የለውጥ መሪ

0
67

አመለካከት ሁሉንም ነገር ነው። በህይወታችን የምናተርፈው ደስታ፣ የምናገኘው ውጤት ሁሉ ስለወደፊቱ ባለን አመለካከት ይወሰናል።

በኑሯችን ውስጥ ለውጥ የምንፈልግ ብንሆንም፥ ይህን ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ትክክለኛ አመለካከቶችን ማዳበር እስካልቻልን ድረስ ለውጡን የማግኘት ተስፋችን አስተማማኝ አይሆንም። ነገር ግን የትኛው ዓለማችን በትክክል ደስታን እንደሚሰጠን፣ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ብንሄድ ግባችንን እንደምንመታ ካወቅን በህይወታችን አስደሳች ልምዶችን መገብየት እንችላለን። በዚህ ሁኔታ ከተጓዝን ደግሞ ትዕግስት የማጣት ችግር እንደማይገጥመን “አይ ዊል” ወይንም በኛው ቋንቋ አቻ ትርጉም “አደርገዋለሁ” የሚለው የቤን ስዊትላንድ መፅሃፍ ያስገነዝባል።

በስኬት እና በውድቀት መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት አንዱ የሚሰራውን ሁሉ አልችለውም ብሎ ሲያስብ፣ ሌላው ግን እችለዋለሁ ብሎ ማሰቡ ነው።

ስኬታማ ለመሆን ከፈለጉ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ በርግጠኝነት ይመኑ። ይህ እጅግ ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ አንድን ነገር እችለዋለሁ በማለትዎ ብቻ ያደርጉታል ማለት አይደለም። መጀመሪያ በርስዎና በአላማዎ መካከል ያሉትን መሰናክሎች ያጥኑ። ከዚያም መሰናክሎችን አልፈው አላማዎን ለማቀናጀት የሚያስችልዎትን የተግባር መርሃግብር ያውጡ።  የተነደፈው መርሃግብር ግብር የሚፈጸመው  በአንድ ተቋም ስር በተሰባሰቡ በርካታ ፈጻሚዎች ከሆነ ደግሞ የተቋም መሪ ሊኖር ግድ ይላል። የተቋሙ ውጤትም ሆነ ውድቀት ደግሞ በዋናነት በመሪው ብቃት ይወሰናል።

አላማችንን ለማሳካት ስንቀሳቀስ ሂደቱ በራሱ ወደ ለውጥ ሐዋርያት ይቀይረናል። ለመሆኑ ግን የለውጥ ሐዋርያ ማለት ምን አይነት ሰው ነው?     ዶክተር ማይልስ ሙንሮ “ቤኔፊትስ ኦፍ ቸንጅ” በተሰኘው መፅሃፉ እንደሚለው የለውጥ ሐዋርያ የሚለው አገላለጽ ገና በማቆጥቆጥ ላይ ያለን መሪ ያሳያል። በሚኖርበት ወቅት ወደፊት ሊመጣ የሚችል ለውጥን ምልክቶች ማየት ችሎ ለሌሎች ብሎም ለዓለም ለውጡ ዝግጅት እንዲደረግ የሚወተውት እና ሌሎችን ለመለወጥ የሚጥር ሰውን የለውጥ ሐዋርያ እንለዋለን።

በአመራር ቦታ ላይ ሆኖ ፍጹም ግራ የተጋባ ወይንም ደግሞ በለውጥ የተሸፈነ የሚመስለው ሰው ካለ የዚህ ሰው ስሜት ወደ ስራ ጓደኞቹ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ መስሪያ ቤቱን ያዛምታል ሲል ዶክተር ማይልስ ሙንሮ ይገልጻል። ሆኖም መሪዎች ሊታወቁበት የሚገባ አንድ መሠረታዊ ባህሪ ቢኖር ለራሳቸውም ሆነ ለሚመሯቸው ሰዎች ጥቅም በማሰብ ለለውጥ ውጤታማ እና ተገቢ በሆነ መልኩ አፀፋ መመለስ ይሆናል።

አንድ መሪ ሁልጊዜ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ለውጥን ቀድሞ ይጋፈጣል። በመሆኑም የአንድ መሪ ጎላ ያለውና ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሥራው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከለውጥ ጋር የሚያደርገውን ፍጥጫ በተገቢው ሁኔታ ማካሄድ እና ለውጥን በራስ ተነሳሽነት ማምጣት ነው። መሪዎች ያለ እረፍት በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው። መሪዎች የሚመሯቸውን ሰዎች ወደ ለውጥ እንዲሁም በለውጥ ውስጥ ይወስዳሉ።

ለውጥ ከዚህ በተጨማሪ የአመራር ልማት ምንጭ በመሆንም ጭምር ይታወቃል። መሪዎች ስለ ለውጥ ሲማሩ፤ ለውጥን ሲገመግሙና ትንታኔ ሲያደርጉበት የለውጥን ተፈጥሯዊ ባህሪ፣ እምቅ ኃይልን፣ ጉልበትን ብሎም አስፈላጊነትን ጭምር ይረዳሉ።

