የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ የአራት ሳምንታት እድሜ ብቻ ቀርቶታል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር እስከ 13ኛ ሳምንት ያለው መርሀግብር በድሬድዋ እና አዳማ መደረጉ ይታወሳል። ከዚያ በኋላ ያሉት መርሀግብሮች ደግሞ በአዳማ ተደርገዋል፤ አሁንም እየተደረጉ ናቸው።ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በሂሳባዊ ስሌት ሁለት ክለቦች ናቸው እየተፎካከሩ ያሉት። ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫውን ለማንሳት የሚፎካከሩ ክለቦች ናቸው። ኢትዮጵያ መድን እስከ ስድስተኛ ሳምንት መርሀግብር በስድስት ነጥብ ልዩነት ከሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።
በአሰልጣኝ ገብረ መድን ኃይሌ የሚመራው ቡድን ዘንድሮ ዋንጫውን ለማንሳት ቆርጦ የተነሳ ይመስላል። የትኛውንም ክለብ የሚያስበረግግ የፊት መስመር እና ተጋጣሚ ሰብሮ የማይገበው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አለው። በአጠቃላይ በማጥቃት እና በመከላከሉ ረገድ የተዋጣለት ቡድን መሆኑን አስመስክሯል። የኋላ ክፍሉ በቀላሉ የማይረበሽ እና የፕሪሚየር ሊጉ ቀዳሚው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ነው።
በአቡበከር ሳኒ፣ ያሬድ ካሳዬ፣ ንጋቱ ገብረ ስላሴ እና በመሳሰሉት የሚመራው የመጀመሪያው የሜዳ ክፍል እስከ 32ኛ ሳምንት መርሀግብር 13 ግቦች ብቻ እንደተቆጠሩበት ቁጥሮች ይናገራሉ። የፊት መስመሩም አስፈሪ ሲሆን ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 41 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። ይህም ብዙ ግብ ያስቆጠረ ቀዳሚ ክለብ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ መድን በ2015 ዓ.ም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ድጋሚ ከተመለሰ በኋላ ወጥ የሆነ አቋም ሲያሳይ የዘንድሮው የመጀመሪያው ነው። በወጣት ኮከቦች የተሞላው ኢትዮጵያ መድን የፊት መስመሩ በሊጉ ከፍተኛ ግቦችን አስቆጥሯል። አሰልጣኝ ገብረ መድህን ወጣት ተጫዋቾችን ልምድ ካካበቱት ኮከቦች ጋር በማጣመር አስደናቂ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ነው።
አሰልጣኙ ከብሄራዊ ቡድኑ ኃላፊነት ከተነሱ በኋላ በክለቡ ላይ ብቻ አተኩረው እንዲሰሩ እድል ሰጥቷቸዋል። ይህም ክለቡ ስኬታማ የውድድር ጊዜ እንዲያሳልፍ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል። አምና የውድድር ዓመቱን እየተንገዳገደ የጨረሰው የአሰልጣኝ ገብረ መድን ኃይሌ ክለብ ዘንድሮ ፍጹም የተለየ ክለብ ሆኖ ዓመቱን በወጥ አቋም እያገባደደው ይገኛል።
አሰልጣኙ ዘንድሮ ቡድኑን በአዲስ መልኩ ማዋቀራቸው ስኬታማ የውድድር ጊዜ ማሳለፍ ችለዋል። በተጨማሪም ቀድሞ የሚታወቅበትን ቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ጎን በመተው በኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት ማድረጋቸው ጥሩ የውድድር ጊዜ ማሳለፋቸው ሌላኛው ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ መድኖች ከመጀመሪያዎች አራት የሊግ ጨዋታዎች ማሳካት ከነበረባቸው 12 ነጥቦች ያሳኩት ሦስት ነጥቦችን እንደነበር አይዘነጋም። ምንም እንኳ የውድድር ዓመቱን በደካማ እንቅስቃሴ ቢጀምሩም ሳምንታት ተቆጥረው ወራቶች ሲነጉዱ ግን ቀስ በቀስ ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ጠንካራ ስነ ልቦና የገነቡ መሆናቸውን የደረሱበት ደረጃ ያሳያል።
ኢትዮጵያ መድን ከውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከ23 ዓመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ ያነሳል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ መድን በ32ኛ ሳምንት ዘንድሮ ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ያለውን ሲዳማ ቡናን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ይበልጥ የዋንጫ ግስጋሴውን አሳምሯል። ክለቡ በቀጣይ መርሀግብር ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መቻል፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ስሁል ሽረ ጋር የሚገጥም ይሆናል። አሁን ላይ እያሳየ ባለው አስደናቂ አቋም የዋንጫ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል።
