር) “ልመና የተራቀቀ ማኅበራዊ ዝቅጠት ነው!…” በማለት በኅዳር 2006 ዓ.ም በማህበራዊ ድረ ገጽ አስፍረዋል፡፡ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮም “ከፍተኛ የማህበራዊ ችግሮች ከሆኑት አንዱ ልመና ነው!” በማለት የምሁሩን ሀሳብ ያጠናክራል፡፡ በተለይ በከተሞች ውስጥ እየተስፋፋ የሚታየው ልመና የመሥራት የባህል ዝቅጠት ማሳያ እንደሆነ ነው በቢሮው የማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያ መከታተያ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ፀጋ የተናገሩት፡፡
አንዱ ማህበራዊ ችግር ከሚገለጽባቸው መንገዶች ልመና አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ሰዎች ከችግር አንፃር ወደ ልመና እንደሚወጡ ቢታሰብም አሁን ግን የማህበረሰቡን እሴት በሚጎዳ መንገድ እየተስፋፋ ያለ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ በላይነህ ማብራሪያ ችግርን በራስ መንገድ መቋቋም እና ጉልበት እያለ ሰርቶ መኖር እየተቻለ ቁጭ ብሎ ምጽዋት መጠየቅ ሲለመድ “ሰዎች ምን ሊሉኝ ይችላሉ?” የሚለውን በመተው ሰዎች ከማህበረሰቡ የሥራ እሴት ያፈነገጡ ይሆናሉ፡፡
ጎዳና የሚወጣው የሰው ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት ቁጥሩ እየጨመረ እና አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን አቶ በላይ ጠቁመዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶችም በልመና ስለሚተዳደሩ ነው፡፡ በተለይ ችግሩ በከተሞች አካባቢ እየተባባሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ችግሩን ያባባሰው ሌላው ምክንያት የመሥራት አቅም የሌላቸው እና ጧሪና ደጋፊ ያጡ በተለይም ሴቶች እና ህፃናት ወደ ጎዳና መውጣትን እንደ አማራጭ በመውሰዳቸው ነው፡፡
በልመና ዙሪያ ዝርዝር ጥናት ማካሄድ ባይቻልም በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች በተሰበሰበ መረጃ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደደረሰ ታውቋል፡፡ እስካለፉት ሦስት ወራት በተካሄደ ጥናት በክልሉ ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ብቻ በልመና ተሰማርተው የነበሩ አምስት ሺህ ድረስ የነበሩ የጎዳና ተዳዳሪ እና አቅመ ደካማ ዜጎች ቁጥር ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ 10 ሺህ አሻቅቧል፡፡
እንደ አቶ በላይነህ ገለፃ እነዚህን በልመና የተሠማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለልመና የሚገፋቸው ዋና ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው ሲጠና ጎዳና ከወጡት መካከል 32 ከመቶው የሚሸፍነው በድህነት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በቤተሰብ አቅም ማጣት እና በኑሮ ውድነት የዕለት ጉርስ በማጣት ወደ ጎዳና ለልመና የሚወጡት ዜጎች ደግሞ ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ልመና እንዲስፋፋ ያደረገው ሌላው የአመለካከት ችግር ነው፡፡ ይህም ሃብት እና የመሥራት አማራጭ እያላቸው ወደ ልመና ገብተው ተጨማሪ ሃብት የመፍጠር አመለካከት መኖር ነው፡፡
እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ደሃ እና አማራጭ የሌላቸው ቢሆኑም እንኳን ሌሎች አማራጮችን መሞከር ሲገባቸው ልመናን እንደ ዋና ገቢ ምንጭነት የመጠቀም የአመለካከት ችግር በመኖሩ ለልመና እንደሚወጡ ጥናቱን ዋቢ አድርገው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ገፊ ምክንያቶች በጤና እና በደጋፊ ማጣት የመሥራት አቅማቸው ሲደክም የጎዳናን ኑሮን እንደ አማራጭ መጠቀም ናቸው፡፡
በተለይ አረጋዊያን እና ሴቶችን የሚገፋው የአቅም ማነስ፣ የሰላም እጦት… እንደሆነ በጥናቱ ተለይቷል፡፡ በክልሉ ያለው የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ (ግጭት) ለልመና ከፍ ያለ ድርሻን ይዟል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደገለፁት የተፈጥሮ አደጋ /የመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ/ በመሣሰሉ ችግሮች ምርት ሲታጣ “ምን ልብላ?” በሚል ምክንያት ወደ ለልመና በተለይም ወደ ከተማ የሚሰደዱ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ ነገሮች ከተስተካከሉ በኋላም እንደ ሃብት ማግኛ አማራጭ አድርገው በማሰብ ወደ መጡበት አይመለሱም፡፡ ሌሎችም እነሱን በመመልከት ወደ ልመና እንዲገቡ የሚገፉበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡
ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ግን ድህነት እና የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ደረጃ ተፅእኖ አድርሶባቸው ወደ ጎዳና የሚወጡ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ነው መረጃው የሚያሣየው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ በልመና የተሰማሩ ዜጎችን ወደ መጡበት አካባቢ በመመለስ እስከ ወረዳ ድረስ ስልጠና በመስጠት እና የሥነ ልቦና ድጋፍ በማድረግ ወደ ገቢ ማስገኛ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ ይደረጋል፡፡
በመንግሥት ደረጃ ደግሞ ለልመና የወጡ እና ተጋላጭ ለሆኑ ዜጐች ብሄራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፓሊሲ ስላለ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ እና ማህበራዊ ችግር ያለባቸውን ገና ሳይፈናቀሉ ጀምሮ ባሉበት አካባቢ የግንዛቤ ፈጠራ ለመስራት በአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ማህበራዊ ጥበቃ ፓሊሲ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ተቋቁሟል፡፡
ለልመና የወጡትን ለመደገፍ የሚሰሩ በርካታ አጋር አካላት እንደሌሉ ያነሱት አቶ በላይነህ፤ የማህበረሰቡ ተቋማት ፣ዕድሮች እና ጥምረቶች ለግለሠቦች ቋሚ ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሠራ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃር የተከናወነው ሥራ በቂ እንደዳልሆነአንስተዋል፡፡
ልመና ከሥር መሠረቱ ባይጠፋም ማህበረሰቡ የቆየ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባህሉን ተጠቅሞ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትን አስተባብሮ ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የማህበራዊ ጥበቃ ፓሊሲውን ይዞ የማስተባበር ሚናውን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባውም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን ለማህበራዊ ጥበቃ ምንም አይነት በጀት የለም ያሉት አቶ በላይነህ፤ ጎዳና የቆዩ ሰዎችን ወደ አካባቢ ለመመለስ ከቆዩበት አንፃር የጤና እና የስነ ልቦና ድጋፍ እንዲሁም ለወጣቶች ሱስ ጀምረው ስለሚሆን ተሃድሶ ለመስጠት ከፍተኛ ወጭ ስለሚጠይቅ በአግባቡ ሊታይ ይገባል ይላሉ፡፡
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ወጣቶች ላይ ሲሰሩ በጎዳና ልመና ላይ ያሉትንም ችግር ለመፍታት ትኩረት ቢያደርጉ ችግሩን መቀነስ እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም