በፀጉሯ የተንጠለጠለችው ባለክብረወሰን

0
56

የ39 ዓመቷ ጐልማሳ ፀጉሯ በመቆንጠጫ ታስሮ ዓየር ላይ ለ25 ደቂቃ ተንጠልጥላ በመቆየቷ ለክብረወሰን በቅታ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ስሟ ሊሰፍር መቻሉን ዩፒአይ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡

ጐልማሳዋ ሌይላ ኑን በካሊፎርኒያ ሬድ ውድ ብሔራዊ ፓርክ በሚገኝ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ታብቶ በተንጠለጠለ ገመድ ሽቅብ የተሰበሰበ ፀጉሯ ታስሮ ዓየር ላይ በሳቢ አቀማመጥ 25 ደቂቃ በመቆየቷ ነው ለክብረ ወሰን መዝገብ የበቃችው፡፡

አሜሪካዊቷ ጐልማሳ ከዚህ በፊት በአውስትራሊያዊቷ ሱታካራን ሲቫግናቱራይ በ23 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ የተያዘውን ክብረወሰን በ25 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ  በማስመዝገብ መስበር ችላለች፡፡ ለዚህ ድሏ ጐልማሳዋ ላለፉት ሁለት ዓመታት ስልጠና እና ልምምድ ስታደርግ መቆየቷ ለውጤት እንዳበቃት ነው በድረ ገጹ የተብራራው፡፡ ለክብረ ወሰን ከበቃችበት አፈፃፀሟ በተጨማሪ በልዩ ቅርፅ እጆችዋን በታጠፈው ጉልበቷ ላይ አሳርፋ በፅናት ረዥም ደቂቃ ዓየር ላይ መቆየቷ አድናቆት አስገኝቶላታል፡፡

ሌይላ ኑን እንዴት ረዥም ሰዓት በዓየር ላይ ተንጠልጥላ ልትቆይ ቻለች? የሚል ጥያቄ በርካታ ተመልካቾች አንስተዋል፡፡ ጐልማሳዋ ኘሮፌሽናል የሰርከስ ትርኢት አቅራቢ መሆኗ ለጥያቄው መልስ ሆኖ ነው በድረ ገጹ የተገለፀው፡፡

ሌይላኑን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፀጉሯ ታብቶ ቀጥብላ እግሮቿን ዘርግታ እጆችዋን ወደ ላይ አጥፋ ተንጠልጥላለች፤ በቀጣዮቹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ደግሞ በ “ዮጋ” ስፖርት አቀማመጥ ስልት በፅሞና ያለ እንቀስቃሴ አሳልፋለች፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here