ያለ ለውጥ መምራት የማይቻል በመሆኑ ለውጥ አንድ መሪ በእጁ አሉ ከተባሉ  ትልቅ የማይዳሰሱ ሃብቶች መካከል አንዱ ነው። የአንድ መሪ ስኬት ከምንም በላይ ለውጥን በሚያስተናግድበት፣ አጸፋዊ እርምጃ በሚወስድበት፣ በሚገራበት ብሎም ደግሞ ራሱን እና ሌሎችን ተጠቃሚ በሚያደርግበት መንገድ ይለካል።

“ማንኛውም ኩባንያ፣ ቡድን፣ ሃገር እና ግለሰብ በለውጥ ሂደት ማለፋቸው አይቀሬ ነው። ሆኖም የለውጥ ልማትን ማካሄድም ግድ ይላል። ዛሬ በብዙ ኩባንያዎች ውስጥ የምናያቸው የምርምር ንዑስ የሥራ ክፍሎች በዋናነት ለኩባንያዎቹ መሻሻል በማሰብ የማያቋርጥ ፈጠራ እና የለውጥ ትግበራ እንዲኖር ለማረጋገጥ የተፈጠሩ ናቸው” በማለት ዶክተር ሙንሮ ያስገነዝባል።

በግልም ሆነ በኮርፖሬት ህይወት አመራር ከለውጥ ጋር ቁርኝት አለው፤ የአመራር ዓላማም ቢሆን ራሱ ለውጥ ነው።

መሪዎች ለውጥ የህይወት መርህ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሌሎችን በሚመሩበት ጊዜም ከዚህ ቀደም ወዳልተደረሰበት ሥፍራ እያመሩ መሆኑን እና ወደዚህ <አዲስ ግዛት> የሚደረሰው ደግሞ በለውጥ መሆኑንም ጭምር ይረዳሉ። በመሠረቱ አመራር ማለት ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችን፣ ቢዝነሶችን፣ ማኀበረሰብን ወይንም የአንድ ሃገር ህዝብን ወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ማድረስን ይመለከታል። አንድ መሪ የሱን ራዕይ የሚጋሩ ከስሩ ያሉ ሰዎችን ወደሚፈልጉት ዓላማ ለመሄድ ለውጥን እንደ ትልቅ መሣሪያ እንዲይዙት ያደርጋል።

እውነተኛ መሪ ለሚፈለገው አይነት የወደፊት ጊዜ የሚሆነውን ራዕይ ያዘጋጃል፤ የለውጥ አቅጣጫን በራሱ ተነሳሽነት ይጠቁማል፤ ወደ አንድ ዓላማ ፍፃሜ ለመድረስ ይሆናል ያለውን ተሳትፎ ያበረታታል።

አንድ መሪ ወደፊት ለማድረስ አስፈላጊ የሆነውን ቀጣይ እርምጃ ራሱ ይፈጥራል። ሂደቱን በማጎልበት ወደሚፈለገው ለውጥ ለመድረስ ወሳኝ የሆኑትን ፕሮግራሞች ጭምር ይቀርጻል።

መሪዎች ሁልጊዜም ቢሆን ለውጥ ለእነሱና ላሉበት ማህበረሰብ የሚሆን ጥቅም የሚገኝበት መልካም አጋጣሚ በውስጡ አይጠፋም ብለው በማመን በአካባቢያቸው የሚመጣውን ለውጥ ይተረጉማሉ እንዲሁም ትንታኔም  ይሰሩለታል። ሁሌም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ጥሩ ነገር አለ ብለው ያምናሉ።

መሪዎች በስራቸው ያሉ ቡድኖችን እና ሰዎችን ወደሚፈለገው የወደፊት ጊዜ ለማድረስ ሲሉ በራዕያቸው የሚመሩ ስትራቴጂዎችን ይቀይሳሉ።

አንድን መሪ መሪ የሚያደርገው አብረውት ላሉትና ለራሱ የሚመኘውን የወደፊት ጊዜ አስቀድሞ በአእምሮው መመልከት መቻሉ እና ወደ አሁኑ ጊዜ ተመልሶ ሌሎችን ወደዚያው ለመውሰድ መጣሩ እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን ይኼ ሲባል መሪዎች ወደፊት ለመሄድ በሚያደርጉት ጥረት ከሩቅ እያዩት ከመሞከር ይልቅ እዚያ ለመድረስም ጥረት ያደርጋሉ። የወደፊቱ ጊዜ ለውጥ የሚፈልግ ሲሆን መሪዎችም ለራሳቸውና አብረዋቸው ላሉት ወደተሻለ የወደፊት ጊዜ ሊያመሩ የሚችሉ ተከታታይ ለውጦችን በራሳቸው ተነሳሽነት ማምጣት ይኖርባቸዋል።

አንድ የመሪዎች ትልቁ መለያ ባህሪ ባልተጠበቀ ወይንም የተጠበቀም ቢሆን ቀውስ እና ለውጥ መሃል አይፈሩም፤ አይረበሹም። ይልቅ እነዚህ ሁኔታዎች በተቻለ መጠን ክህሎታቸውን፣ አቅማቸውን፣ የፈጠራ ኃይላቸውን እና እምቅ አቅማቸውን እንዲያወጡ መልካም አጋጣሚዎች ይሆኑላቸዋል።

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here