የባህር ውስጥ ሽክርክሪትን ለኃይል ምንጭነት

0
61

በጥልቅ ባሕር ውስጥ የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሁነቶችን ካሜራ በተገጠመባቸው አነስተኛ መጠን ባላቸው ባሕር ሰርጓጅ ሮቦቶች ለመከታተል እና ለማጥናት በውስጥ የሚፈጠር ሞገድን በመንቀሳቀሻ የኃይል ምንጭነት ማዋል እንደሚቻል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡

በአሜሪካ የካሊፎርኒያ የቴክኖሎጂ ተቋም በኘሮፌሰር ጆን ዲቢሪ የሚመራው   የተመራማሪዎች ቡድን በተፈጥሯዊው “ጄሊፊሽ” ዓሳ አናት ላይ ካሜራ በማሰር ያደርጉት ከነበረው ክትትል እና ጥናት በአነስተኛ ባህር ሰርጓጅ ሮቦት መከወን ተመራጭ ሆኖ አግኝተውታል፡፡

በ “ጄሊፊሽ” አናት ካሜራ ተገጥሞ በሚደረገው ቀረፃ እና ክትትል   ለሁነቶች ምላሽ መስጠት  መቆጣጠር እንደማያስችል የጠቆሙት ተመራማሪዎቹ በሮቦቶች ላይ ግን በሰው ሰራሽ ኪሄሎት (AI) በመታገዝ መንቀሳቀሻ ቀጣናን፣ አቅጣጫን እንዲሁም ለጥቃቅን ችግሮች ተገቢ  ውሳኔ መስጠት ማስቻሉን ነው የደረሱበት፡፡

የኘሮፌሰር ጆን ዲቢሪ የቀድሞው የድህረ ምረቃ ተማሪው ዶክተር ፒተር ጉናርሰን ከ አንድ ዓመት በፊት አምስት ሜትር ርዝመት ባለው ውኃ መያዥ በርሚል ስለውኃ ሽክርክሪት ወይም ቀለበቶች ናሙና ምርምር  አካሂዷል፡፡ ሽክርክሪቶቹ ወይም ሞገዶቹ አንዱ በአንዱ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅእኖም መገንዘብ ችሏል፡፡

ውጤቱን በአብነት ሲያስረዳም አዕዋፍ በርከት ብለው ሲበሩ ለመፍጠን አንዱ ከአንዱ በላይ ወጥቶ ከመቅዘፍ ይልቅ በአንዱ ትይዩ ፊት እና ኋላ ሆነው ሲከንፉ ኃይል መቆጠብ እንደሚያስችላቸው ነው በአስረጂነት ያሰመረበት- ዶክተር ፒተር ጉናርሰን፡፡

በባሕር ውስጥ የሚፈጠሩት ሞገዶችም በጢስ ከሚፈጠር ቀለበት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው መሆኑንም በናሙና ሙከራው አረጋግጧል- ዶክተር ፒተር ጉናርሰን፡፡ እያንዳንዱ ቀለበትም ርቀቱን ጠብቆ እየተገፋፋ መንቀሳቀሱን ተገንዝቧል፡፡

በመጨረሻም ባህር ስርጓጅ ሮቦቶች በባህር ውስጥ ከሚፈጠሩ ሞገዶች እና ሽክርክሪቶች በተቃራኒ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በትይዩ የኃይል ምንጭ ሆነው እንዲያገለግሏቸው ማስቻል ተመራጭ እና ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግድ መሆኑንም በማጉላት ነው  የድረ ገጹ ጽሁፍ ያደማደመው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here