ሌላው በሁለተኛው ዙር ሳይጠበቅ ጠንካራ ተፎካካሪ ክለብ በመሆን ብቅ ያለው ኢትዮጵያ ቡና ነው። ቡናማዎች የመድን ተፎካካሪ ሆነው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በመጀመሪያው ዙር የነበሩባቸውን ክፍተቶች አርመው በሁለተኛው ዙር ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ መፎካከር የሚያስችለውን ውጤት አስመዝግበዋል። አሁን ላይም ከገቡበት የውጤት ቀውስ ተላቀው የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከኢትዮጵያ መድን ጋር እየተፎካከሩ ነው። ምንም እንኳ የቡናማዎች የዋንጫ ተስፋ በኢትዮጵያ መደን ነጥብ መጣል ላይ የተንጠለጠለ ቢሆንም ከ14 ዓመታት በኋላ ዋንጫውን ለማንሳት ዘንድሮ ሳይታሰብ የቀረበበት ወቅት ነው።
ባሕር ዳር ከነማ አምና እና ዘንድሮ በተጠበቀው ልክ እየተጓዘ አለመሆኑ ያስመዘገበው እና እያስመዘገበ ያለው ውጤት ይናገራል። የጣናው ሞገድ ከኢትዮጵያ መድን ቀጥሎ በሊጉ አስፈሪ የፊት መስመር ያለው ክለብ ነው። በተመሳሳይ ከመሪው ኢትዮጵያ መድን እና ከተከታዩ ቡና ቀጥሎ ከሊጉ ሁለተኛው ጠንካራ የኋላ ክፍል ነው። ይሁን እንጂ ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖት እየተንገዳገደ ይገኛል። የጣናው ሞገድ ዋንጫውን የማንሳት እድሉ በ32ኛ ሳምንት ተመናምኗል። ባሕር ዳር ከተማ ቀሪ ጨዋታውን ከአዳማ ከተማ፣ ወላይታ ዲቻ፣ ሀዋሳ ከተማ እና በመዝጊያው የሊጉ መርሀግብር ከወልዋሎ አዲግራት ጋር ይገናኛል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወትሮ ኃያልነቱ የከዳው ሌላኛው ክለብ ፋሲል ከነማ ነው። አጼዎቹ ጉልበታቸው ዝሎ በተደጋጋሚ አቅም አንሷቸው ተመልክተናል። ዘንድሮም በሁሉም የሜዳ ክፍል ያሉት ተጫዋቾች የማሸነፍ ወኔአቸው ተሰልቦ ክለቡ የቀድሞ አቋሙ ላይ እንዳይገኝ አድርጎታል። በጌታነህ ከበደ የሚመራው የፊት መስመር በ29 ጨዋታዎች 28 ግቦችን አስቆጥሯል። ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ ግቦች የፊታውራሪው ጌታነህ ከበደ ግቦች መሆናቸውን የሊግ አክሲዮን ማህበሩ መረጃ አመልክቷል።
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥብ ብቻ ርቆ የተቀመጠ ሲሆን በቀሪ መርሀግብሩ ካልበረታ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ አስከፊ ውጤት ይዞ ሊያጠናቅቅ እንደሚችል ይታመናል። ፋሲል ከነማ በቀጣይ ቀሪ የፕሪሚየር ሊግ መርሀግብር ከወላይታ ዲቻ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪ፣ አዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጋር ይጫወታል።
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ከነማ በዚህ ዓመት መልካም የሚባል የውድድር ጊዜ እያሳለፉ አይደለም። እነዚህ ክለቦች ከወራጅ ቀጠናው ብዙ አለመራቃቸው ከስጋት እንዳይላቀቁ አድርጓቸዋል። አዳማ ከተማ፣ ስሁል ሽረ እና ወልዋሎ አዲግራት አሁንም ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ተስኗቸው በቦታው የተቀመጡ ክለቦች ናቸው። በመጀመሪያው ዙር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደርገው መቀለ 70 እንደርታ ወራጅ ቀጠና ያለ ሌላኛው ክለብ ነው።
በመጨረሻዎች የሊግ ሳምንታት መርሀግብሮች ለዋንጫ ከሚደረገው ትንቅንቅ ባልተናነሰ ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክርም ትኩረትን ይስባል ተብሎ ይጠበቃል። የትኛው ክለብ ዋንጫውን ያነሳል? የትኞቹ ክለቦችስ ወደታችኛው የሊግ እርከን ይወርዳሉ? ከአራት ሳምንታት በኋላ ምላሽ ያገኛል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም